የሀዋሳ ከተማን የቄራ አገልገሎት የማሻሻል ፕሮጀክት በመጠናቀቅ ላይ ነው

አዋሳ ሐምሌ 19/2005 የሀዋሳ ከተማን የቄራ አገልግሎት ለማሻሻል ከ25 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ የሚካሄደው ፕሮጀክት ግንባታ የመጀመሪያው ምዕራፍ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ፡፡ በማዘጋጃ ቤቱ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ መብራቴ መለሰ ትናንት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በአለም ባንክ ፣ በክልሉ መንግስትና በከተማው አስተዳደር ወጪ የሚካሄደው የቄራ አገልግሎት ግንባታ የተጀመረው በ2003 መጨረሻ ላይ ነው፡፡ በእቅዱ መሰረት የግንባታው የመጀመሪያው ምዕራፍ 90 በመቶ መጠናቀቁን አመልክተው ቀሪውና ቀጠዩ የውስጥ ድርጅት የማሟላት ስራ በሂደት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ለስጋ ፍጆታ የሚውሉ በግና ፍየልን ጨምሮ በቀን ከ400 በላይ የእርድ እንስሳትን የማሰተናገድ አቅም ያለው አዲሱ የቄራ ፕሮጀክት ለሁለቱም ሀይማኖቶች የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የቀድሞው ቄራ ከበሬ በስተቀር የፍየልና የበግ እርድ ያልነበረው ፣ ከከተማው ፈጣን ዕደገትና ከተጠቃሚው አንጻር የማስተናገድ አቅም በቂ ባለመሆኑ ይህንን ለማሻሻል አዲስ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል፡፡ በህብረተሰቡ ጥያቄ መሰረት መንግስት በሰጠው ትኩረት የሚካሄደው ፕሮጀክቱ ከነባሩ የተሻለና የጥራት ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎቱን ለማቀላጠፍና ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም የከተማውን ዕደገትና የተጠቃሚውን ፍላጎት የሚያሟላ ነው ብለዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ግንባታ ቀሪ ስራ የህንጻና ኤሌክቶሮ ሜካኒካል ስራን አካቶ በመጪው መስከረም 2006 መሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልገሎት ሲበቃ ጥራትና ቅልጥፍናን ያሻሽላል፡፡ ህገወጥ እርድን በመቆጣጠር ከጤና ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ለማስቀረት የሚያስችል ፕሮጀክት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የቀድሞው ቄራ እንዳለ ሆኖ አዲሱ ፕሮጀክት ራሱን ችሎ የሚያገለገል መሆኑም ተገልጿል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር