የደኢህዴን/ኢህአዴግ አስተዳደሩና ጎሴኝነቱ በሲዳማ ህዝብ ላይ ያደረሰው ኪሳራ

ከማህበራዊ መረብ ላይ የተገኘ ጽሁፍ
በሃዋሳ ዱሜ

 ኢትዮጵያ ሀገራችን ወዳና ፈቅዳ የፌዴራል መንግሥት ህገ-መንግሥት አካል አድርጋ የተቀበለችውና ዓለም ዓቀፍ ሰብአዊ መብቶች ሰነድ አንቀጽ 1 ላይ እንደተደነገገው ዘረኝነትም ሆነ ጎሴኝነት ከሰብአዊነት መርህና ከሰብአዊ መብቶች የሚቃረን መሆኑንና በዚህ መሠረት የመጀመሪያ አንቀጽ የሚያውጀው የሰው ልጆች እኩልነትን ነው፡፡
ሰዎች ሁሉ እኩል ክብርና መብቶች ይዘውና ነፃ ሆነው ተፈጥረዋል፡፡ ሰው የሚባለው ፍጡር የማሰብና የማመዛዘን ችሎታ በተፈጥሮ ስለታደለ እርስ በርሳቸው በወንድማማችነት ሊተያዩ ይገባል ይላል፡፡

በአንቀጽ ሁለት መሠረት ደግሞ ጉዳዩን ባይበልጥ በማብራራት በዘር፣በቀለም፣በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተያየት፣በህብረተሰብ ምንጭ፣በሀብት፣በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደርግበት እያንዳንዱ ሰው በተጠቀሱ መብቶችና ነፃነቶች የመጠቀም መብት አለው ይላል፡፡

ነገር ግን በሲዳማ ውስጥ በተግባር የሚታየው የዚሁ ተቃራን ነው፡፡
የተወሰኑ ማስረጃዎችን መጥቀስ ካስፈለገ፡-
ደኢህዴን/ኢህአዴግ የመንግሥት መዋቅርን ማስተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሲዳማ ህዝብ በጎሳና በቤተሰብ እንዲከፋፈልና አንድነቱ እንድናጋ ፖለቲካዊ ደባ ተሰርቶበታል፡፡
ህዝባችን ግን አስቀድሞ በመንቃቱ በጎሴኝነት ስሜት የተዘራው ቫይረስ በመንግሥትና በፖለቲካው መዋቅር ተወስኖ ቀረ እንጂ ሊያስከትል የሚችለው አደጋና ኪሳራ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
አሁንም ቢሆን በጎሴኝነትና በዘረኝነት የተዘራብን በሽታ በየወረዳው ህዝብን ሰለባ እያደረገና ገና ብዙ ዋጋ የሚያስከፊል የተቀበረብን ፈንጂ ያለ መሆኑን አሁን በተለያዩ ጎሳዎች ላይ እየተሠራ ያለው ከፋፋይ ድራማ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚሁ መሠረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ለምሳሌ፡- የተማረ የሰው ኃይል የለንም እየተባለ በሌላ በኩል ያለ በቂ ድጋፍ በግል ጥረታቸው ዩኒቬርስቲ ገብተው ትምህርት ጨርሰው የመጡ ወጣት ምሁራን በሙያቸው በየወረዳው በፈለጉበት ተመድበው መሥራት እንዳይችሉ ጎሴኝነት መሰናክል ሆኖበታል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሚጠየቁት የትምህርት ዓይነትና ውጤት ሳይሆን የማን ጎሳ እንደሆነ ነው፡፡ በወረዳው በሥልጣን ላይ ያሉ ግለሰቦች ጎሳ ከሆኑ ገና ከዩኒቬርስቲ ትምህርቱን እንኳን ሳይጨርስ የስራ መደብ ይዘጋጅለትና የጠቀሙ እየመሰላቸው ወደ ጎሴኝነት መረብ ውስጠ ያስገቡአቸዋል፡፡
አንደኛው መንገድ በዚሁ መሠረት ነው የተቀበረብን የጎሴኝነት ፈንጂና በሽታ የሚፈነዳብንና የሚተላለፊብን፡፡
በዚህ የተነሣ ነው ብዙ የተማሩ የሲዳማ ልጆች ከዚህ ከጎሴኝነት ተላላፊ በሽታ በመጥላት ህዝባቸውን ማገልገል ሳይችሉ ተሰደው ሌላ አካባቢ ለመሥራት የሚገደዱት፡፡የቀሩት ደግሞ ይህም ያልፋል በማለት በማይመጥናቸውና ከትምህርታቸው ጋር በማይሄድ ቦታ ተመድበው ያሉት ወጣት ጡረተኞችን ቤቱ ይቁጥረው፡፡
የዚህ ችግር ሰለባ የሚሆኑት ከዩኒቬርስቲ ተመርቀው የሚመጡ ብቻ ሳይሆኑ በማንኛውም ደረጃ የሚመደቡ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ብሎም ከፍተኛ ካድሬዎችም ጭምር ከተወለዱበት ወረዳ ውጪ ሲመደቡ ተመሳሳይ የችግሩ ገፈት ቀማሽ በመሆን የሚያማሪሩ እጅግ በርካታ ናቸው፡፡

በዚህ ረገድ ህዝባችን የደረሰበት ኪሣራ ማካካሻ የሌለው መሆኑን ልንገነዘበው ይገባል፡፡
በሌላ በኩል የመልካም አስተዳደር እጦትና ጎሴኝነት በህዝባችን ላይ ያመጣው ችግር፣ በሲዳማ ክልል ከህዝባችን ጋር አብረው መኖር ብቻ ሳይሆን ተጋቢተውና ተዋልደው አንድ ሆነው ለዘመናት የኖሩትን ህዝቦችን ማጋጨት ብቻ ሳይሆን ድንበርተኛ ከሆኑ ብሔሮች ጋር በሚፈጠሩት ተደጋጋሚ ግጭቶች ህዝባችን ከፍተኛ ቁሳዊና ስነ-ልቦናዊ ኪሳራ ያደረሱብን አሳዛኝ ክስተቶች ናቸው፡፡

በወንዶ ገነት፣በቦርቻ፣በማልጋ፣በሀዋሳ ዙርያ እና በሎካ አባያ ወረዳዎች አካባቢ ህዝባችን ላይ የደረሰው አላስፈላጊ የህይወት መስዋዕትነት፣ሰብአዊ፣ቁሳዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ኪሣራ፣ የህዝብ መፈናቀልና መንገላታት ከመልካም አስተዳደር እጦትና የጎሴኝነት ውጤቶች ሲሆኑ ደኢህዴን/ኢህአዴግ በሲዳማ ህዝብ ላይ አቅዶ ከሚንቀሳቀስባቸው አንደኛውና እየተሳካላቸው ያለው የዕቅዳቸው ቀዳም ክፍል እንጂ እዚህ ላይ ያበቃ ጉዳይ እንዳልሆነ የሲዳማ ካድሬዎችም ጭምር ቆም ብለው የህዝባችንን ወድቀት ልገነዘቡት ይገባል፡፡
አሁንም ቢሆን በተጠቀሱት አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ዘላቂ መፍትኼ ያገኘና ህዝባችንን እፎይ የሚያሰኝ እንዳልሆነና ከደኢህዴን/ኢህአዴግ ገዥነትና ውሳኔ ሰጭነት ሥር እስካልወጣንና እራሳችንን በራሳችን ማስተዳደር እስካልቻልን ድረስ ከተጠቀሱ አካባቢዎች በተጨማሪ በሁሉም አካባቢዎች በስጋት ቀጠና ውስጥ መሆናችን ግንዛቤ ሊያገኝ ይገባል፡፡

http://www.facebook.com/HawassaDumme

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር