በሐዋሳ ከተማና በሲዳማ ብሔር ላይ የሚደረጉ ትንኮሳዎች ይቁሙ!


በሀዋሣ ከተማ ውስጥና በአንዳንድ የሲዳማ ዞን የወረዳ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ መጠኑ ይለያይ እንጅ በሁለቱም ብሔሮች ተወላጆች ላይ የሕይወት መጥፋትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ከዚህ በፊት በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች የሲዳማ ዞንና ከተማ አስተዳደሩ አመራር አካላት ቀርቦ የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ የተፈጠረውን ጉዳት አስመልክቶ የክልሉ መንግስትና ደኢህዴን አመራርም ይቅርታ መጠየቃቸውንም ሁሉም የሚገነዘበው ሀቅ ነው፡፡

የግጭቱ መንስኤ እየተጣራ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ድርጊቱ እኩይ አላማ ባላቸው ግለሰቦች የተፈፀመ እንጅ ሰፊውን የሲዳማን እና የወላይታን ብሔር እንደማይወክል መታወቅ አለበት፡፡

በደረሰው የፀጥታ መደፍረስ የተፈናቀሉ አካላትን ከተማ አስተዳደሩ ከክልል መንግስት፣ ከሃይማኖት መሪዎችና፣ ከከተማው ህብረተሰብ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ጊዜያዊ መጠለያ በማመቻቸት የምግብ፣የአልባሳትና የሕክምና እርዳታ ቡድን በማቅረብ እና በማሰማራት እንዲሁም ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋም የጉዳት መጠኑን የሚያሳይ መረጃ እየተሰበሰበ ለውሳኔ ሰጪነት ለመጠቀም በተሠራው ሥራ በግጭቱ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደነበሩበት መንደር ተመልሰው ጤናማ ኑሮ መምራት ከመቻላቸውም በላይ ከአካባቢው የሲዳማ ሕብረተሰብ ጋር የተለመደውን ማህበራዊ ትስስር ፈጥሯል፡፡ 

ይሁንና ቀሪዎቹን በጊዜያዊ መጠለያ ያሉትን ለመመለስ መጠነ ሰፊ ሥራዎች እየተሰሩ ቢሆንም አንዳንድ ሃላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች አሁንም በሲዳማ ብሔር እና በሀዋሳ ከተማ ላይ ያላቸውን የተዛባና አፍራሽ ዘመቻቸውን ቀጥለውበታል፡፡ 

ከሚያራምዱት አፍራሽ ዘመቻዎች መካከል፡- 
1. ከተማችን ሀዋሳ ከ8ዐ በላይ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የሚገኙባት እና ሁሉም ተቻችለው ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ መሆኗን በግላጭ በመካድ አሁን በሲዳማ ብሔርና በወላይታ መካከል የተፈጠረውን ያልተለመደ ግጭት ተጠቅሞ አፍራሽ ሃይሉ የከተማውንና የእንግዳ ተቀባይ ባህል መገለጫው የሆነውን የሲዳማን ብሔር በተዛባ መልኩ ገፅታውን ለማበላሸት አቅዶ በሚሰራ አካል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ተረድተናል፡፡

ለአብነትም፡- በአሁኑ ጊዜ በሌሎች በከተማዋ የሚኖሩ የከምባታና የሀዲያ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየተፈፀመባቸው እንደሆነ በመግለጽ የአንድ ብሔር የበላይነት አለ በሚል በአሜሪካ በተለያዩ ግዛቶች የሚኖሩ ከላይ የተጠቀሱ ብሔረሰብ ተወላጆች እንዳወገዙ ተደርጎ የተለቀቀውን መረጃ የዋልታ ቲቪ በፌስ ቡክ ገጽ አስነብቧል፡፡ 

ማንም ጤናማ አስተሳሰብ ያለው እንደሚገነዘበው በሀዋሣ ከተማ ለከንባታና ለሀዲያ ብቻም ሣይሆን ሌሎች ስማቸው ያልተጠቀሱት ብሔር ብሔረሰቦች ያለ ምንም ልዩነት ሠርቶ የመኖር መብታቸውን ተጠቅሞ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶችና የሥራ ዘርፎች ተሠማርቶ ራሳቸውንና ሕዝቡን መጥቀም የቻሉ በርካቶች መኖራቸውን ያላገናዘበ አስተሳሰብ እንደሆነ እንረዳለን፡፡

ለዚህ አፍራሽ ዘመቻ የተጠቀመው አካል የወላይታን፣የከንባታንና የሀዲያን ባህላዊ አልባሳት አልብሶ በሚዲያ መልቀቁ አንድም የማያውቀውን የክልላችን ነዋሪ ሀሳብ በተዛባ መልኩ ለመቀየርና በሌላ በኩልም አሁን በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ ሃይል ለማሰባሰብ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የተሳሳተ ዘመቻ እንደሆነና አልባሳቱን የለበሱትም የአንድ ብሔር ሰዎች ለማስመሰል ያደረጉት እንደሆነ ጉዳዮን በቅርበት ከሚያውቁ አካላት የተገኘ መረጃ ያሳያል፡፡ 

2. ሌላው ወላይታ ዞን ባህል ቱሪዝም የመ/ኮሙ/ጉዳ/መምሪያ ኦፊሰር የሆነው ግለሰብ ለጀርመን ዶቼቬለው ሬዲዮ የሰጠውን የተዛባ መረጃ ሬዲዮ ጣቢያው ተቀብሎ መዘገቡ የሚዲያውን ሚዛናዊነት ያልጠበቀ ከመሆኑም በላይ በሀዋሳ ከተማም ሆነ በሲዳማ ዞን ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ተጠይቆ ባልሰጡበት የተላለፈበት ሁኔታ በእሳት ላይ ቤንዝን የመጨመር ያህል እንደሆነ የሚዲያው አንቀሳቃሾች ሊያውቁት ይገባል፡፡ 

በየትኛውም አለም አንድ የሚዲያ ባለሙያ ዘገባዎችን በሚዘግብበት ጊዜ ሚዛናዊ ሆኖ ከስሜት በፀዳ መልኩና ህብረተሰቡን ለተጨማሪ ግጭትና ቅሬታ በማይጋብዝ መልኩ መሆን እንደሚገባው እየታወቀ የጀርመን ዶቼቬለው ሬዲዮ በከተማችን ያለውን ሁኔታ ግለሰቦች አዛብቶ የተሳሳተ መረጃ ሲሰጡ የመረጃውን ተአማንነት ማጣራት ሲገባው ይህን አለማድረጉ የጋዜጠኛውን የሙያ ሥነ ምግባር ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ሆኖ አግንተነዋል፡፡ 
በዚሁ መሠረት ትክክለኛውን በከተማችንና በሲዳማ ዞን ያለውን መረጃ በመውሰድ ሚዲያው የተፈጠረውን ስህተት ማረም ይጠበቅበታል እንላለን፡፡ 
ሲጠቃለል በአሁኑ ጊዜ በከተማችን የተፈጠረውን ሰላም ወደ ኋላ ለመቀልበስ ፍላጎቱ ያላቸው አካላት በሁለቱ ብሔሮች መካከል በተፈጠረው ግጭት አንድ ብሔር ብቻ እንደተጎዳ አድርጎ የሚለቁት መረጃና በተሳሳተ መልኩ ሃይል /አጋዥ/ አካላትን ለማሰባሰብ በዞኑና በከተማው ላይ በተለያዩ ሚዲያዎች ተጠቅመው የሚያራምዱት አቋምና የከፈቱት ዘመቻ ከአሉባልታነት የዘለለ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ 

ይህም ሲባል በተፈጠረው ግጭት በሃዋሣ ዙሪያ ወረዳ በሻመና ከተማ ገበያ ውስጥ እንደዝናብ በዘነበው የቦንብ ናዳ ብዙ የሲዳማ ብሔር ተወላጆች ሕይወታቸውን ከማጣታቸውም በላይ በርካቶች የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት እንደደረሰባቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ 

በተጨማሪም በሀዋሳ ከተማና በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በርካታ የሲዳማ ልጆች ደማቸው እንደ ውሃ ሲፈስ እና በወላይታ ዞን ዙሪያ የሚኖሩ በርካታ የሲዳማ ህዝብ ከቤት ንብረቱ ሲፈናቀል የሲዳማ ህዝብ ምንም እንኳን አላግባብ የፈሰሰው ደምና በወደመው ንብረት ሀዘን የተሰማው ቢሆንም ከወላይታ ብሔር ጋር ያለውን የረዥም ጊዜ ወዳጅነትና የማህበራዊ ትስስር ከግምት ውስጥ በማስገባት ለይቅርታና ለፍቅር እራሱን እያዘጋጀ ባለበት በአሁኑ ወቅት በግለሰቦችና በተቋም ደረጃ የሚደረግበት ዘመቻና ትንኮሳ ይቁም እንላለን፡

የከተማዋ አስተዳደር 

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት