የ2015 ዲቪ ሎተሪ ተጀመረ

የ2015 የዲቪ ሎተሪ መርሐ ግብር (ዲቪ 2015) ከመስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለሚቀጥሉት 32 ቀናት ማለትም እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ማመልከት እንደሚቻል፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ መስከረም 20 ቀን 2006 ዓ.ም. አስታወቀ፡፡
በተፈቀደው የማመልከቻ ቀን ውስጥ በድረ ገጽ “dvlottery.state.gov” በመሙላት ማመልከት እንደሚቻል ያስታወቀው ኤምባሲው፣ የወረቀት ማመልከቻዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስታውቋል፡፡
ኤምባሲው እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያ የዲቪ 2015ን ዕድል ለመሳተፍ የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ታሟላለች፡፡ ቀደም ባሉ አምስት ዓመታት ውስጥ ከ50 ሺሕ በላይ ዜጐቻቸውን ወደ አሜሪካ የላኩ አገሮች የዕድሉ ተጠቃሚ እንደማይሆኑና ኢትዮጵያ ግን ያንን ያህል ስላላከች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆኗን አስታውቋል፡፡
አንድ አመልካች ወይም ግለሰብ ማመልከት የሚችለው በሚኖርበት አገር ሳይሆን በተወለደበት ቦታ ወይም አገር መሆኑንም ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዲቪን ሒደትን ቀልጣፋና አስተማማኝ ለማድረግ እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ የኤሌክትሮኒክ ምዝገባን ተግባራዊ ማድረጉንና በሕገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመግባት፣ ለማጭበርበር የሚሞክሩ ወይም ከአንድ በላይ ማመልከቻ የሚያስገቡ ሰዎችን መለየት የሚችሉ ቴክኖሎጂዎችንና ሌሎች ሥልቶችን በሥራ ላይ ማዋሉን ገልጿል፡፡ 
መሥሪያ ቤቱ የዲቪ 2015 ዕድለኞች መመረጣቸውንም ሆነ የቪዛ ማመልከቻና ቃለ መጠይቅ ስለሚያደርግበት ሁኔታ የሚያሳውቀው በኢንተርኔት በመሆኑ፣ አመልካቾች በድረ ገጹ ማወቅ እንደሚችሉ ኤምባሲው አስታውቋል፡፡ 
የተመረጡ አመልካቾች ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው ኢሚግራንት ቪዛ ስለሚጠይቁበት ሒደት የሚገልጽ መመርያ እንደሚደርሳቸውም ኤምባሲው ገልጿል፡፡ ማመልከቻው ሲሞላም ሆነ ሲላክ ምንም ዓይነት ክፍያ እንዳማይፈጸምም ጠቁሟል፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋብቻ አዋጅን በከፊል መሰረዙን ተከትሎ፣ በኢሜግሬሽን አሠራሮች ላይ የተደረጉ ለውጦች በዲቪ 2015 አመልካቾች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ኤምባሲው አስገንዝቧል፡፡ ማመልከቻዎች እስከ ምዝገባው የመጨረሻ ሳምንት ድረስ እንዳይቆዩም መክሯል፡፡
የዲቪ 2015 ውጤት ከሚያዚያ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ በኢንተርኔት እንደሚገለጽና አመልካቾች ውጤታቸውን ለማየት የራሳቸውን መለያ ቁጥር ማስገባት እንደሚኖርባቸው አስታውቋል፡፡ ከኢትዮጵያ በዲቪ 2014 መርሐ ግብር 3,500 ያህል ዜጐች ዕድለኞች መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር