ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚቀርቡትን የገለልተኝነት ትችቶች አጣጣሉ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምርጫ ቦርድ ላይ የሚቀርቡትን የገለልተኝነት ትችቶች አጣጣሉ‹‹ምርጫ ቦርድ እየተሰደበ የሚቀጥል አይመስለኝም››  ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ
‹‹አሁንም እደግመዋለሁ ቦርዱ ገለልተኛ አይደለም››  አቶ ግርማ ሰይፉ
የ2007 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸማቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሐሙስ ሪፖርት ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ የሚሰነዘሩ ትችቶችን ጠንከር ብለው በማጣጣል ተከላከሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 18 ገጽ ባለው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው ውስጥ ዘንድሮ አገሪቱ ከምታስተናግዳቸው ትልልቅ ኩነቶችና የቀጣይ አምስት ዓመት የአገሪቱ ጉዞን ከሚወስኑ ጉዳዮች ዋነኛው፣ በግንቦት ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በግንቦት ወር የሚካሄደው አምስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና በሕዝቦች ዘንድ ዓመኔታ ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግሥት በሁሉም መስክ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዳደረገና በቀጣይ ሒደቱን በንቃት በመከታተል መንግሥታዊ ግዴታውን እንደሚወጣ አስታውቀዋል፡፡
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብና አገላለጽ ግን ሊበተን የዚህን ዓመት መገባደድ በሚጠብቀው ፓርላማ ውስጥ የተቃዋሚው የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ብቸኛ ተወካይ ለሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ አልተዋጠላቸውም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርት አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ምርጫ ቦርድ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ላይ የሰጠው ውሳኔ፣ አቶ ግርማ የሚመሩትን የፓርቲው ወገን ዕውቅና የነፈገ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹ዛሬ እንደ ወትሮው ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ዝርዝር ጉዳዮች እያነሳሁ ማብራሪያ እንዲሰጡኝ እንደማልጠይቅ የሚያውቁ ይመስለኛል፤›› በማለት የጀመሩት አቶ ግርማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ምርጫው በሕዝብ ዘንድ ዓመኔታ ኖሮት እንዲጠናቀቅ መንግሥት እየሠራ ነው ብለው የሰጡትን አስተያየት ጥያቄ አንስተውበታል፡፡ 
‹‹ምርጫ ቦርድ ከመቼ ጀምሮ ነው ለፓርቲዎች መሪ መምረጥ የጀመረው? ምርጫ ቦርድ ሕገወጥ አስተዳደራዊ ውሳኔ ለማስፈጸም የፖሊስ ኃይል ማሰማራትና ቢሮ የመዝረፍ መብት ማነው የሰጠው? ይህ የመንግሥት ግዴታ አካል መሆኑ ነው? ፍርድ ቤቶች ፓርቲዎች የሚያቀርቡትን ክስ አልቀበልም የማለት መብት አላቸው ወይ?›› ያሉት አቶ ግርማ፣ ‹‹ገለልተኛ ምርጫ ቦርድና ፍርድ ቤት በሌለበት አገር በሪፖርቱ ውስጥ የገለጹት ዓይነት ምርጫ ከየት ነው የሚመጣው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በእውቀት የተመሠረተ ከግብግብ ነፃ የሆነ ፖለቲካ በማራመድ ቁርጠኛ የሆነው አንድነት ፓርቲ ድንክ እንዲሆን መደረጉ፣ ገዥው ፓርቲም ሆነ መንግሥት የዚህ ዓይነት ፖለቲካ ለመቋቋም አቅም እንዳነሰው ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በዚህ የፖለቲካ ውሳኔ በአገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ በእርስዎ የአመራር ዘመን የተፈጸመ አሳዛኝ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል፡፡ ይህ ያስመዘገባችሁት ታሪክ ለእኔም ለእናንተም ልጆች ታሪክ ፍርድ ይቀመጣል፡፡ እንኳን ደስ ያላችሁ፡፡ እንኳን ደስ አለዎት፤›› ሲሉ የፓርላማ ንግግራቸውን ገተዋል፡፡ 
ለቀረቡት ወቀሳ አዘል ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ መስጠት የጀመሩት፣ በምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖችን በመገሰጽ ነበር፡፡ ‹‹ምርጫ ቦርድ በዚህ በተከበረ ምክር ቤት የተቋቋመ ነው፡፡ ይህ ቦርድ በአንዳንድ አካላት አላስፈላጊ ማጥላላትና ማንቋሸሽ እየተካሄደበትም ቢሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ በትዕግሥት ረዥም መንገድ መሄድ አለብኝ ብሎ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አንዳንድ ፓርቲዎች ራሳቸው የፈጠሩትን የውስጥ ችግራቸውን ጭምር እያወቁ ሌሎችን የችግሩ ፈጣሪ አድርገው የሚሳደቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሁለት መቶና ሦስት መቶ ሰዎች የሚገመቱ አባላት እርስ በርስ ተከፋፍለው ምርጫ ቦርድ ነው እኛን የከፋፈለው ለማለት ይሞክራሉ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ምርጫ ቦርድ የፓርቲዎችን ሹም ሽር የሚያደርግ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንንም አላደረገም፤›› በማለት ቦርዱን ተከላክለዋል፡፡
ምርጫ ቦርድ ያደረገው አንድነት ፓርቲ ባስገባው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የተፈጠረውን ውዝግብ መዳኘት ነው ካሉ በኋላ፣ ‹‹በአንድ ወገን የመጡት የአንድነት የዱሮ አመራሮች ናቸው፡፡ በሌላ ወገን የመጡትም የአንድነት አመራሮች ናቸው፡፡ ልዩነታቸውም ቢሆን አንደኛው በውጭ ኃይል የሚመራ በመሆኑ ቶሎ ውሳኔ ላይ መድረስ አለመቻሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የግል አስተያየታቸው እንደሆነ በመግለጽም ከዚህ በኋላ ምርጫ ቦርድ እየተብጠለጠለ መቀጠል አለበት ብለው እንደማያስቡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት ተሳዳቢ አካላትን ቦርዱ ወደ ሕግ የሚያቀርብ ይመስለኛል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሰጡት ምላሽ ላይ ሪፖርተር በድጋሚ ያነጋገራቸው አቶ ግርማ፣ የዕለቱ የፓርላማ ውሎ ምርጫ ቦርድንና ፍርድ ቤትን አትናገሩ የሚል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 
‹‹እኛ እየተናገርን ያለነው ተቋማቱን አይደለም፡፡ ተቋማቱን የሚመሩ ግለሰቦችን ነው፡፡ ግለሰቦቹ ማየት የማይችሉና ሸፋፎች ከሆኑ ሸፋፎች እንላለን፡፡ በዚህ የምንጠየቅ ከሆነ ለመቀጣት ዝግጁ ነን፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን የተናገሩት አቶ ግርማ፣ ‹‹የተረዳሁት ነገር ቢኖር አገሪቱን እየመሩ ያሉት በተሰጣቸው መረጃ ላይ ብቻ ተመሥርተው መሆኑን ነው፤›› ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ቦርድንም ሆነ ፍርድ ቤትን ገለልተኛ እንዳልሆኑ የምንገልጸው በተግባር ፈትነን ዓይተናቸው ነው ካሉ በኋላ፣ ‹‹እደግመዋለሁ አሁንም ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለነገሩ አንድነትን ያፈረሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምርጫ ቦርድም አይደሉም፡፡ ኢሕአዴግ አደጋ ሲገጥመው የሚደነግጠው የደኅንነት አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር