በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር


በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ የአገሪቱ ጉዳይ ላይ ከገዢው ፓርቲ አመራር ጋር ምክክር አካሄዱ። የምክክር ተሳታፊዎች በበኩላቸው የውውይት መድረኩ በመሀል አገር የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች የሚያጋጥማቸውን የደህንነት ሥጋት ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተናግረዋል::

በሀዋሳ ከተማ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ዛሬ ከሲዳማ ክልል ገዢው ፖርቲ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የሲዳማ ብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብረሃም ማርሻሎ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተካሄደ በሚኘው ጦርነት መነሻና አሁን ያለበትን ሁኔታ ለተሳታፊዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አገር ሊያፈርስ ተነስቷል ያለውን የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ህወሃትን እየታገለ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ አብረሀም ለዚህም የትግራይ ሕዝብ በጋራ አብሮ ሊቆም ይገባል ብለዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ያሥፈለገው በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ለመያዝ መሆኑን የገለፁት አቶ አብረሀም ተሳታፊዎቹ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ጋብዘዋል፡:

አብዛኞቹ የውይይቱ ተሳታፊዎች ጦርነቱን እንደሚያወግዙ የገለፁ ሲሆን በትግራይ የሚገኘው ሕዝብ ግን የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ አመራሮችን ለመቃወም በሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም ያለው ብለዋል፡፡ ሳጅን ገብረኪሮስ ሞገስ እባላለሁ ያሉ አንድ የውይይቱ ተሳታፊ አዛውንት ከትግራይ ክልል አምልጦ ሰቆጣ አካባቢ የገባ አንድ የእህቴን ልጅ በስልክ አውርቼው ነበር ካሉ በኋላ ‹‹ አሁን ላይ ትግራይ ውስጥ አንዱ በሌላው ስለሚሰለል ስለህውሃት ምንም አይነት ነቀፌታ ያለው አስተያየት መስጠት ሕይወት ሊያሳጣ እንደሚችል ገልጾልኛል ›› ብለዋል፡፡ እኔም ብሆን ህወሃት እየካሄደ የሚገኘውን ጦርነት እዚህ መቃወምና ማውገዝ እችላለሁ እዛ ብሆን ግን አልሞክረውም ያሉት እኝሁ አዛውንት ‹‹ ነገር ግን ትግራዋይ በሙሉ የህውሃት ደጋፊ አለመሆኑን ሁሉም ሊያውቅ ይገባል ›› ብለዋል፡፡

ዶቼ ቬለ DW ካነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ጠረፍ መብራህቱ በበኩሏ የክልሉ መንግሥት ይህን መሰሉን መድረክ ማዘጋጀቱ በየአካባቢያቸው የሚያገጥማቸውን የደህንነት ሥጋት ለመቅረፍ ያግዛል ትላለች፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ‹‹ ጁንታ ›› የሚለውን ቃል ንፁሐን ተጋሩን በቂም ለማጥቃት እየተጠቀሙት ይገኛሉ የምትለው አስተያየት ሰጪዋ ‹‹ መንግሥት ንፁሃንን ከቡድኑ ተባባሪዎች ለመለየት በሚደረጉ ሂደቶች ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ›› ብላለች፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዎስ በክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች አላሥፈላጊ ሥጋት ሊያድርባቸው አይገባም ብለዋል፡፡ በእርግጥ ቀደም ሲል በአንዳንድ አካባቢዎች ግለሰቦች የደህንነት አባላት ነን ገንዘብ አምጡ አለበለዚያ እናስራችኋላን የሚሉ ማጋጠማቸውንና በወቅቱም በህግ አግባብ መታረሙን አቶ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በክልሉ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች እንደማንኛውም ዜጋ መብታቸው ተጠብቆ ሠርተው በሠላም እየኖሩ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ አለማየሁ ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ዶቼ ቬለ DW 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት