«የፕሬስ ነፃነት እንዲከበር መግለጫዎችን ማውጣት ብቻ በቂ አይደለም»

ሚስተር አማዱ ማህታር ባ፣ የአፍሪካ ሚዲያ ኢኒሼቲቭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ምንም እንኳን የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ለማንኛውም የኅብረተሰብ ክፍል በተለይ ለማደግ ጥረት በምታደርገው አፍሪካ እጅግ በጣም አስፈላጊ ቢሆንም፣
ይህን ማሳካት የሚቻለው ግን ዋሽንግተን፣ ኒውዮርክ፣ ፓሪስ፣ ዳካር ወይም ሌላ ቦታ ተቀምጦ መግለጫዎችን በማውጣት እንደልሆነ የአፍሪካ ሚዲያ ኢንሼቲቭ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር አማዱ ማህታር ባ ገለጹ፡፡
ሥራ አስፈጻሚው ይህን የገለጹት ዛሬ በአዲስ አበባ የሚከፈተውን ስድስተኛው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረምን አስመልክቶ  አዘጋጆቹ ማክሰኞ በሰጡት የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው፡፡ የአፍሪካ የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሊሳካ የሚችለው ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር በሚደረግ ውይይት መሆን እንዳለበትም አክለው አስረድተዋል፡፡
«በአፍሪካ የሚዲያ መልከ አምድር ላይ በርካታ ወትዋች ድርጅቶች አሉ፡፡ እኛም ለአፍሪካ የፕሬስ ነፃነት ከሚወተውቱ ተቋማት መካከል አንዱ ነን፡፡ ነገር ግን የእኛ መንገድ ከሌሎቹ የተለየ ነው፤» ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት እ.ኤ.አ. በ2013 ይህ ኢንሼቲቭ ሁለት ጋዜጠኞችን ከእስራት እንዳስፈታም አክለው ገልጸዋል፡፡ ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኞች ከብሩንዲና ከማሊ መሆናቸውን፣ የማስፈታቱ ሒደቱም የተከናወነው በቀጥታ ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር በመነጋገር እንደነበርም አውስተዋል፡፡
በተለይ የብሩንዲው ጋዜጠኛ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት የነበረ ቢሆንም፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እስራቱ ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ እንዲልለት በማድረግ ከወራት በፊት መፈታቱን ከመግለጻቸውም በተጨማሪ፣ በዚሁ የአዲስ አበባው ጉባዔ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሚካሄድ ውይይት በይፋ የሚጀመረው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም በመጪው ዓርብ የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ የአፍሪካን ሚዲያ የሚመለከቱ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች ይቀርቡበታል፡፡
በአዲስ አበባው ዝግጅት ላይ ከአሁን ቀደም ከተካሄዱ ጉባዔዎች በላይ በርካታ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩ ተገልጿል፡፡ በሴኔጋል በተካሄደው አምስተኛው ጉባዔ ላይ የተሳታፊዎች ቁጥር 550 የነበረ መሆኑን፣ በአዲስ አበባው ጉባዔ ግን ቁጥሩ ወደ 650 አድጓል በማለት ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
 WRITTEN BY  

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር