መለስ ሀዋሳን ክልል ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር


መለስ ሀዋሳን ክልል ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር
የሲዳማ አገር ሽማግሌዎች አቶ መለስ እድሜያቸው አጭር እንደሚሆንና እንደሚቀሰፉ ነግረዋቸው እንደነበር ተሰማ። በክልሉ የአገር ሽማግሌ ከሚባሉት መካከል አንዱን በማነጋገር በተለይ ለጎልጉል የተላከው መረጃ እንደጠቀሰው መለስ እድሜያቸው ሊያጥርና በድንገት ሊቀሰፉ የሚችሉት የሲዳማን ባህላዊ ልብስ ለብሰው ከዋሹ ነበር።
እንደመረጃው መለስ በ1997 ዓ ም ምርጫ ውጥረት ውስጥ በነበሩበት ወቅት አራት ተከታታይ ቀናት ሃዋሳ የብሄር ብሄረሰቦች አዳራሽ ውስጥ የብሄረሰቡን ተወላጆች ሰብስበው አነጋግረው ነበር። “አዲስ አበባ ያለው ድንኳናችን ፈርሷል። እዚህም ከፈረሰ በቃን ማለት ነው” በማለት የአገር ሽማግሌዎችን በተማጸኑበት ንግግራቸው መለስ አስቀድሞ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።
ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ሙሉ ልብስ ለብሰው መድረክ ላይ ተቀምጠው የነበሩትን መለስ “ማን እዛ ላይ አወጣህ? አውርደንሃል” በማለት ሽማግሌዎች ሲናገሩ በወቅቱ የጸጥታ ሃይሎችና የአቶ መለስ ጠባቂዎች ተደናግረው ነበር። ሽማግሌዎቹ አቶ መለስን ከመድረክ አውርደው “አስቀድመህ ያገራችንን የባህል ልብስ ለብሰህ ነው መድረክ ላይ የምትወጣው” በማለት ከመድረክ አውርደው ጓዳ በማስገባት “ሴማ” የሚባለውን የባህል ቡሉኮ አለበሱዋቸው።
“ይህንን የሚለብስ እውነት የሚናገር ብቻ ነው” በማለት አቶ መለስ መዋሸት እንደማይገባቸው ሽማግሌዎቹ አሳስበው እንደነበር የጠቆመው መረጃ፣ “ይህንን የሚለብስ መሪ የሆነ፣ እውነት የሚናገር ብቻ ነው። የሚዋሽ ይሞታል። እድሜው ያጥራል። ይቀሰፋል” በማለት በሲዳምኛ ደጋግመው መናገራቸውንና አቶ መለስም የተባሉትን ለማድረግ ተስማምተው እንደነበር አመልክቷል።
በዚሁ መሰረት አቶ መለስ በ1997 ምርጫ ተከትሎ ካጋጠማቸው ቀውስ ለመውጣት ሃዋሳን ከሌሎች የደቡብ አካል በመነጠል ራስዋን የቻለች ክልል ለማድረግ ለቀረበላቸው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ሃዋሳን ክልል ማድረግ አስቀድመው ቃል በመግባት በወቅቱ ከሲዳማ ህዝብ ማግኘት የፈለጉትን ድጋፍ ለማግኘት እንደተጠቀሙበት መረጃው ያስታውሳል።
አሁን በስደት የሚገኝና በወቅቱ ስብሰባው ላይ ተገኝቶ እንደነበር የገለጸ ለጎልጉል እንደተናገረው ቢችልም አቶ መለስ የገቡትን ቃል ለማስፈጸም የተመረጡትን 20 ሽማግሌዎች አዲስ አበባ ትልቅ ሆቴል በማስቀመጥ ገንዘብ በመስጠትና መሬት በማደል በሲዳማ ቅንጅት እንዲመረጥ የቀሰቀሱ ሰዎችንና ዋና አስተባባሪዎች ላይ የቂም ርምጃ እንዲወሰድ አድርገዋል።
ጉዳዩ አፈታሪክና ወይም ተረት ቢመስልም የሲዳማ አባቶች መለስ በፈጸሙት ክህደት እንደረገሟቸውና ሞቱ ተብሎ የሚታመነውም በዚሁ ርግማን እንደሆነ ያመለከተው መረጃ የሲዳማ ህዝብ አሁን እየደረሰበት ያለው በደልና ግፍ እያየለ በመሄዱ የሲዳማ አርነት ንቅናቄ “ሲአን” ራሱን ከምርጫ ማግለሉ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው አመልክቷል። ድርጅቱ ዋና ጸሃፊ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ከኢሳት ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ከ787 በላይ አባሎቻቸው በመታሰራቸውና ባለፈው ሳምንት በዳሌ ወረዳ እጩ ተወዳዳሪው ተሾመ ካሰና የሚባል ሰው ተገድሎ በመገኘቱ እንዲሁም የሲአን አባላትን ማዋከብ፣ ከስራ ማፈናቀል እና ተማሪዎችን ማባረሩ በመቀጠሉ ድርጅቱ ራሱን ለማግለል መወሰኑን ዋና ጸሀፊው ተናግረዋል።
የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአካባቢው ተሰማርተው በድርጅቱ አባሎች ላይ ወከባ እየፈጸሙ መሆኑን ዋና ጸሀፊው ተናግረዋል። መንግስት ከምርጫው እንዳይወጡ ለምኗቸው እንደነበር ዋና ጸሀፊው መግለጻቸውን ኢሳት ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር