የጋራ ምክር ቤቱ በኣገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመወያየትና ችግሮችን ለመፍታት እድል ፈጥሯል-ፓርቲዎች

የጋራ ምክር ቤቱ በታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከገዥው ፓርቲ ጋር በሰከነ መንፈስ ለመወያየትና ችግሮችን ለመፍታት እድል ፈጥሯል-ፓርቲዎች

አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ በታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር በጋራ ለመስራትና በመካከላቸው የሚከሰቱ ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እድል መፍጠሩን አንዳንድ አባል ፓርቲዎች ገለፁ።
በጋራ ምክር ቤቱ ያልተካተቱ ፓርቲዎችም በአገሪቱ የተጀመረው የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ካነጋገራቸው የጋራ ምክር ቤቱ አባል ፓርቲዎች መካከል የአዲስ ትውልድ ፓርቲ (አትፓ) ፕሬዝዳንት አቶ አስፋው ጌታቸው ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚደረገው ውይይት በታላላቅ አገራዊ ጉዳዮች ላይ በፓርቲዎች መካከል መግባባትን ከመፍጠር ባለፈ የመጪውን ትውልድ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ ለማዳበር የጎላ ሚና አለው ብለዋል።
ፓርቲዎች በአንድ አገራዊ ጉዳይ ላይ የሰከነ ውይይት ማድረጋቸው በመካከላቸው የሚከሰቱ አለመግባባቶችን በቀላሉ እልባት ከመስጠቱም ባሻገር ለመደብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓቱ መጠናከር የማይተካ ድርሻ አለው።
በምክር ቤቱ ውስጥም የሁሉም አባል ፖለቲካ ፓርቲዎች አገራዊና ድርጅታዊ አጀንዳዎች እንደሚስተናገዱ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ ጠንካራ ክርክሮችን በማድረግ ለህዝብ የሚቀርቡ አማራጭ ሃሳቦች ጎልተው እንዲወጡ ይደረጋል ብለዋል።
አቶ አስፋው እንዳሉት እስከታችኛው የስልጣን እርከን ድረስ የምክር ቤቱ አባላት ለሚያነሷቸው ችግሮች ከሁሉም ፓርቲዎች የተውጣጡ አጣሪ ኮሚቴዎችን በማዋቀር ዘላቂ እልባት እንዲኖር እድል መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
በጋራ ምክር ቤቱ የተቋቋመው ኮሚቴ በተከሰቱ ችግሮች ዙሪያ የሚያቀርበው ሪፖርት በመነሳት ገዥው ፓርቲ ስህተት ፈጽሞ ከሆነ ሂስ እንዲወስድና በቀጣይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ ይደረጋል።
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ያልተጨበጠ ውንጀላና ክስ እያቀረቡ ከሆነ እንዲስተካከሉ ጠንካራ ሂስ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
"ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ መወያየታቸው በአገሪቱ ብቸኛው አማራጭ ሰላማዊ ትግል ብቻ መሆኑን የሚያስተምር መድረክ ነው" ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፍትህና ዴሞክራሲ ብሄራዊ ግንባር (ኢፍዴብግ) ዋና ፀሐፊ አቶ ግርማዬ ሓደራ ናቸው።
"ችግሮችን ከገዥው ፓርቲ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ በመነጋገር ለመፍታት መጣር የዴሞክራሲ ስርዓት ትልቁ መለኪያ ከመሆኑም ባሻገር ፓርቲዎች ለሰላማዊ ትግሉ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል" ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አቭዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር(ኢህአዴግ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው የጋራ ምክር ቤቱ ፓርቲዎች የያዙትን አጠቃላይ ፕሮግራም በማንፀባረቅ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አማራጭ ሃሳቦችን እንዲያቀርቡ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በአገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ነፃ፣ፍትሃዊና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለዋል።
ተቃዋሚ ፓርቲዎችም  ገዥው ፓርቲ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ አላወያየንም ብሎ በጭፍን ከመተቸት ይልቅ የስነ-ምግባር ደንቡን ፈርመው ወደ ጋራ ምክር ቤቱ በመግባት ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግሉ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርበዋል።
"በጋራ ምክር ቤቱ ውስጥ ገብተው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ለማካሄድ ፍላጎት ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አብሮ ለመስራት ኢህአዴግ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው"ሲሉም አቶ ደስታ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንደተናገሩት ደግሞ ፓርቲዎች በጋራ ምክር ቤቱ መወያየታቸው በመካከላቸው የእኩልነት መንፈስ እንዲፈጠር ከማድረጉ ባለፈ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሻለ መግባባትን እየፈጠረ ይገኛል።
"የጋራ ምክር ቤቱ የውስጥ ዴሞክራሲን በማሳደግ አገራዊና ህዝባዊ አጀንዳዎችን ለማንሽራሸር ትልቅ ሚና አለው" ያሉት አቶ ተሻለ በስነ-ምግባር ደንብ አዋጁ ለፓርቲዎች የተሰጠውን መብት አሟጦ ለመጠቀም በቅንነትና በግልጽ መወያየቱ ትልቅ ፋይዳ አለው ብለዋል።
በምክር ቤቱ አባል ያልሆኑ ሌሎች ፓርቲዎችም ልዩነት በማይፈጥሩ ጉዳዮች ላይ ወደአለመግባባትን ከመሄድ ይልቅ ህግ ሆኖ እያገለገለ ያለውን የስነ-ምግባር ደንብ ፈርመው ወደ ጋራ ምክር ቤቱ እንዲቀላቀሉ ጠይቀዋል።
የጋራ ምክር ቤት አባል ፓርቲዎችም “ምክንያታዊና አሳማኝ በሆኑ ጉዳዮች ያለፍርሃት ያለስጋት በቅንነት ስለእውነት ስንል የዴሞክራሲ  ባህሪያት የሚጠይቁንን ሁሉ እያደረግን እንገኛለን።”ሲሉ ተናግረዋል።
የምርጫ ስነ-ምግባር ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 662/2002 አንቀጽ 20 ንዑስ አንቀጽ አንድ መሰረት በምርጫው ሂደት የሚነሱ የአፈፃፀም፣የዴሞክራሲ፣የሰብዓዊ መብትና የህግ የበላይነትን በኢትዮጵያ ለማጎልበት በተከታታይ እየተገናኙ እንዲወያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት እንዲያቋቁሙ መብት ተሰጥቷቸዋል።
በዚህም መሰረት ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ዘጠኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ አባል ሆነው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
ምንጭ፦ ኢዜኣ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር