ፓርቲዎች በምርጫ ማስፈጸሚያ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ውይይት ጀመሩ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ረቂቅ ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አካሄደ።
ለ5ኛ ጊዜ በመጪው ግንቦት የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አፈጻጸም የጊዜ ሰሌዳ ረቂቅ ላይ ከ23 አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ነው ውይይቱ የተካሄደው።
የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ በቃና እንዳሉት ውይይቱ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቦርዱ ባዘጋጀው ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲንቀሳቀሱ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ከፍተኛ እገዛ ይኖረዋል። 
በምርጫ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ የምክክር መድረክ ላይ ከተገኙት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ረቂቁ ሊያሰራ የሚችል ተስማሚ የጊዜ ሰሌዳ መሆኑን ተናግረዋል።
የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ፕሬዝዳንት አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው ረቂቅ የምርጫ ድርጊት መርሃ ግብሩ መካተት ያለባቸው ጉዳዮች የያዘ በመሆኑ ፓርቲያቸው የተወሰኑ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አስታውቀዋል።
የኢህአዴግ ተወካይ የሆኑት አቶ ደስታ ተስፋው በበኩላቸው "የ2007 ዓ.ም የምርጫ አፈጻጸም የድርጊት መርሃ ግብር ረቂቅ የሚያሰራ እና በተቀመጠው መሰረት ወደ ስራ የሚያስገባ ረቂቅ ሰነድ ነው" ብለዋል።
የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ  አስፋው ጌታቸው  ምርጫ ቦርድ እንደዚህ አይነት የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ ለአገሪቱ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸው የቀረበውን ረቂቅ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል።
 የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር መርጋ ከተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በረቂቁ ላይ በሰጡት አስተያየት የመራጮች ምዝገባ፤ የፓርቲዎች የቅስቀሳ ጊዜ፣ ተወዳዳሪ እጩዎችን ማስመዝገቢያ የጊዜ ሰሌዳ እና ሌሎች አስተያየቶች ቦርዱ ሊያስተካክላቸው እንደሚችልና በሌላ ወቅት የመጨረሻውን የድርጊት መርሃ-ግብር እንደሚያሳውቅ ተናግረዋል።
መጪው ምርጫ ሰላማዊ፤ ነጻ እና ፍትሃዊ እንዲሆን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በህገ መንግስቱና በፓርቲያቸው ህግ መሰረት መንቀሳቀስ እንደሚጠበቅባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በኢትዮጵያ 75 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመዝግበው በመንቀሳቀስ ላይ ሲሆኑ ከነዚህ ውስጥ 23ቱ አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ 52 ደግሞ ክልላዊ ፓርቲዎች ናቸው።
 ምንጭ፡- ኢዜአ

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር