ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ውግዘትና የመንግሥት ክርክር

በመስፍን መንግሥቱ
ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ መንግሥት በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የገዛ ዜጎቹን መብቶች ያለገደብ የሚጥስና ሰብዓዊ መብት የሚጥስ እየተባለ ያልተከሰሰበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል፡፡
ይሁን እንጂ ይህ መንግሥት በዜጎች ላይ ይፈጽመዋል በሚባለው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዓለም አቀፍ ትኩረትን በሚመለከት የመጀመሪያ ምዕራፍ አይደለም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የዜጎች ጅምላ ግድያዎችን ዓለም በከፍተኛ መገረም ተከታትሎ አውግዟቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማሪያም አገዛዛቸው በኢትዮጵያ የከፍተኛ ጭካኔና የመብት ጥሰት ዘመን ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባተረፈው ታዋቂነት ምክንያት የውግዘት ዒላማ ሆኖ አልፏል፡፡ 
የደርግ መውደቅ በኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የፍፃሜ ምዕራፍ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ከኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለይም ሒዩማን ራይት ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያኔ አዲስ የነበረውን የኢትዮጵያ መንግሥት በሰብዓዊ መብት ጥሰት በማብጠልጠል ነበር የተቀበሉት፡፡ ባለፉት ሃያ ዓመታት ይህ ሥራቸው ሆኖ ዘልቋል፡፡ ጋዜጠኞችን ከመንግሥት ጥቃት በመከላከል ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጀቶችም የኢትዮጵያን መንግሥት በየጊዜው መክሰስ ሥራቸው ሆኗል፡፡
ከእነኝህ ዓለም አቀፍ  ድርጅቶች በተጨማሪ የአሜሪካ  መንግሥት ውጭ ጉዳይ መሥርያ ቤትም በየጊዜው በሚያወጣው ዓመታዊ መግለጫው የኢትዮጵያ መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ መብቶችን ማፈን ሳይከስ ያለፈበት ጊዜ የለም፡፡ አሁን አሁን የእነኚህን አካላት መግለጫዎች የታወቁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ድርጅቶች በመቀባበል ኢትዮጵያ የዜጎቿን መብቶች በመጣስና በማፈን ወደር የሌላት አገር እንደሆነች ዓለም እንዲረዳው እያደረጉ ናቸው፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ለጋዜጠኞች መግላጫ በሰጡበት ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ጥያቄ ያቀረበችው ጋዜጠኛ እንዳብራራችው፣ ኢትዮጵያ በ1960ዎቹ በአስከፊ ድርቅና ረሃብ ለመታወቅ እንደበቃችው ሁሉ በአሁኑ ወቅት መንግሥቷ የዜጎቿን መብቶች በመጣስና በማፈን እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጽመው ወንጀል በዓለም ላይ ታዋቂነትን እያተረፈች ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ተቀናቃኞችን መብቶች ለመጣስ ስለሚጠቀምባቸው ዜደዎች የሚቀርቡ ማብራሪዎች እጅግ ዘግናኝ ናቸው፡፡ የመንግሥታችን መሪዎች የፖለቲካ ተቀናቃኖችን ለማዳከም ሲሉ ንፁኃንን ወንጀለኛ የሚያደርግ (criminalization of Decent) ዜዴዎችን ሥራ ላይ እንደሚያውሉ በተለያዩ ይፋዊ ሪፖርቶች ላይ ሁሉ ሲጠቀስ  ቆይቷል፡፡
የሚገርመው ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የተመሠረተው መንግሥት መሠረታዊ የዓለም አቀፍ የመብት ድንጋጌዎችን ሁሉ እንዳለ ገልብጦ የአገሪቱ ሕጎች አካል ያደረገ ሆኖ እያለ መሆኑ ነው፡፡ እነኝህን ዓለም አቀፍ መሠረታዊ መብቶች ደንጋጌዎችን በአገራችን እንደተደረገው ሁሉ የሕገ መንግሥት አካል የሆነበት ሌላ አገር አለ ማለት አይቻልም፡፡ የሽግግር ዘመኑ ቻርተር ዓለም አቀፍ መሠረታዊ ድንጋጌዎችን እንዳለ የአገሪቱ ሕግ አድርጓቸው ነበር ፡፡ በኋላም የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ከሞላ ጎደል ይህን አድርጎ ፀድቋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የመብቶች ሕጋዊነት ይህ ቀረሽ በማይባል ደረጃ የተደነገጉባት አገር ነች፡፡ እንግዲህ ይህ ሆኖ እያለ ነው በአገሪቱ የመብቶች ጥሰት ጉዳይ ከአገሪቱ ብሔራዊ አነታራኪ ፖለቲካዊ አጀንዳነት አልፎ ዓለም አቀፍ አጀንዳ  ሆኖ የሚገኘው፡፡
የኢሕአዴግ መንግሥትና ደጋፊዎቹ በአገሪቱ ስለመብቶች ሕጋዊነትና የተፈጠሩ ሁኔታዎችን ሁሉ በመዘርዘር ኢትዮጵያ መብቶች የተረጋገጡባት አገር ስለመሆኗ እያብራሩ የመብት ተሟጋች ድርጀቶችን ክሶችን ሲያጣጥሉ ቆይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በየጊዜው ለእነኚህ አካላት መግለጫዎች በሚሰጠው ምላሽ ይህን ከማብራራት አልፎ የአሜሪካ መንግሥት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሥርያ ቤትን ጨምሮ የእነኘህን መብት ተሟጋች አካላትን ሀቀኝነትና ለዓላማቸው ያላቸውን ታማኝነት ጭምር ጥያቄ ላይ ለመጣል ሲሞክር ቆይቷል፡፡ ይህ በሚገርም ሁኔታ እነኝህ አካላት ይህንን የሚያደርጉት በርዕዮተ ዓለም ልዩነት የተነሳና አንዳንዶቹም ኢትዮጵያ በቅርቡ የጀመረችውን የዕድገት ግስጋሴ እንዲመቀኙ ስላደረጋቸው ነው እስከማለት ተደርሷል፡፡ በዚህ በኩል በተለይም በአዲስ ዘመንና በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጦች ላይ በየጊዜው እየተጻፉ ሲወጡ የቆዩት ምላሾች የሚያሳዩት መንግሥት እነኝህ አካላት በየጊዜው በሚያወጡት መግለጫ ምን ያህል ይበሳጭ እንደነበር ነው፡፡ ጉዳዩ በራሱ በመንግሥትና ውሎ አድሮም በአገር ገጽታ ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተጽዕኖ በመገንዘብ በችግሩ ላይ ተጨባጭ መፍትሔ ለመስጠት አስቀደሞ ሞክሮ አለማወቁን ያረጋግጣሉ፡፡ አንዳንድ የመንግሥት መከራከሪያዎች ተመልሰው በመንግሥት ላይ የሚቀርበውን ክስ ይበልጥ የሚያጠናክሩ ናቸው፡፡ 
ይህ አጭር ጹሑፍ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለውን የንትርክ ምንጭና በዚህ ጉዳይ የመንግሥታችንን ክርክር ለመገዳደር ታስቦ የተጻፈ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በእርግጥ መንግሥታችንን በሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲህ የሚያብጠለጥሉት በርዕዮተ ዓለም ልዩነት የተነሳ ነው? የእኛ ዕድገትና ልማት  እንዲመቀኙ አድርጓቸዋልን? ለእነኝህ ጥያቄዎች ምላሽ ለማበጀት መነሻ ሊሆንልን የሚገባው ኢትዮጵያ የዜጎች ሁለንተናዊ መብቶች የማይጣሱባት አገር ነች ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አይፈጸምም?
የዚህ ጥያቄ ምላሽ የኢትዮጵያ መንግሥትንና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን የሚያወዛግባቸው አይደለም፡፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማሪያም ለጋዘጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት ሲናገሩ፣ የትኛውም አገር የሰብዓዊ መብት ጥሰት አልፈጽምም ብሎ ለመከራከር እንደማይችል አመልክተው፣ በኢትዮጵያም ከአገሪቱ ታሪክና ባህል ነባራዊ ሁኔታዎች የሚመነጩና ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት የሆኑ ችግሮች እንዳሉ አብራርተዋል፡፡ ይህ የጉዳዩን ማዕካለዊ ነጥብ ግልጽ ያደርግልናል፡፡ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር መኖሩን የኢትዮጵያ መንግሥት ያምናል ማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዚህ ምንጭ አቶ ኃይለ ማሪያም እንዳሉት ከአገሪቱ ታሪክና ባህል ነባራዊ ሁኔታዎች የሚመነጩ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆኑ ችግሮች በመኖራቸው ነው? ወይስ ከሥርዓት ባህርይና ከአገዛዝ ጨቋኝነት? የሚለውን ጥያቄ  በግልጽ አንስተን መወያየት በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ከመንግሥት ጨቋኝነትና መብት አፈና ባህርይ ውጭ የሚከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በየጊዜው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በሚያወጡት መግለጫ መጠን ትኩረታቸውን የማይስቡ ስለመሆናቸው መከራከር ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በዚህ መጠን በአንድ አገር ላይ ትኩረት የሚያደርጉት፣ በአገሩ ከመንግሥት ጨቋኝነትና አምባገነንነት የተነሳ መብትን ለማፈንና ነፃነትን ለመገደብ በሚደረግ ክፋትና ጭካኔ መነሻነት  የሚፈጸም የሰብዓዊ መብት ጥሰት አለ ብለው ሲያምኑ እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
ከዚህ አንፃር ስንመለከት እነኝህ ወገኖች በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የሚያቀርቡት ክስ መሠረት የለውም ወይ የሚለውን ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ መንግሥት ተደነገጉ መብቶችን መንግሥት እንደማያከብር የታወቀና የተረጋገጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ  ብቻ ሳይሆን መንግሥት ይህን ማደረጉን ለመከልከልም ሆነ ይህን በማደረጉ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተማማኝ ሥርዓታዊ ሁኔታ አለመፈጠሩ ከቶውንም የሚያከራክር አይደለም፡፡ በአገሪቱ የሕግ በላይነት ጉዳይ ሥር የሰደደ ችግር ነው፡፡ በየተዋረድ ያሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሰብዓዊ መብቶች መጣሳቸውን በማረጋገጥ በሕግ ከሶ ማስቀጣት ከባድ ነው፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ ደካማነትና የፍርድ ቤቶች ገለልተኛ አለመሆን ፍርድ ቤቶች የዜጎች መብቶችንና የአገሪቱን ሥርዓት ዲሞከራሲያዊነት ጠባቂዎች መሆን እንዳልቻሉ  በግልጽ ሲያሳዩ ቆይተዋል፡፡ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች በታሰሩ ቁጥር በእስር ቤት በሕገ  መንግሥቱ በግልጽ የተደነገጉ መብቶችን በማሳጣት ጭምር ስለሚፈጽምባቸው በደሎች መገናኛ ብዙኃን በይፋ ሲዘግቡ ቆይተዋል፡፡ እነኘህ በግልጽ ተደጋግመው በሚስተጋቡበት ሁኔታ መንግሥት ያቋቋመው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊዎች ወደ እስር ቤቶች ብቅ ይሉና የእስር ቤቶች አያያዝ ችግር የሌለበት መሆኑን አረጋገጥናል የሚል መግለጫ ይሰጣሉ፡፡ ይህ በሀቀኝነት የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ለመቆጣጠር ሳይሆን በጥሰቶቹ ዙሪያ የሚስተጋቡ ክሶችን ለማስተባበል የሚደረግ ድርጅታዊ ሥራ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ መንግሥታችን ለመሆኑ ይህንን ኮሚሽን ያቋቋመው ለምንድነው ብለን እንድንጠይቅ ሲያደርገን ቆይቷል፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባለፉት ዓመታት በሕግ የተደነገገው መብታቸው አለመከበሩን፣ በአባሎቻቸው ላይ ከሕግ ውጭ አሰቃቂ የመብት ጥሰቶች እንደሚፈጸሙ መንግሥትን ሲከሱ መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ያለፉት ሃያ ዓመታት ይቅሩና ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሰላማዊ ሠልፎችን ለማካሄድ በሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች አጋጠመን የሚሉት ሁሉ፣ ሀቀኛና ቅን ዜጎችን በእርግጥ ይህቺ አገር በሕገ መንግሥት ሥር ናት ብለው እንዲጠይቁ  እያደረገ ነው፡፡
በየደረጃው ያሉ የሕግ አውጪ አካላት ሌላው ቀርቶ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ በግልጽ መገናኛ ብዙኃን በሚዘግቧቸው ክሶች ዙሪያ እንኳን ለአስፈጻሚዎች ጥያቄዎችን በማቅረብና እንዲጣሩ ለማረጋገጥ ሲሞክሩ ተሰምተውም ሆነ ታይተው አያውቁም፡፡ በቅርቡ በመንግሥትና በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል በተፈጠረው ግጭት ዙሪያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሰዎች አላግባብ መታሰርና የመብቶች ጥሰት በመገናኛ ብዙኃን በየጊዜው ሲዘገብ፣ የሕዘብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህ ተጣራቶ እንዲቀርብ ለማድረግ አንድም ጊዜ አልሞከረም፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች በግልጽ መከሰታቸው ቀርቶ ገና ፍንጭ ሲገኝ እንዲጣሩ በማድረግ እውነታውን ማውጣት፣ ጥፋተኞችን ለሕግ ማቅረብና የአስፈጻሚውን ተጠያቂነት ማረጋገጥ፣ በየትኛውም የዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኝ ዲሞክራሲያዊ አገር የሕግ አውጪው መደበኛ ተግባር ነው፡፡ 
መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶች አዋጅ፣ የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የፀረ ሽብር አዋጁ በሕገ መንግሥት ለዜጎች የተሰጡ መብቶችን የሚያጣበቡ እንደሆኑ በብዙ መልኩ ሲተነተን ቆይቷል፡፡ ምንም እንኳን እነኝህን አዋጆች ማውጣት የሚያስገድዱ ተቀባይነት ያላቸው ምክንያቶች መኖራቸው የታወቀ ቢሆንም፣ ኢሕአዴግ እነዚህን ሁኔታዎች መጠቀሚያና ማመካኛ በማድረግ ከምርጫ 97 በኋላ በአገሪቱ እያየለ የመጣውን ለመንግሥት ጭቆና የማይበገር የሕዝብ መነቃቃት መንፈስን በማምከን፣ ሥልጣኑን ያላግባብ ለማጠናከር እየተጠቀመባቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በርካታ የታወቁ ጉዳዮችን በማንሳት በአገራችን የመብት ጥሰቶች ከሥርዓቱ ፀረ ዲሞከራሲያዊነትና ከመንግሥት ጨቋኝነት ባህርይ እንደሚመነጩ በብዙ በዝርዝር ማስረጃዎች ማስረገጥ ይቻላል፡፡ በመሆኑም ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በመንግሥታችን ላይ በየጊዜው የሚያቀርበት ክስ ከተገቢ መነሻዎች የሚነሱ መሆናቸው የሚያጠራጥርም ሆነ የሚያከራክር አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ክርክር ደካማነት
የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አካላት በአገሪቱ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ከሚገባው በላይ በማጋነን አገሪቱን ለማጥቃት የሚደርጉት ከርዕዮተ ዓለም ልዩነት በሚመነጭ ምክንያት ነው የሚለው ክርክር የመጀመሪያው ነው፡፡ ለመሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ኢትዮጵያን እንደ አገር የማጥቃት ዓላማ አላቸውን? ይህን እንዴት ማመን ይቻላል? ይልቁንስ በኢትዮጵያ በመንግሥት አካላት የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚገባቸውን ያህል ዓለም አቀፍ ትኩረት አግኝተው ያውቃሉ የሚለውን አንስቶ መወያየት ነው የበለጠ ተገቢ የሚሆነው፡፡ ምዕራባዊያን መንግሥታት ለኢትዮጵያ ባላቸው ጥሩ አመለካከት የተነሳ የመንግሥቷን ጥፋቶች በመሸፋፈን ሲያግዙ እያየን ነው ያለነው፡፡
 ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም ለምዕራባዊያን ተግዳሮት ለመሆን ይቻለዋል ወይ? ያም ሆኖ በአሁኑ ጊዜ የርዕዮተ ዓለም ልዩነቶች ሳይሆኑ የኢኮኖሚ ጥቅሞች የሚቀድሙበት ዓለም ውስጥ ነው የምንኖረው፡፡ የአገሮች ግንኙነት በርዕዮተ ዓለም ልዩነት ሳይሆን  በኢኮኖሚ ጥቅም ቀዳማይነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነቶቹ አገሮች የሚፈጥሩት ርዕዮተ ዓለም ምዕራባዊያንን የሚያሳስባቸው ተግዳሮት ይሆናል ተብሎም አይታሰብም፡፡ በዓለም ላይ የሊበራል ዲሞክራሲ እሴቶች በሕዝቦች አስተሳሰብ ውስጥ ያገኙት የተቀባይነት ደረጃ፣ የዓለም ሕዝቦች በምዕራባዊያን የዲሞክራሲ መንገድ ለመተዳደር ያላቸውን የማያወላዳ ፍላጎት እያረጋገጠ መጥቷል፡፡ ለዚህ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ተጨባጭ ማስረጃ ነው፡፡ ካፒታሊዝም በራሱ ፈተናዎች ውስጥ እያለፈ ቢሆንም ለሰዎች መብት በሚሰጠው ቦታና በነፃነት አስተሳሰቡ ተደማጭነት የተነሳ እሱን ለመተካት ተግደርድሮ የተሳካለት ሌላ ርዕዮተ ዓለም አልተገኘም፡፡ አሁን በዓለም ላይ በአንዳንድ አገሮች እየታየ ያለው አንዳንድ ገዥ ፓርቲዎች በመርህ ደረጃ ዲሞክራሲን ተቀብለው ሲያበቁ፣ የዲሞክራሲን ውጤቶች በመፍራት የራሳቸውን የበላይነት ብቻ የሚያረጋገጥ የአገዛዝ ሞዴል በመፍጠር፣ ይህንንም በሌላ የርዕዮተ ዓለም አማራጭ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ አድርገው ለማቅረብ ሲሞክሩ ነው፡፡ ይህ የምዕራብ ዲሞክራሲ ለእኛ ተጨባጭ ሁኔታ ተስማሚ አይደለም ከሚል መነሻ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ክርክር የፈጠራቸው እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ዓይነቶች የኢ-ሊበራል አስተሳሰቦች፣ ለሊበራል ዲሞክራሲ ተገዳዳሪ አማራጭ ሊሆኑ ይቅርና በተጨባጭ ምን ማለት እንደሆኑ ራሳቸውንም  በአግባቡ አብራርተውም አያውቁም፡፡
ምዕራባዊያን ኢሕአዴግ እንደሚለው በርዕዮተ ዓለም ልዩነት የተነሳ ኢትዮጵያንና መንግሥትን ለመጫን የሚፈልጉ ቢሆኑ ኖሮ ኢትዮጵያም ሆነ መንግሥቷ ይኼን መቋቋም የሚቻላቸው አይሆንም ነበር፡፡ ይልቁንም በተጨባጭ እያየን ያለነው ምዕራባዊያን ለኢትዮጵያ ልማትና ለመንግሥቷም ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሥልጣን ፖለቲካዊ አጋሮች ሲሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ወይም ከስድሳ  ቢሊዮን ብር በላይ ከምዕራባዊያን በዕርዳታ የምታገኝ አገር ናት፡፡ ይህ ደግሞ ማደጓ እንዲመቀኙ እያደረጋቸው ነው የሚለውንም የመንግሥታችንን ክስ ጨርሶውን እንድንቀበለው አያደርገንም፡፡ እንዲያውም መልማታችንና ማደጋችን ያስደስታቸዋል ብለን እንድናስብ የሚያደርጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ፡፡ በተራብን ቁጥር እንዲመግቡን በልመና ከምናጣድፋቸው፣ ራሳችንን ችለን ብናሳያቸው ከችግር ተላቀቅን ብቻ ሳይሆን የእነሱንም ሸክም አቃለልን ማለት ነው፡፡
ለመሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጀቶች በኢትዮጵያ ላይ በየጊዜው በሚያወጡት መግለጫ መጠን በቻይና ላይ አውጥተው ያውቃሉን? ይህን የማያደርጉት ቻይና የሊበራል ዲሞከራሲ ተከታይ ስለሆነች ነውን? የአሜሪካ መንግሥትን በሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሰው አያውቁምን?  የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ለአንድ የጤና ጉዳይ ስብሰባ አዲስ አበባ መጥተው በነበሩ ጊዜ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ይዞ እንዲያስራቸው የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጀቶች ሲወተወቱ ነበር፡፡ መነሻው ቻይና ሊበራል ዲሞክራሲን ስለምትከተልና አሜሪካ ልማታዊ መንግሥት ስለሆነች ወይም ጆርጅ ቡሽ አብዮታዊ ዲሞክራት ስለሆኑ አይደለም፡፡ ጉዳዩን ከርዕዮተ ዓለምጋር የሚያይዘው ምንም ነገር የለም፡፡
በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ተከባሪነትን ለማረጋገጥ ኢሕአዴግና መንግሥቱ ምን ማድረግ አለባቸው?  በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሠረታዊ የሆነ የፖለቲካዊ ቅራኔ ውጤት ነው፡፡ በዚህ አገር ዲሞክራሲ ከታወጀ ሃያ ዓመታት ያለፈው ቢሆንም የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ዋነኛ ግልጋሎት የሆነው የፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተሳለጠ ውድድርና የሊህቃን ትብብርና አንድነት ሥርዓት ሊሰፍን አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን ብቸኛ የሕዝብ ተወካይ ብቻ ሳይሆን ሕዝብም ጭምር በማድረግ ተፎካካሪ የሥልጣን ሊህቃንን ሁሉ አግልሏል፡፡ የመሠረተው ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት  ከላይ ከተቀባው አርተፊሻል ቀለም ሥር በቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ ዘመን መንግሥትም ሆነ በደርግ ጊዜ ከነበረው የተለየ ባህርይ የለውም፡፡ የሕገ መንግሥቱ  ዲሞክራሲያዊነት በአገዛዝ አስተሳሰብ ላይ ተፅዕኖ ያለው ለመሆን አልበቃም፡፡ ይህ ደግሞ ለሥልጣን የሚፎካከሩትን ሁሉ መንግሥቱን አምረው እንዲታገሉ የሚያደርግ ምክንያቶችን ፈጥሮ ይገኛል፡፡ ኢሕአዴግና መንግሥቱ ይህን ምክንያት ሳይሆን በዚህ ምክንያዊነት ዙሪያ የተሠለፉትን በማሸነፍ፣ ከቶውንም በዚህ አገር መሠረትን የሚሉትን ሥርዓት ዘላቂ ሊያደርጉ እንደማይቻላቸው ማወቅ ይገባቸዋል፡፡
የመንግሥት ሥልጣን ከሀቀኛ የሕዝብ ፍለጎት ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች በተለይም የፖለቲካ መሀይምነትንና ጥቅም ፈላጊነትን በመረዳት፣ ብዙዎችን ለአገዛዝ ምቹ እንደሆኑ አድርጎ የመፈብረክ የማያባራ ንቅናቄ ላይ እንዲተማመን ማድረግ የመጀመሪያው አደጋ ለራሱ ለሥርዓቱ ነው፡፡ ቀስ በቀስ መንግሥት ከፅኑ ሐሳብና ምክንያታዊነት እየራቀ እንዲሄድ በማድረግ፣ በመጨረሻ የሌሎችን ምክንያትና አስተሳብ ጨርሶ ወደማይቀበልበት፣ በጉልበትና በኃይል ብቻ  ወደሚተማመንበት ጫፍ ያደርሰዋል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ የመብት ጥሰቶች የፖለቲካዊ ሥርዓቱ ደካማነት ቋሚ ማሳያ የዕለት ተዕለት ክስተቶች ይሆናሉ፡፡
ኢሕአዴግ ሥርዓቱን ዲሞክራሲያዊ ባለማድረጉ ምክንያት የሚመነጨውን ተግዳሮት ሁሉ በመንግሥትነቱ ጡንቻ አምበርክኮ ለመግዛት እስከወሰነ ድረስ፣ ለፖለቲካ መብት እንታገላለን የሚሉና  በሕግ የተሰጣቸውን ነፃነት እንጠቀማለን የሚሉ ሁሉ  ‹‹ሸብርተኛ›› መሆናቸው አይቀርም፡፡ ሥርዓቱ በራሱ ላይ የደኅንነት ሥጋት በሚፈጥር አካሄድ ይጠመድና ይህንን ሥጋት ለማስወገድ ሲል ሁሉንም ሽብርተኛ በሚያደርግ አካሄድ ለመጠመድ ይገደዳል፡፡ በዚህ ሒደት የሥርዓቱ ዋስትና በሕግ የበላይነትና በሕገ መንግሥታዊነት ላይ የተመሠረተ  ስርፀት ሳይሆን፣ የፖሊስ ጉልበትና የሥርዓቱ ተከላካዮች ቁርጠኝነት ላይ ይመሠረታል፡፡ የእነዚህ አካላትም በሕግ ያልተገደበ እንቅስቃሴ አስፈላጊ ይሆናል፡፡ የሥርዓቱ ዋነኛ አንቀሳቃሾች ነን የሚሉም ራሳቸው በደኅንነት ሥጋት ውስጥ ይወድቁና የራሳቸውን ዋስትና ለማረጋገጥ የሥርዓቱ ተግዳሮቶች ናቸው የሚሉትን ሁሉ በጠላትነት በመፈረጅ ደፍቀው ጭር በማሰኘት ሰላም ማግኘትን ይመኛሉ፡፡ ይህ በሌሎች ወገኖች መብቶች ሁሉ ጠንቅ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ በሥራቸው ሁሉ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች የማሰብ ግዴታ ለእነሱ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም የእነሱ ደኅንነትና ጥቅም የሚረጋገጠው በሕገ መንግሥቱ ተከባሪነት ሳይሆን ከሥርዓቱ ጨቋንነት ነውና፡፡
ብዘዎቹ የኢሕአዴግ ታማኝ ካድሬዎች ተቃዋሚዎችን እጅግ ይፈሯቸዋል፡፡ ተቃዋሚነትን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መሣሪያ ሳይሆን ጠላት አድርገው ነው የሚያዩት፡፡ ይህም ኢሕአዴጋዊነት ያረጋገጠላቸውን ጥቅም ጠብቀው ለመቆየት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው፡፡ በተለይም ይህ በታችኞቹ መዋቅሮች ሥር የሰደደ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በአካባቢያቸው አሉ ከተባሉ ምክንያት ፈጥረው ካልበተኑ ወይም ወንጀለኛ አድርገው መብትና ነፃነት አሳጥተው አሳደው ካለስወገዱ በቀር ዕረፍት አይሰማቸውም፡፡ አልፎ አልፎ ለምነው ተቃዋሚነትን ማስተውም አለ፡፡ ሥርዓቱ በሕዝብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ ባለመሆኑ ሕዝብ የጎንዮሽ ተጠያቂነትን (Horizontal Accountablity) በማረጋገጥ በሹማምንቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር አይችልም፡፡ ያጠፋ ሹምምነት ጥፋተኝነቱ የሚረጋገጠው መጀመሪያ በድርጀቱ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ይህ እስኪሆን ድረስ ጥፋቱን አንስቶ የሚሟገትን ሁሉ ድርጀቱ በራሱ ላይ የተቃጣ ጥቃት አድርጎ ስለሚከላከል በማንኛውም መንገድ መሞከር ከድርጀቱና ከሥርዓቱ ጋር መታገል ይሆናል፡፡ የፌዴራል አወቃቀሩ በዲሞክራሲያዊነት ባለመታገዙ የሕግ በላይነት አለመኖር ወደታች የወረደውን ሥልጣን የታቸኞቹ ሹማምንት ሕዝብን እንደፈለጉ መጨቆኛ እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ 
ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ መብቶች ተከባሪነትን ለማረጋገጥ ሁለት ነገሮችን ማድረግ አለበት፡፡ የመጀመሪያውና በጣም አስፈላጊው የሥርዓቱን ባህርይ መቀየር ነው፡፡ ይህም በአንድ ፓርቲ የበላይነት ላይ የተመሠረተውን ፖለቲካ ወደብዙ ፓርቲዎች ትብብርና ኅብረት ሥርዓታዊነት (መድበለ ፓርቲ ዲሞክራሲ) መለወጥ ነው፡፡ ተቃዋሚነትን በማዳፈን ሳይሆን እያሳለጠ በመግራት የሥርዓቱ ተግዳሮት ሳይሆኑ ዕድል እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ የመጀመሪያው አስፈላጊ ነገር በኢሕአዴግ ውስጥ ቅራኔዎችን ለማዳፈን ከመሞከር ወደ ማስተዳደር (Regulatory) ሥርዓታዊነት አስተሳብ መምጣት አለበት፡፡ ሁለተኛው ማንኛውም ዓይነት በመንግሥት አካላት የሚፈጸም ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ጥሰት ላይ  በሙስና ላይ የሚደረገውን ዓይነት ዘመቻ መክፈትና ተቋማዊ አሠራርና ሥርዓታዊ አስተሳሰብን ማጠናከር ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ አውጫጭን ዓይነት የማያባራ የስብሰባ ጋጋታ ሳይሆን፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ተቋማዊ አሠራርንና ሥርዓታዊነትን ማጠናከር ያስፈልጋልና፡፡ 
ከአዘጋጁ፡ ጸሐፊው የኢዴፓ አመራር አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩ ሲሆን፣ በቅርቡ ከኢዴፓ ራሳቸውን አሰናብተዋል፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸውmsfinmengistu2@gmail.com  ማግኘት ይቻላል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር