"ልጣድ"እና "ሚስ ፌስ"

ምንጭ፦ ኢዜኣ
ልጣድና ሚስ ፌስ በአንድ መስሪያ ቤት የሚሰሩ ባለደረቦች ናቸው። ሁለቱም የቅጽል ስማቸውን ያገኙ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለከፉበት ሱስ ሳቢያ ነው። በአንድ ተቋም በመምህርነት የሚያገለግሉት ቲቸር ፌስ በተመሳሳይ የሱሱ ሰለባ ናቸው። 
ብዙዎች ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ አንስቶ እሰከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ያሉ ተማሪዎች ፣ነጋዴዎች ፣የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞችና ሌሎችም  በዚህ ሱስ የመለከፋቸው ጉዳይ የአደባባይ ሚስጢር ነው ። 
ከሁሉም ግን የሰማሁት የሚስፌስና ልጣድ የከፋ ሳይሆን አይቀርም። እነዚህን ሁለት ሰዎች ለማግኘት ስል ወደሚሰሩበት መስሪያቤት አመራሁ። 
አንድ የልጣድን የቅርብ ጓደኛ አገኘሁና ስለ ልጣድ የሚያውቀውን እንዲያጫውተኝ ነገርኩት ምን እባክህ በተደጋጋሚ ብንነግረውም አልሰማ አለን ማህበራዊ ህይወቱ እየቀጨጨ መጥቷል። በፊት ከስራ ሰዓት ውጪ ተገናኝተን የምንጨዋወትባቸው ጊዜያት ዛሬ እየናፈቀኝ ነው። 
ልጣድ ጨዋታ አዋቂ በመሆኑ እሱ ባለበት ቦታ ብዙ ሰዎች ተሰባስበው ማየት የተለመደ ነበር ዛሬ ይህ የለም ማለት ይቻላል። ልጣድን ለማግኘት አጋጣሚን መጠበቅ ግድ ይላል።
 አንዳንዴ በአጋጣሚ ስንገናኘው ሁለተኛ ማቆም አለብኝ እስከመቼ እንዲህ እንደምሆን ግራ ይገባኛል ከዛሬ ጀምሮ አልደርስበትም ይላል ግን ተመልሶ ያው ነው።
 ቅጽል ስሙ ከምን ተነስቶ ተሰጠው አልኩት ከዚሁ ከሱሱ ነው በሎ ተመልሶ ይጣድበታል፡፡ በዚህ ሳቢያ ልጣድ ዋና ስሙን ተክቶ መጠሪያው ሆኖ አረፈው። 
በሁኔታው እየተገረምኩ ልጣድ ጋር እንዲወስደኝ ጠየኩትና ይዞኝ ሄደ። ልጣድ ጋር ስንደርስ በትኩረት ስራውን እየሰራ ነው። አይኖቹ ከኮምፒውተሩ ሞኒተር ላይ ተተክለዋል። አንዳንዴ ፈገግ እያለ። ያለማቋረጥ እጆቹን ኪቦርዱ ላይ አድረጎ ጣቶቹን ያራውጣል።
 ላነጋግርህ ፈልጌ ነው አልኩት። ዞር ብሎ ተመልክቶኝ ወደ ኮምፒውተሩ አተኮረና በኋላ አለኝ። ስራ ላይ ስለሆነ ልረብሸው አልፈለግኩምና ትቼው ወደ ሚስ ፌስ አመራሁ። 
ሚስ ፊስ እንደ ልጣድ ሁሉ እሷም በስራ ላይ ትኩረቷን አድርጋለች እንደ ልጣድ ባይሆንም ሙሉ ትኩረት ለስራዋ የሰጠች ትመስላለች ሰላምታ አቅርቤላት ከጎኗ ካለ ወንበር ላይ ተቀመጥኩና ይቅርታ አንዴ ባነጋግርሽ አልኳት ስራዋን አቁማ ምን ነበር አልችኝ። 
እንደው የስምሽ ነገር ይገርማል ሚስ ፌስ ዋና ስምሽ ነው እንዴ አልኳት ፈገግ አለችና ይሄውልህ ከዚህ እኮነው ስሙን የሰጡኝ እኔ ግን እወደዋለሁ አልከፈኝም አለችኝ በጣቷ ወደ ኮምፒውተሩ እያሳየችኝ። 
ነገሩ ገባኝ የልጣድና የሚስፌስ ሱስ ለካ ፌስቡክ ኖሯል።

ዛሬ ዛሬ በሁሉም ተቋማትና ኢንተርኔት ካፌዎች ኮምፒውተሮች ያለ እረፍት በሚባል ሁኔታ በፌስቡክ ተወጥረው ማየት የተለመደ ሆኗል። ከሰኞ እስከ አርብ ያሉት ቀናት አልበቃ ብሎ ቅዳሜና እሁድ ሳይቀር ለፌስ ቡክ ሲባል ቢሮ የሚገቡ ሰራተኞች ቁጥር እየበዛ መጥቷል። 
ከተላላኪ እስከ ኃላፊ ድረስ በፌስ ቡክ ቢዚ ሆነው የሚታዩበት ሁኔታ እየተለመደ መጥቷል፡፡ አንድ ወዳጄ ስለስራ ስጠይቀው የሰጠኝ ምላሽ መቼም አይረሳኝም እንዴት ነው ስራ አልኩት እንደተለመደው ወደ ጨዋታ ለማምራት ይመስገነው በጣም ቆንጆ ነው ስራ በፌስ ቡክ ከሆነ ወዲህ ሁሉም አሪፍ ነው። 
በአንድ ወቅት ለስራ ጉዳይ ከአንድ ተቋም ገብቼ ያጋጠመኝ ከአንድ ክፍል ወደ ሌላ ክፍል መልዕክት ለመለዋወጥ በተላላኪ መሆኑ ቀርቶ በፌስ ቡክ ቻት በማድረግ ሆኖ ተመልክቼ ግርም አልኝ።
 ሌላ አንድ ገጠመኜን ላውጋችሁ አንድ ኃላፊ ዛሬ ለትምህርት ውጪ ሀገር ሄደዋል ፡፡ ቃለመጠይቅ ላድርግላቸው ቀጠሮ ይዤ በቀጠሮዬ ሰዓት ከቢሯቸው ስገባ በተቀመጡበት አንድ እጃቸውን ለሰላምታ ዘርግተው አንድ አጃቸው የኮምፒውተሩን ማውስ ይዞ አትኩረው በሞኒተሩ ላይ ሰላም አሉኝና ቁጭ አልኩ።
 በቀጠሯችን መሰረት ቃለ መጠይቁን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን እንደነገሩኝ መቅረጸ ድምጼንና ማስታወሻዬን አዘጋጅቼ በቅድሚያ ስማቸውንና የስራ ድርሻቸውን እንዲገልጹልኝ ጠየቅኳቸው።
 ራሳቸውን እንዳስተዋወቁ በሩብ አመቱ የተከናወኑ ጉዳዮችን ገልጹልኝ፡፡ ሁለተኛ ጥያቄ አቀረብኩ ኧ....በሩብ አመቱ ኧ....ትኩረታቸው ሁሉ በኮምፒውተር ላይ ነው የሳቸው እንዲህ መሆኑ ትኩረቴን ስለሳበው ቀስ ብዬ ወደ ኮምፒውተሩ ሳይ ፌስ ቡክ ላይ ተጥደውል።
 የተቀመጥኩት ከኮምፒውተሩ ሲስተም ዩኒት አጠገብ ነበርና ቀስ በዬ የኢንተርኔት ኬብሉን ነቀልኩት። ውይ ተቋረጠ አሉ ምኑ አልኳቸው ኢንተርኔት ከዛ በኋላ የሄድኩበትን ጉዳይ ያለምንም መቆራረጥ አጠናቅቄ እንደጨረስኩ አመስግኜ ለመሄድ ተነሳሁ ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው ለሰላምታ እጃቸውን ዘረጉልኝ።
 የዘረጉትን እጅ ጨብጬ ይቅርታ ቅድም ኢንተርኔት ተቋርጦ ሳይሆን ከዚህ ነቅዬው ነው ብዬ የነቀልኩትን ኬብል መልሼ ሰካሁና አመስግናለሁ በማለት እጅ ነስቼ ልሄድ ስል እየሳቁ ሰራህልኝ አይደል ሲሉኝ እኔም ምን ይደረግ ስራ አይደል ብዬ ስወጣ መልካም ስራ አሉኝ እኔም መልካም ፌስ ቡክ ብያቸው ተሰናበትኩ።
 ከዛን ጊዜ ወዲህ ከእኝህ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሰረትን ዛሬ ለትምህርት ወደ ቻይና ከሄዱ አመት አለፏቸው። እባክዎ ወዳጄ ይህን ጽሁፍ ካነበቡ አደራ ከቻይና ሲመለሱ ለፌስ ቡክ የሚሆን አንድ ሰከንድ አንድ ላፕቶፕ ያምጡልኝ።
 እንደው የኔነገር ፌስ ቡክ ውል እያለኝ ነው መሰለኝ የመምህሩን ነገር ዘነጋሁት። መምህሩ ያስተማሩትን አመት ሙሉ የደከሙበትን ምርት ለመሰብሰብ ፈተና አዘጋጅተው ተማሪዎቻቸውን ለመፈተን በቦርሳቸው ፈተናና የማይለያቸውን ላፕቶፕ የዘው ወደ ክፍል ይገባሉ። 
የተማሪዎቹን አቀማመጥ አስተካክለው ፈተናውን አደሉና ትንሽ ጎርደድ ጎርደድ አያሉ ቆይተው መከረኛ ላፕቶፓቸውን አውጥተው ይከፍቱና ሲዲኤማቸውን ሰክተው ፌስቡክ መጎርጎር ይጀምራሉ። 
ቁጭ ብድግ አያሉ ዞር ዞር መልከት አይደረጉ ቆይተው ሙሉ በሙሉ ትኩረታቸው ፌስ ቡክ ላይ ሲያተኩሩ ተፈታኝ ተማሪ ስራውን ሰርቶ ጨረሰና መምህሩን ይጠበበቅ ጀመር። በመጨረሻ ወረቀቱን ሰብስበው ላፕቶፓቸውን ዘጋግተው ከክፍል ወጥተው ይሄዳሉ። 
ከቀናት በኋላ የፈተና ወረቀቱን ይዘው ወደ ተማሪዎቹ ያመሩና እንዴት ሊሆን ቻለ ይላሉ ሁላችሁም እንዴት ልትደፍኑ ቻላች ተናገሩ። ከቆይታ በኋላ አንድ ተማሪ እጁን ያወጣና ቲቸር ሁላችንም የደፈንነው በፌስ ቡክ ነው ብሎ አረዳቸው የፈተና ወረቀቱን ለአለቃው ሰጥተው ወጡ። 
ከዛን ቀን ወዲህ ቲቸር ፌስ  ስማቸው ሆነ። ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስራችንን ቀልጣፋ እያደረገልን የመጣ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በቁጥጥሩ ስር አውሎ ስራችንን እያዘናጋን ከመጣ ሰንበትበት ብሏል።
 ፌስቡክ የማንበብ ባህላችንንም እየሸረሸረ መጥቷል። ሚስ ፌስ ከስራ ላለማርፈድ ዘወትር ብትጥርም የባጃጅ ጉንዳን በሚርመሰመስባት ሀዋሳ የትራንስፖርት ችግር እንዴት ሊያስብል ይችላል። 
ግን ሚስ ፌስ ዘወትር አርፍዳ ገብታ ፌስቡከን ስትከፍት የምትፈልገውን ሰው ኦን ላይና ባለማግኘቷ ምክንያት አይ ሚስ ሂም ስትል በመደመጧ ሚስ ፌስ መባሏን ሰማሁ ልጣድም ለራሱ ያወጣው ስም መሆኑን ተረዳሁ። ይህ ፌስ ቡክ ለኛስ ማን የሚል ስያሜ አሰጥቶን ይሆን?  
ኧረ አንድ ትናንት የሰማሁትን ዜና ረስቼው ኖሯል። ካለን ትንሽ ሀብት ላይ ሸልመንና መርቀን ወደ ደቡብ አፍሪካ የቻን ዋንጫን ይዘው እንዲያመጡ የላክናቸው ዋሊያዎቹ ለውጤት ማጣታችን ምክንያቱ ፌስቡክ ያመጠው ጣጣ ድርሻ ያለው ይመስለኛል፡፡ 
እናም ይህ " ልጣድ" እና "ሚስ ፌስ" የተባለው የፌስቡክ ጉዳይ ይዞን ገደል እንዳይገባ ፈራሁ።  ቸር ይግጠመን።
https://www.blogger.com/blogger.g?blogID=1449985302016269437#editor/target=post;postID=5461017431107284044

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር