የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ተስፋ ፈንጣቂ ዕርምጃ


ባለፈው ሳምንት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆና የተወለደች ሕፃን ወዲያው በተደረገላት ሕክምና ከቫይረሱ ነፃ የመሆኗ ዜና መሰማት በዓለም ኤችአይቪን በመዋጋት ረገድ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ፈንጣቂ ሆኗል፡፡
አሜሪካ ሚሲሲፒ ውስጥ እ.ኤ.አ. 2010 ላይ የተወለደችው ሕፃን ከቫይረሱ ነፃ ልትሆን የቻለችው እንደተወለደች ባሉት 30 ሰዓታት ውስጥ ከፍተኛ የፀረ ኤችአይቪ ሕክምና ተደርጐላታል፡፡

ሕክምናው በዚያም ሳያበቃ ለአሥራ ስምንት ወራት ዘልቋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ሕፃኗ ከቫይረሱ ነፃ መሆኗን ይፋ ያደረገው በባልቲሞር የሚገኘው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ቡድን መሪ ዶክተር ዲቦራ ፐርሳውድ ግኝቱ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው የሚወለዱ ሕፃናትን ከኤችአይቪ ኢንፌክሽን ነፃ በማድረግ ሕክምና ትልቅ ዕርምጃ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቢሆንም ግን ተመራማሪዎቹ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው የሚወለዱ ሕፃናትን ሕፃኗ ከተፈወሰችበት መንገድ በተሻለ ሕክምና ከኢንፌክሽኑ ነፃ ማድረግ፣ በተለይም ሕክምናውን ለስድስት ሳምንታት ማሳጠር ሊተኮርበት የሚገባ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕፃናት የኤችአይቪ ፖዘቲቭ ኢንፌክሽንን በመከላከል ረገድ የኤችአይቪ ቫይረስ ከእናቶች ወደ ሕፃናት እንዳይተላለፍ የሚደረግ ሕክምና ዓይነተኛው መፍትሔ ነው፡፡ ነገር ግን ሕክምናው በቀላሉ በሚገኝባቸው እንደ አሜሪካ ባሉ የበለጸጉ አገሮች እንኳ ሕፃናት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው ይወለዳሉ፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ ውስጥ በየዓመቱ ከ100 እስከ 200 የሚሆኑ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ ሕፃናት ይወለዳሉ፡፡ የሮይተርስ ዘገባ እንደሚያመለክተው ዓለም ላይ በተለይም በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች በቀን አንድ ሺሕ የሚሆኑ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሕፃናት ይወለዳሉ፡፡ ግኝቱ ለእነዚህ ሕፃናት ትልቅ ተስፋ ነው፡፡

የ28 ዓመቷ አሜሪካዊት ኤችአይቪ ኤድስ አክቲቪስት ሔዲያ ብሮድበንት ግኝቱ ፖዘቲቭ ሆነው ለሚወለዱ ሕፃናት ትልቅ ተስፋና ብርሃን እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ‹‹የጭንቅላት፣ የደም ኢንፌክሽን ነበረብኝ፡፡ በአንድ ወቅት ሐኪሜ ከትምህርት ቤት ቆይታው ጀምሮ ሰምቶት የሚያውቀው ዓይነት ኢንፌክሽንም ነበረብኝ፤›› የምትለው ወጣት ባለፈው ሳምንት የሕፃኗን ከኤችአይቪ መፈወስ ስትሰማ እሷም ጨቅላ ሳለች ይህ ዕድል ገጥሟት ቢሆን ኖሮ ሕይወቷ ምን ሊመስል ይችል እንደነበር ራሷን ጠይቃለች፡፡ ‹‹ዘወትር ወደ ሆስፒታል መመላለስ ግድ አይሆንብኝም ነበር፡፡ ዘወትርም መድኃኒት መዋጥ ግዴታዬ አይሆንም ነበር፡፡ ትልቅ መታደል ነበር፤›› ትላለች፡፡

ወጣቷ በቀን ሦስት ፀረ ኤችአይቪ ኪኒኖች ትወስዳለች፡፡ ከዚህ ባሻገርም ለሰውነት ብርታት ተጨማሪ ኪኒኖችን ትወስዳለች፡፡ የራስ ምታትና ሆድ ቁርጠት በተደጋጋሚ የሚሰሟት የፀር ኤችአይቪ መድኃኒት ተጓዳኝ ችግሮች ናቸው፡፡ ብታቋርጥ መድኃኒቱ መለመድን ይፈጥራል፡፡

በሰሜን አፍሪካና መካከለኛው ምሥራቅ ሦስት በመቶ የሚሆኑ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እናቶች ቫይረሱ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት ይሰጣቸዋል፡፡ በመካከለኛውና ምዕራብ አፍሪካ 23 በመቶ የሚሆኑ ነፍሰ ጡር እናቶች ፀረ ኤችአይቪ ሕክምናውን ያገኛሉ፡፡

ተመራማሪዎች እንዳሉት ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው የሚወለዱ ሕፃናትን በማከም ረገድ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው ትኩረት የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒቶቹ ዓይነት ወይም ብዛት ላይ መሆን የለበትም፡፡ ሕክምናው በዚህ መልኩ የሚደረግ ከሆነ በቀጣይ ትልቅ ተስፋ እንደሚኖርም አመልክተዋል፡፡ በተመሳሳይ ለተፈወሰችው ሕፃን የተደረገውን ሕክምና ለሌሎች ሕፃናትም በማድረግ ሕክምናው በእርግጥም ለሌሎች ሕፃናት ፈውስ ያመጣ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ወደፊት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ ነገሩ ትልቅ ተስፋ ፈንጣቂ ቢሆንም በተደጋጋሚ ተግባራዊ ሆኖ መረጋገጥ እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር