‹‹መንግሥት የሃይማኖት ብዝኃነትን ሲጠብቅ ነፃነትን እንዳይጋፋ መጠንቀቅ አለበት›› ተሰናባቹ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ላለፉት ሦስት ዓመታት በአዲስ አበባ የቆዩት አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ በእስልምና ተከታዮችና በመንግሥት መካከል ስላለው አለመግባባት፣ በዓባይ ወንዝና በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ስላለው ፖለቲካዊ ትኩሳትና ሌሎች ጉዳዮች የመንግሥታቸውን አቋምና የራሳቸውን ግንዛቤ ለሪፖርተር ጋዜጣና ሌሎች ሁለት ሚዲያዎች ባለፈው ሰኞ አካፍለዋል፡፡
አምባሳደሩ የሦስት ዓመታት የአዲስ አበባ ተልኳቸውን አጠናቀው ወደ አገራቸው መመለሳቸውን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆይታ ከተነሱ ጉዳዮች መካከል በእስልምና ተከታዮችና በመንግሥት መካከል የሚስተዋለው አለመግባባትና ግጭት አንዱ ነው፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔሮችና ሃይማኖቶች የሚኖሩባት አገር ነች፡፡ ይህ ስብጥር እንደረጋ እንዲቆይ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የእምነት ነፃነትና እኩልነትን አረጋግጧል፤›› በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት አምባሳደር ቡዝ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ እንዲሁም ሃይማኖቶች በመንግሥት ላይ ጣልቃ እንዳይገቡ በግልጽ በሕገ መንግሥቱ መቀመጡ መሠረታዊ ነው ይላሉ፡፡

ይህ መሆኑ የትኛውም ሃይማኖት ነፃነት እንዲኖረውና ለተከታዮቹም የመረጡትን ሃይማኖት የመከተል መብት ይሰጣል ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ካለው ሁኔታ የምንረዳው ግን አንዳንድ ሰዎች ይህንን የመቀየርና የራሳቸውን እምነት በሌሎች ላይ በግድ የመጫን ፍላጎትና አመለካከት መኖሩን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ሃይማኖታዊ ፅንፈኝነት ወይም አክራሪነት ሊባል ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እየጣረ ያለውም ይህንን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ ነው፡፡ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ ላይ ያለውን የመንግሥትና የሃይማኖት ግንኙነት ፅንሰ ሐሳብ የሚጎዳና በአገሪቱ የቆየውን የሃይማኖት ብዝኃነት የሚያደፈርስ በመሆኑ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

መንግሥት በአገሪቱ የቆየውን የሃይማኖት ብዝኃነት ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ግን ቀላል አለመሆኑንና እጅግ ከባድ ሥራ መሆኑን የሚገልጹት አምባሳደሩ፣ መንግሥት የጀመረው የመከላከል እንቅስቃሴ በሃይማኖት ነፃነት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መንግሥታቸው ሥጋት እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ የአሜሪካ መንግሥት ተቋም የሆነው የዓለም አቀፍ እምነቶች ነፃነት ኮሚሽን ጉዳዩን እየተከታተለ መሆኑን፣ በአዲስ አበባ ኤምባሲ በኩልም መንግሥት በቁጥጥር ሥር አውሎ ለፍርድ ያቀረባቸውን ግለሰቦች የፍርድ ሒደት በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹ዋናው ቁልፍ ነገር አክራሪዎች  በሌሎች ላይ እምነታቸውን ለመጫን የጀመሩትን እንቅስቃሴ ለመቀልበስ መንግሥት የጀመረው መከላከል በሃይማኖቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ መጠንቀቅ ነው፡፡ ምክንያቱም አንድ ሃይማኖት የተለያዩ አስተምህሮዎች ይኖሩታል፡፡ መንግሥት ከእነዚህ አስተምህሮዎች በመምረጥ አንዱን እንዲከተሉ በኃይል እንዳይጭን መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ብዝኃነትን ሲጠብቅ ነፃነትን እንዳይጋፉ መጠንቀቅ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ይህ እንዳይሆንም መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ የአሜሪካ እንዲሁም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጤን አሜሪካ እየሠራች ነው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል አምባሳደሩ የተጠየቁትና ያንፀባረቁት የመንግሥታቸው አቋም የህዳሴውን ግድብ በተመለከተ ስላለው ፖለቲካ ነው፡፡

የዓባይ ወንዝን በተመለከተ ያለው ዋነኛ ጥያቄ ወንዙ መልማት አለበት ወይ የሚለው እንደሆነ የሚገልጹት አምባሳደር ቡዝ፣ ‹‹ወንዙ መልማት አለበት፣ ተገቢም ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ሲሆን ግን ሁሉም የተፋሰሱ አገሮችን የጋራ ተጠቃሚነት መረጋገጥ አለበት፤›› ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የጀመረችው የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለወንዙ ተጋሪ አገሮች የጋራ ጥቅም እንደሚኖረው መንግሥታቸው የሚረዳ መሆኑን አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከኤሌክትሪክ ኃይል ኤክስፖርት፣ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮች ደግሞ ከሚያገኙት የኤሌክትሪክ አቅርቦት የጋራ ጥቅማቸው የሚረጋገጥ ከመሆኑም ባሻገር፣ ግድቡ ውኃውን አመጣጥኖ በመልቀቅ ረገድ አስተዋጽኦ ሊኖረው የሚችል በመሆኑ ሁሉም አገሮች ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ በማለት አስረድተዋል፡፡

‹‹ዋናው ነገር ኢትዮጵያ በግብፅ ላይ ጉዳት እንደምታደርስ ማረጋገጥ ይኖርባታል፡፡ በፕሮጀክቱና ወንዙን በጋራ ለጋራ ጥቅም በማዋል ላይ የተፋሰሱ አገሮች መነጋገርና መግባባት ይኖርባቸዋል፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ከተጠቀሱት ጉዳዮች በተጨማሪ ያነሱት ሌላው ነጥብ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ነው፡፡ በአገሪቱ በተለይ የመናገር ነፃነት መንግሥታቸውን የሚያሰጋና በትኩረት የሚከታተለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመናገርና የፕሬስ ነፃነት ላይ ማነቆ መኖሩን እንደሚገነዘቡ የገለጹት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚሰጠው የተለየ ምክንያት መኖሩን፣ ይህም በመናገር ነፃነት ሽፋን ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳለ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ የተከሰሱ ጋዜጠኞችን ጉዳይ መንግሥታቸው እየተከታተለ መሆኑን የሚናገሩት አምባሳደሩ፣ ሰብዓዊ መብት በኢትዮጵያ በበቂ ሁኔታ መከበር እንዳለበት መንግሥታቸው አቋም እንዳለውና በዚህ ላይም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በተደጋጋሚ እየተወያየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ሌላው የምትሠራበት ነጥብ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምና መረጋጋት መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ እንዲሁም በሱዳንና ደቡብ ሱዳን የተጫወተችውንና እየተጫወተች ያለውን ሚና አድንቀዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር