ዩኒቨርስቲው ሶስት አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች በድህር ምረቃ ደረጃ ሊከፍት ነው

ሃዋሳ ግንቦት 03/2005 የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በ2006 የትምህርት ዘመን በድህረ ምረቃ ደረጃ አዳዲስ ፕሮግራሞችን ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ዩኒቨርሰቲው የቅበላ አቅሙን ለማሳደግም 2 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ በጀት የማስፋፊያ ግንባታ በማካሄድ ላይ ነው፡፡ ዩኒቨርስቲው የሚከፍታቸው አዳዲስ ኘሮግራሞች በጋዜጠኝነትና ማስ ኮሚኒኬሽን፣ በሶሻል ሳይኮሎጂ እንዲሁም በጎልማሶች ትምህርትና የህብረተሰብ ልማት ዘርፎች ነው፡፡ ለሶስቱ አዳዲስ የትምህርት ፕሮግራሞች የተቀረጹትን ስርዓተ ትምህርቶችን ለማዳበር ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በተዘጋጀው መድረክ ላይ በዩኒቨርስቲው የሶሻል ሳይንስና ሂውማኒቲስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ንጉሴ መሸሻ እንዳስታወቁት በድህረ ምረቃ ደረጃ የሚከፈቱት እነዚህ ፕሮግራሞች በየትምህርት ዘርፉ ሀገሪቱን ወደተሻለ አቅጣጫ እንድትጓዝ የሚያስችሉ ብቁና ተወዳደሪ ምሁራን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጾኦ አላቸው፡፡ በተለይ በጋዜጠኝናትና ማስ ኮሚኒኬሽን የስልጠና መስክ የዕድገትና የፖለቲካ ተግባቦት ፣ የማስታወቂያና የህዝብ ግነኙነትን ሲያካትት በሶሻል ሳይኮሎጂ ዘርፍ ደግሞ ወደፊት በሀገሪቱ ስለሚኖረው የማህበረሰባዊ ስነልቦና እና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች በማጥናት ብሎም ዜጎች በትክክለኛው መንገድ እንዲገዙ ለማስቻል ታስቦ የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የጎልማሶች ትምህርትና የህብረተሰብ ልማት ዘርፍም በሀገሪቱ ያልተማሩ ዜጎችን ለማብቃት የጎልማሶች ትምህርት ከማህበረሰብ እደገትና ልማት ጋር አብሮ ለማስኬድ የሚስችሉ ብቁ ሙሁራን ለማፍራት ከፍተኛ አስተዋጸኦ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በፈጣን የእድገት እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው የሀዋሳ ዩኒቨርሰቲ ሀገሪቱ በምትፈልገው የዕድገት ጎዳና እንድትጓዝ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ጠንክረው እየሰሩ መሆናቸው ዶክተር ንጉሴ አመልክተው ሶስቱ አዳዲስ ፕሮግራሞቹን ከ2006 መስከረም ወር ጀምሮ ይከፈታሉ ብለዋል፡፡ ለዚህም ከስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ባሻገር ለፕሮግራሞቹ የሚመጥኑ ብቁ መምህራን፣ የተሟላ ቤተ መጻህፍት፣ የመማሪያ ክህሎችና ሌሎችን የትምህርት ግብአቶችን የማደራጀት ስራ አጠናክረው መቀጠላቸውን ጠቁመዋል፡፡ በእያንዳንዱ የትምህርት ፕሮግራም 15 ተማሪዎችን በመቀበል ለሁለት አመታት እንደሚሰለጥኑ አብራርተዋል፡፡ የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በበኩላቸው በተለይ የሀገሪቱን የዴሞክራሲ ሂደት እየቀጠለ ባለበት ብቃት ያለው ጋዜጠኛ ወሳኝነት እንዳለው አመልክተው ለዚህም በድህረ ምረቃ ደረጃ የሚከፍተው የጋዜጣኝነትና ማስ ኮሚኒኬሽን ፕሮግራም ትልቅ ፋይዳ አላው ብለዋል፡፡ ሶስቱም አዳዲስ ፕሮግራሞች የዩኒቨርሰቲው ሴኒት ካጸደቀው በኋላ በሚቀጥለው አመት መግቢያ ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ጠቁመው የተዘጋጁት ስርዓተ ትምህርቶችም በዩኒቨርሰቲው ምሁራን በሚገባ ከታዩ በኋላ አሁን ደግሞ በውጪ ምሁራን እንዲተችበትና እንዲዳብር እየተደረገ መሆኑን ገልጠዋል፡፡ የዩኒቨርሰቲው የቅበላ አቅም በመደበኛ የትምህርት ፕሮግራሞች አሁን ያሉትን 17ሺህ 500 ተማሪዎች በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጨረሻ አመር ወደ 26 ሺህ ለማድረስ በአምስቱም ካምፓሶች ሁለት ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ገንዘብ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሄዱ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡ የሚቀበላቸው ተማሪዎችም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ በመከተል 70 በመቶ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ የማህበራዊ ሳይንስ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የዩኒቨርስቲው ራዕይ በኢትዮጵያ ቀዳሚ፣ በአፍሪካ ተመራጭና በአለም አቀፍ ደረጃም ታዋቂና ተቀባይነት ያለው ለማድረግ ሰፋፊ ፕሮግራሞችን ነድፈው ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የተዘጋጁትን ስርዓተ ትምህርቶች ለማዳበር ዛሬ ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ ከዩኒቨርሰቲው ውጪ በመጡ ባለድርሻ አካላት ተተችቶ ጠቃሚ የማዳበሪያ ሀሳብ መገኘቱንም የመድረኩ አሰተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=7841&K=1

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር