ቡናና ወርቅ በወጪ ንግድ ገቢ ከፍተኛ ማሽቆለቆል ማሳየታቸው ቀጥሏል

የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከሦስት ዓመታት በፊት ይፋ ሲደረግ፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በየዓመቱ ያስገኛል ተብሎ የተጠበቀው ገቢ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ ቢሆንም፣ በየዓመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ያስገኛሉ ተብለው ከታሰቡት ውስጥ ወቅርና ቡና ከፍተኛ ማሽቆልቆል በማሳየት ሦስተኛ ዓመታቸውን ይዘዋል፡፡
የንግድ ሚኒስቴር የ2006 በጀት ዓመት አምስት ወራት ኤክስፖርት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያረጋግጠው፣ ካለፈው ዓመት አምስት ወራት ጋር ሲነፃፀር የዘንድሮው የቡና ኤክስፖርት በገቢም ሆነ በተላከው መጠን ዝቅተኛ ሆኗል፡፡ ባለፈው ዓመት በመጀመሪዎቹ አምስት ወራት ከተላከው ከ81 ሺሕ ቶን በላይ ቡና ከ322.3 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ዘንድሮ እስከ ታኅሳስ መጨረሻ የተመዘገበው የቡና የወጪ ንግድ ከ59 ሺሕ ቶን ብዙም ፈቅ ያላለ ከመሆኑም በላይ፣ ከ200 ሚሊዮን ዶላር በታች ገቢ የተገኘበት ሆኗል፡፡ በመሆኑም በመጠን የ27 በመቶ ወይም 22 ሺሕ ቶን ቅናሽ ሲመዘገብ፣ በገቢ ደግሞ የ38 በመቶ ወይም የ122.5 ሚሊዮን ዶላር ቅናሽ ተመዝግቧል፡፡
በግብርና ምርቶች ዘርፍ ዋና ዋና ከሚባሉት ሸቀጦች መካከል ከቡና ኤክስፖርት መቀነስ ባሻገር በኅዳር ወር የነበረውን አፈጻጸም በማስመልከት  ምክንያቶችን ያቀረበው ንግድ ሚኒስቴር፣ ኅዳር ወር የከረመ ቡና የሚሟጠጥበት ወቅት በመሆኑና የዓለም ገበያ የቡና ዋጋ በተከታታይ በመቀነሱ፣ ለቡና ግብይት መዳከም አስተዋጽኦ አድርገዋል ብሏል፡፡
ከቡና ተጨማሪ ካላፈው ዓመት ተመሳሳይ ወራት አኳያ ዝቅተኛ ገቢ ያስገኙት የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ፣ የብዕርና የአገዳ እህሎችና ጥጥ በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡  አበባም ከፍተኛ የገቢና የመጠን ቅናሽ ካስመዘገቡት ውስጥ ተመድቧል፡፡ 
 በማዕድን ዘርፍ የወርቅ ኤክስፖርት አፈጻጸም በተለይ በዋጋ ደረጃ እስከ 30 በመቶ የሚጠጋ ቅናሽ ወይም የ70.5 ሚሊዮን ዶላር ዝቅተኛ ግኝት የተመዘገበበት ሆኖአል፡፡   
በአጠቃላይ በአምስት ወራት ውስጥ የ1.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከኤክስፖርት ዘርፍ የተገኘ ቢሆንም፣ ዓምና በተመሳሳይ ወራት የተገኘው ገቢ ከ1.2 ቢሊዮን ዶላር ይበልጥ እንደነበር ንግድ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል፡፡ 
በበጀት ዓመቱ አምስት ወራት 405,897 ቶን የሚሆኑ የተለያዩ የሰብል ምርቶች፣ እንዲሁም 476,960 የቁም እንስሳት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከ837 ሚሊዮን ዶላር የማያንስ ገቢ እንደሚገኝ ቢታቀድም፣ የተገኘው ግን 633 ሚሊዮን ዶላር ብቻ ነው፡፡ 
በአምስቱ ወራት ከግብርና ባሻገር የታየው አፈጻጸምም የሚጠበቀውን ያህል አልሆነም፡፡ የ87 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሲያገኝ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ 147.5 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘት ግማሽ ዓመቱን ለማጠናቀቅ ተቃርቧል፡፡ መንግሥት ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዘንድሮ ለማግኘት ያቀደው ገቢ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ 
በወጪ ንግድ አፈጻጸምና በገቢ ግኝት ላይ እየታየ ያለው ከዕቅድ በታቸ አፈጻጸም ያሳሰበው መንግሥት፣ ባለሥልጣናቱን በሙሉ ሰብስቦ ግምገማ ሲያካሂድ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ይህም ሆኖ ነገሮች በነበሩበት ቀጥለዋል፡፡ ‹‹የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝቅተኛ አፈጻጸሞችን በማሟላት እናካክሳለን›› የሚሉ መግለጫዎች ከመንግሥት ባለሥልጣናት ሲደመጡ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ እስካሁን በታየው አፈጻጸም ዕቅዱ ከታሰበው በታች እየተጓዘ ይገኛል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር