አስደንጋጮቹ የሙስና ምልክቶች


በአማን ንጋቱ
በሁሉም መሥሪያ ቤቶች ግድግዳ፣ በር፣ የማስታወቂያ ሰሌዳ አንዳንዴም በውስጥ ክፍሎች የተደረቱ ጽሑፎች ይታያሉ፡፡ ቢነበብም ባይነበቡም አንዱ በሌላው ላይ እየተደራረቡ ጽሑፎች ይለጠፋሉ፡፡ አሥራ ሦስት ገደማ ፍሬ ነገሮችን የያዘው “የሥነ ምግባር ደንብ መርሆዎች” የሚለው ርዕስ በየቦታው ጎልቶ ይታያል፡፡
እንደ ቅንነት፣ ታማኝነት፣ ግልጽነት፣ ሐቀኝነት ያሉት የአብዛኛዎቹ መርሆዎች ማጠንጠኛቸው፣ “ሙስና፣ ጉቦና መድልኦን መፀየፍ” እንደሆነ ከጽሑፎቹ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይሁንና መርሆዎቹ ከወረቀት ጌጥነት ባለፈ ያመጡት ለውጥ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ መነሳት አለበት፡፡ የለውጥ ሥራዎች ተግባራዊነት፣ የድርጅት ግምገማ መጠናከር (ከብዛቱ አንፃር ትግል ደክሟል የሚሉ የኢሕአዴግ ሰዎች አሉ) የሕጉ መሻሻልና የማስቀጣት አቅም መጨመር ዕውን ሙስናን ቀንሶታል ወይስ ተባብሷል በማለት የሚጠይቁ በዝተዋል፡፡ 
አቶ ጀማል ያሲን የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር መምህር ናቸው፡፡ በትምህርት ሥርዓቱ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ቢቀረፅም ሳይሠሩ የመክበር ዝንባሌው ሥር የሰደደ በመሆኑ በቀላሉ የሚነቀል ነቀርሳ አይደለም ይላሉ፡፡ “ሲሾም ያልበላ…” ከሚለው ተረት “የኮንትሮባንድ ፈታሽ” ወይም “የመርካቶ ትራፊክ ያድርግህ” እስከሚለው ምርቃት ድረስ ሳይሠሩ የመክበር አስተሳሰብ የተንሰራፋ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ቀስ በቀስ እየገነነ የመጣው ከመንግሥታዊ መዋቅር ባለፈ በሃይማኖት ተቋማትና በሲቪክ ማኅበራት ሳይቀር የሚታይ ጉቦ የመጠየቅ ፍላጎት ምንጩም ይኼው ነው፡፡ 
ዛሬ በትምህርትና በሕክምና ተቋማት ብቻ ሳይሆን በቀብር ሥፍራ ሳይቀር ሕግ ከሚያውቀው ክፍያ ውጪ “መወሸቅ” ተለምዷል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ፣ የነፃ ገበያና ኮሚሽን (ኤጀንት) ከሥራ መስክነት ባሻገር ለሙሰኝነት በር እንደከፈተ ያስረዳሉ፡፡ ነጥብ በመነጥብ ለማየት እንሞክር፡፡
ከንግግርና ከመርህ ማለፍ ያለበት የመንግሥት ትግል
መንግሥት የፀረ ሙስና ኮሚሽን አቋቁሞ፣ የተለያዩ አገሮችን ልምድ የቀመረ የፀረ ሙስና ጥምረት አደራጅቶ (ስብስቡ የራሱ ክፍተት ቢኖረውም)፣ በወንጀል ሕጉ የሙስናውን ክፍሎች የቅጣት ደረጃ ማሻሻሉ አንደኛው አዎንታዊ ዕርምጃ ነው፡፡ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት በሥርዓት ደረጃ “የከፋው ችግራችንና የሥርዓቱ አደጋ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው” ብሎ በማመን ይህንኑ ፈተና ለመቋቋም ትግል በመጀመሩ መሰናክልን ቀድሞ እንደማወቅ ይቆጠራል፡፡ ያም ሆነ ጠበቅ ያለ ዕርምጃና በውጤት የታጀበ የፀረ ሙስና ትግል መደረጉ ላይ ብዙዎች ከፍተኛ ጥርጣሬ አላቸው፡፡ ይልቁንም የይስሙላ ነው ይላሉ፡፡ 
ፀረ ሙስና ኮሚሽን በቅርቡ በወጣው መረጃ እንደገለጸው፣ በትምህርት ቤት ከሚሰጠው የሥነ ምግባር ትምህርት ባሻገር ሰፊ የአስተምህሮትና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በዚህም፣ “አሁን ስለሙስና ጎጂነትና ነቀዝነት እንዲሁም ወንጀል መሆን ያልተገነዘበ የለም፤” ይላል፡፡ ነገር ግን አደጋው ሊታረም የሚችለው በራሱ በሕዝቡ ትግል መሆኑን ተገንዝቦ በፅናት መሥራት ላይ የሚቀር ተግባር አለ በማለት ያስረዳል፡፡ በእርግጥ በፀረ ሙስና በወንጀል ሕግ ቁጥር 414/96 አንቀፅ 404 የሙስና ወንጀል በግልጽ ተቀምጦ፣ ዘርዘር ያሉ አንቀጾች መካተታቸውና በመክሰስና በማስቀጣት አቅሙ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም ይናገራል፡፡ 
አንዳንድ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትም የመንግሥትን ቁርጠኝነትን ሲገልጹ እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የደረሱ የአገሪቱ መሪዎችን ጭምር በሙስና ወንጀል ማስጠየቁን ያብራራሉ፡፡ በፌደራልና በክልል ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች በድርጊቱ ውስጥ ከተገኙ ከመጠየቅ እንደማያመልጡ በመጥቀስ (በተቃራኒ ወገን ግን ድርጅቱ ቁርጠኛ አይደለም የሚል ትችት ይነሳል) አስተያየት ሰጪዎችም ጅምሩ የሚናቅ ባይሆንም በቂ አይደለም ባይ ናቸው፡፡ በግል ጥብቅና ሥራ የተሰማራው አቶ መላኩ አሻግሬ የፀረ ሙስና አካሄድ ሰዶ ማሳደድና ተመዝብሮ ያለቀን ጉዳይ ወደ መፈለግ ያዘነብላል ሲል ያስረዳል፡፡ ለአብነት ያህል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሚመለከታቸው አካላት ሀብታቸው ተመዘገበ ቢባልም መቼ ለሕዝብ ይፋ ተደረገ? ዕውን ሁሉም ያስመዘገበው በተጨባጭ ያለውን ሀብት ነው (አንዳንዶች በእርግጥም ያላቸው ሕንፃ፣ ቪላና ትርፍ ቤት በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከተሞች አላስመዘገቡም ስለሚባል) የሚሉ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ 
አንዳንዶች ደግሞ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተቋማዊ አቅም በቂ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ጥቆማ መቀበያ ክፍሉ በየሳምንቱ በርካታ ጥቆማዎች ቢደርሱትም ከመመርመር (Investigation) ይልቅ የቀረበውን መረጃ እንዳልተሟላ ይቆጥራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚሠራ አንድ ባለሙያ በአንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች ላይ የሚታየውን ሕገወጥ ድርጊት በተደጋጋሚ ቢጠቁምም በቂ ምላሽ አልተሰጠውም፡፡ ምክንያቱን ሲጠይቅ ደግሞ የፌዴራል ፀረ ሙስና ተቋሙ በትልልቅ ፕሮጀክቶችና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ በጀቶች ላይ እንደሚያተኩር ተነግሮታል፡፡ የአዲስ አበባ ችግሮ የሚናቅ ባይሆንም በየሴክተሩ ትንሽ ትልቁን ለመመርመር አቅም የለም (አዲስ አበባ እንደ ክልሎች የራሱ ፀረ ሙስና ተቋም የለውም) መባሉን ያስታውሳል፡፡ የፋይናንስ ቢሮው የሚሠራው ኦዲት ደግሞ በጥቃቅን ክፍሎች ላይ እንጂ የሚታሙ “ትልልቅ ምዝበራዎችን” አይነካም ሲል ይተቻል፡፡ 
ይህ ባለሙያ ከሙስና የፀዳ ሥርዓት ማለትም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአንድ ወቅት የመላዕክት ስብስብ አይደለንም እንዳሉት መፍጠር ባይቻል እንኳ መመከት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የተቋሙን አቅም ማሳደግና የአስፈጻሚውና የፍትሕ አካሉ ጥንካሬ ያሻል፡፡ ሥራውን በተመለከተ በግልጽነትና በተጠያቂነት መንፈስ ለሕዝቡ ሊገለጽለት ይገባል ይላል፡፡ 
ትልቁ የሕዝብ ወኪል ሕግ አውጪው ጥርስ ይኑረው 
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስካሁን ከ740 የማያንሱ አዋጆችን በማውጣት የአገሪቱ የልማት፣ የዲሞክራሲና የውጭ ግንኙነት ሥራዎች እንዲጠናከሩ በማድረግ ላይ መሆኑ ይነገራል፡፡ አስፈጻሚውን “በመከታተልና በመቆጣጠር” ሥራ ላይም ይንቀሳቀሳል ይባላል፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ሙስናና መድልኦን ለመታገል የሚረዱ ሕጎችን ማውጣቱን እንጂ አፈጻጸማቸውን ፈትሾ የሠራው ተግባር አልተሰማም ይላሉ፡፡ አስደንጋጭ የኦዲት ሪፖርቶችን ሰምቶ “በሙሉ ድምፅ” ከማፅደቅ ባለፈ ምን የማሻሻያ ዕርምጃ አስወሰደ? ከጥፋቱስ እነማን ተማሩ? የሚሉ ጥያቄዎች በዚያም በዚህም ይደመጣሉ፡፡ 
ሰሞኑን በቀረበው የአገሪቱ የ2004 ዓ.ም. ኦዲት ሪፖርት በ57 ናሙና ተቋማት ላይ ተሠርቶ የ1.4 ቢሊዮን ብር ገደማ ብክነት፣ ምዝበራና ሒሳብ ማወራረድ እንዳልተፈጸመ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴርን የሚያክል አንጋፋ መሥሪያ ቤት 460 ሚሊዮን ብር ገደማ አለማወራረዱ ወዴት እየሄድን ነው? ያስብላል የሚሉ አሉ፡፡ የትምህርት ተቋማትና ሚኒስቴሩ ካልታረሙ ምን እንማራለን? ብሎ መሥጋት ተገቢ ነው፡፡ 
ባለፉት ተከታታይ ዓመታትም ከ800 ሚሊዮን እስከ 1.1 ቢሊዮን ብር በየዓመቱ የኦዲት ሪፖርት ክፍተቶች ለፓርላማው ቀርበዋል፡፡ ምን ዕርምጃ ተወሰደ? ቢያንስ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ከችግሩ ተነስቶ ያገኘው ውጤት የት ጋ ተሰማ? ይህ በጥቂት መሥሪያ ቤቶች የተካሄደ የናሙና ኦዲት በትልልቅ ፕሮጀክቶችና በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራልና የክልል መንግሥታዊና ሕዝባዊ መሥሪያ ቤቶች ቢካሄድ ብክነቱ ምን ያህል ይሆናል? በማለት የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ሕግ አውጭው አካል የሕጉን ተፈጻሚነት ከመከታተል በላይ የሕዝብ ዕንባ የመጥረግና አጥፊዎችን የመታገል ሕጋዊና ሞራላዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባው ነበር፡፡ ሕግ አውጪው አስፈጻሚውን መቆጣጠር ካልቻለ ወዴት እየተሄደ ነው? 
ከመንግሥታዊ ቢሮክራሲ ውጭ ያልተቀጣጠለ ትግል 
የሙስና ፈተና ሥልጣንን መሠረት አድርጎ በስፋት የሚፈጸም ነው፡፡ በተለይ በአፍሪካ፡፡ ያም ሆኖ እያደገ በመጣው የግል ሴክተር ውስጥ በአክሲዮኖችና በማኅበራትም በከፍተኛ ሁኔታ የሚንፀባረቅ ችግር ነው፡፡ ከሰሞኑ በዚሁ ጋዜጣ ላይ በባንክ ሴክተሩ የሚስተዋለውን አስፈሪ ድርጊት አንብበናል፡፡ በዝርዝር ቢጠና ከዚህም በላይ አደጋው እንደሚኖር በሬዲዮ ውይይትም ሲጠቀስ አድምጫለሁ፡፡ በተመሳሳይ በሌሎች አካባቢዎችስ ሙስና አይሸትምን በማለት አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችን ጠይቄአለሁ፡፡ 
አቶ በርሄ የተባሉ በግል ሥራ የሚተዳደሩ የአዲስ አበባ ነዋሪ፣ “እላፊ የመፈለግና ያልሠሩበትን የመሰብሰብ ዝንባሌ በግልና በመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተብሎ ሊለያይ አይችልም፡፡ በተፈጠረው ዕድልና በአጋጣሚው ሁሉ የሚሰርቅ ሰው እጁ ሊፀዳ አይችልም፤” ይላሉ፡፡ በመሆኑም ዛሬ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ የሚሠሩ አንዳንድ ሰዎች በምን በለፀጉ? አክሲዮን ሰብስበው ትርምስ ውስጥ የገቡ ወይም የተሰወሩ እያየን መሆኑ ለምን ይዘነጋል በማለት ይጠይቃሉ፡፡ 
“በግል ተቋራጮችና ኮንትራክተሮች አካባቢ ያለው በፍጥነት የመበልፀግ ዝንባሌስ ምንጩ ምንድን ነው? ከሦስትና ከአራት ዓመታት በፊት አነስተኛ ኮንትራክተር ፈቃድ የነበረው ሁሉ ተምዘግዝጎ ሰማይ የነካው በምንድን ነው?” የሚሉት አቶ በርሄ፣ በሥራና በላብ ብቻ የተገኘ ሳይሆን ካለቀረጥ በሚገባ ዕቃ፣ በሕገወጥ ብረትና ሲሚንቶ ሽያጭ፣ በግንባታ ጥራት መጓደል (በፍጥነት መሥራት…)፣ ወዘተ እንደሆነ ግምታቸውን ይሰነዝራሉ፡፡ በእርግጥም በቅርቡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለጋዜጠኞች በሰጠው ሥልጠና ወቅት የትምህርትና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ አሰፋ ያሉትም ከዚህ አባባል ጋር ይስማማል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰፊ የመሠረተ ልማት ሥራ ውስጥ በገቡ አገሮች ዋነኛ የሙስና ምንጭ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ነው፡፡ “እኛም እንደ ሱስ ቦታ (Senstive Area) ይዘነዋል፤” ነበር ያሉት፡፡ ይህ ዘርፍ አጓጊና ትርፍ የሚዛቅበት በመሆኑ ከተለያዩ ቦታዎች በሙስና በተገኘ ገንዘብ የተገዙ የኪራይ ተሽከርካሪዎችና ማሺን አቅራቢዎች እንደበዙበት እያየን ነው፡፡ መሬት ወረው ከሸጡ እስከ ባንክ ባለሙያዎች ድረስ ይህንን የሞቀ ቢዝነስ ተቀላቅለውታል፡፡ 
ከእነዚህ ምልክቶች አንፃር ፀረ ሙስና ኮሚሽንም ሆነ መንግሥት (ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው) ልብ ያላሉት የሕዝብ ሀብት መመዝበሪያ ሆኗል የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፣ የመንግሥት የሥራ ኃላፊና ባለሙያ ሀብቱ እየተመዘገበና እየተገመገመ መረጃ ሲገኝ ተከሶ እየተቀጣ ነው፡፡ ለሌላው ግን እንዲያውም “ለመንግሥት ሌባው” መሸሸጊያ ሆኗል፡፡ ንፋስ አመጣሽና ሙስና መበልፀጊያ እንዳይሆኑ መጠርጠር ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የእነዚህ ድርጊቶች የከፋው አደጋ ደግሞ በሕዝቡ ውስጥ የጎላ የኑሮ ልዩነት በመፍጠር፣ ተስፋ ቆራጭነትና ብሶትን መቀስቀሳቸው ነው፡፡ ስለዚህ ጠበቅ ሊባልበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በ“ዕድገት” ስም እየተጀቦነ ውስጥ ውስጡን የአገር ኢኮኖሚ የሚበላው “ነቀዝ” መድኃኒት ሊፈለግለት ይገባልም ይላሉ፡፡ 
የሌሎች ልማታዊ ባህሪ ያላቸው አገሮችን ልምድ ያልቀመረ ትግል 
ቻይና በዓለም በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ የትልቅ ኢኮኖሚ ባለቤት ነች፡፡ በትሪሊዮን ዶላሮች የተከማቸው ገንዘቧ ከራሷ አልፎ ለአሜሪካና ለሌላው ዓለም ኢንቨስትመንት እያገለገለ ነው፡፡ በዚያው ልክ የከፉ የሙስና ድርጊቶች የሚስተዋሉባት አገር ነች፡፡ ዘ ግሎባል ታይምስ እንደገለጸው እ.እ.አ. ከ2008 እስከ 2011 ባለው ጊዜ ውስጥ ከቻይና በቢሊዮን የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚገመት ሀብት ዘርፈው ወደ ሌላ አገር የጠፉ 128 ሰዎች ተከሰዋል፡፡ አብዛኛዎቹ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የከተማ ከንቲባዎችና ሥራ አስኪያጆች፣ የባንክ ገዢዎችና ኃላፊዎች፣ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊዎችና ሙያተኞች መሆናቸውን ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡ እንደዚያም ሆኖ ቻይና ሙሰኞችን በመቅጣት ትታወቃለች፡፡ ሙስና የዘረፉትን ሀብት ከማስመለስ አንስቶ እጅ እስከ መቁረጥና ሞት ድረስ የሚያስቀጣ ነው በቻይና፡፡ የሀብት ማስመዝገብ ሥራም ባለፉት ዓመታት የተጀመረ ሲሆን፣ በውሸት ሀብት ያስመዘገበ የሚከፍለው ዋጋ ቀላል አይደለም፡፡ የግሉ ሴክተርና አክሲዮኖችም ቢሆኑ ከግብር ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ የገቢና ወጪ ምዝገባ ሥርዓት ሚናቸው ተለይቷል፡፡ መንግሥት ከቻይና የሚወስደውን የልማት ተሞክሮ በፀረ ሙስና ትግሉስ ለምን አይደግመውም? ይላሉ ታዛቢዎች፡፡ ከዚህ ባለፈም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት ሥርዓት በመዘርጋት ሙስናን ለምን አይቆጣጠርም በማለት የሚጠይቁ አሉ፡፡
በብሔራዊ የፀረ ሙስና ጥምረት አስፈላጊነትና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ ላይ ጥናት ያዘጋጁት ረዳት ፕሮፌሰር ጌታቸው አሰፋ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር) የደቡብ አፍሪካ፣ የአርጀንቲና፣ የህንድ፣ የቦትስዋና የጋናና የደቡብ ኮሪያን ተሞክሮ ፈትሸዋል፡፡ ታዲያ የብዙዎቹ አገሮች ጥምረት ጠንካራ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንን ሊያግዝ የሚችልና ገለልተኛ የመሆን አቅም ያለው ይመስላል፡፡ 
“ለምሳሌ የአፍሪካዊቷ ቦትስዋና ፀረ ሙስና ጥምረት የእንባ ጠባቂ ተቋም፣ ዋና ኦዲተር፣ ገልተኛ የምርጫ ኮሚሽን፣ የፀረ ሙስናና የኢኮኖሚ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት፣ የመገናኛ ብዙኃንና (የግሉን ጭምር) የሲቪል ማኅበራትን ያካትታል፤” የሚለው ጥናቱ፣ በጋናም ጥምረቱ የመንግሥት ተቋማትን፣ የግል የንግድ ተቋማትንና የዘርፍ ማኅበራትን፣ እንዲሁም የሙያና የሲቪል ማኅበራትን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲን ጨምሮ ያቀፈ ሲሆን፣ የራሱ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤትና ፎረም ኖሮት የተሻለ ስብስብ ያለውና ለውጥ እየመጣ ያለ ተቋም ነው፡፡ የደቡብ ኮሪያ ጥምረትም ሞዴል የሚባል ሲሆን፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማሰባሰብ ተጨባጭ ውጤት ማምጣቱን ረዳት ፕሮፌሰሩ በጥናታቸው አመልክተዋል፡፡ 
ከዚህ አንፃር በአገራችን የፀረ ሙስና ጥምረት መቋቋሙ አንድ ዕርምጃ ሆኖ አሳታፊነቱና ገለልተኝነቱ በቂ አይደለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ቢያንስ የሲቪክ ማኅበራት፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና የግል ሚዲያ ማኅበራት ወኪሎችን በሚገባ ባለማሳተፉ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ለመታገል አቅም ያንሰዋል በማለት ይተቻሉ፡፡ ከዚህም በላይ የራሱ አስፈጻሚ ኖሮት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ መመራቱ በጎ ጅምር ቢሆንም፣ ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞለት የሕዝብ ቅሬታና መረጃን እየተቀበለ ካልሠራ ጥንካሬ ሊኖረው እንደማይችል የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ 
“የመንግሥት ሚዲያ፣ እምባ ጠባቂና ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ ናቸው ወይ?” የሚለው ጥያቄ በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎችና በሕዝቡ ዘንድ ተመሳሳይ መልስ ሲኖረው፣ የዴሞክራሲ ግንባታ ብቻ ሳይሆን ሙስናንም ለመታገል እንደሚረዳ ነው ባለሙያዎቹ የሚናገሩት፡፡ ስለሆነም መንግሥት በብዙ ዘርፎች ከሌሎች መንግሥታት የሚቀስመውን ልምድ ለዚህ ጉዳይም ማዋልና በፅናት መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ 
ምን ይደረግ?
ሙስና ሁሉንም ነገር የሚያጠፋ አደጋ ነው፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ያስተጓጉላል፡፡ የሕግ የበላይነትን ይሸረሽራል፡፡ ወንጀልና ማጭበርበር ያንሰራፋል፡፡ በዚህም የሕዝብ ብሶትንና ሥርዓት አልበኝነትን ያነግሳል፡፡ ይኼ ሟርት ሳይሆን ሥጋት ነው፡፡ ስለዚህ የጋራ ጠላት የሆነውን የልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን እንቅፋት በጋራ መታገል ግድ ይለናል፡፡ “በአሉባልታና መረጃ በማይቀርብበት ወሬ” ጊዜ ማጥፋት ሳይሆን ካለድካም የበለፀጉ ካሉ ማጋለጥ ግድ ይላል፡፡ መንግሥትም ቢሆን ከራሱ ቢሮክራሲ ውጪ በግሉ ሴክተርና በኅብረተሰቡ ውስጥ ሙስና እንዲወገድና የሕግና የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በሁሉም አካባቢ አደጋው መኖሩን የሚያሳየው፣ “በአሥር ዓመታት ውስጥ 200 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የአገሪቱ ገንዘብ ወደ ውጭ ወጥቷል!” የሚለው አስደንጋጭ የዓለም ፋይናንስ ተቋማት ፎረም ዜና ነው፡፡ ይኼ ጉዳይ ቀደም ብሎ ቢነገርም መንግሥት ማስተባበሉን አልሰማሁም፡፡ ስለሆነም የፀረ ሙስና ጥምረቱና የተወካዮች ምክር ቤት ጥርስ ኖሯቸው ሊታገሉ ግድ ይላል፡፡ የፍርድ ቤቶችና የሚዲያው ኃላፊነትም ትልቅ ነው!! ለአንድ ዓላማ ተጣምሮ አገርን ማዳን ይገባልና!!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው AmanN@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡    

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር