የሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ችግር ፈቺ ከ200 በላይ የምርምር ፕሮጀክቶች እያካሄደ ነው

ሃዋሳ ነሐሴ 17/2005 የሃዋሳ ዩኒቨርሰስቲ ችግር ፈቺ የሆኑ ከ200 የሚበልጡ የምርምር ፕሮጀክቶች በራሱና በውጪ ሀገራት ትብብር እያካሄደ መሆኑን ገለጠ። በዩኒቨርሰቲ የምርምር ፕሮግራም አስተባባሪ ዶክተር አለማየሁ ረጋሳ ሰሞኑን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጡት የምርምር ስራዎቻቸውን በየአመቱ በማስፋፋት በአሁኑ ውቅት 180 ፕሮጀክቶች በራሳቸው አቅምና ከ40 በላይ ደግሞ በውጪ ሀገራት ትብብር እየተካሄደ ነው። ከምርምር ፕሮጀክቶቹ መካከል ትምህርት ፣ግብርና፣ተፈጥሮ ሀብትና እፅዋት ሳይንስ፣እንስሳት ጤና፣አግሮኖሚ፣ ኑውትሪሽንና ሌሎች ማህበራዊና የኢኮኖሚ ተጠቃሜታ ያላቸው እንደሚገኙበት አስታውቀዋል። በክልሉ ወረዳዎች በተመረጡ ስድስት የቴክኖሎጂ መንደሮች የሚያካሄዳቸው ምርምር ስራዎች ከስድስት ወራት እሰከ ሶስት አመታት እንደሚቆዩ ገልጸዋል። የምርምር ስራዎቹ ችግር ፈቺና ህብረተሰብ አሳታፊ መሆናቸውን አመልክተው ህብረተሰቡን ከመጥቀም ባሻገር የመምህራንን የብቃት አቅም ያሳድጋል፣የትምህርት ጥራትን በመጠበቅ የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጠዋል። ከዚህ በፊት የሚካሄዱ የምርምር ውጤቶች ሼልፍ ላይ ይቀሩ እንደነበር በማስታወስ አሁን ለህብረተሰቡ ቅርበት ባላቸው የቴክኖሎጂ መንደሮች በመሞከር በማላመድና ወደ ምርት ስራ በማሸጋገር እንዴት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ በሰፊው እየተሰራ ነው ብለዋል። ለምርምር ስራው በዩኒቨርሰቲ በኩል 5 ሚሊዮን ብር መመደቡን አመልክተው በእያንዳንዱ የምርምር ፕሮጀክቶች ከአንድ እስከ አራት ተመራማሪዎች እንደሚሳተፉ ዶክተር አለማየሁ ተናግረዋል። ከውጪ ሀገራት ኖርዌይ፣ ካናዳ፣ አሜሪካና የሌሎች ሀገራት ዩኒቨርሰቲዎች የምርምር ስራውን በትብብር ለማካሄድ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጠዋል። መንግሰት የጀመረውን የልማት እንቅስቃሴ በጥናትና ምርምር ውጤቶች ለመደገፍ በተለይ የአካባቢ ህብረተሰብ የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂ በማፍለቅ ባለፈው አመት በርካታ የምርምር ስራ ማከናወናቸው ተመልክቷል።
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=11170&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር