በሃዋሳ ከተማ ከ7 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው የነዳጅ ማደያ አገልግሎት ጀመረ፡፡


ሃዋሳ ጥር 20/2005 የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማሳካት የኢንዱስትሪውን ልማት ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት የልማታዊ ባላሃብቶች ተሳትፎ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለዉ የደቡብ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ገባኤ አስታወቁ ፡፡ በሃዋሳ ከተማ ከሰባት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጭ የተገነባው ዳሎል ኦይል የነዳጅ ማደያ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ምክትል አፌ-ጉባኤ አቶ ማሞ ጎዴቦ ማደያውን መርቀው ስከፍቱ እንደተናገሩት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት በግብርና፣ በከተማ ልማት፣ በኢንዱስትሪ፣ በመልካም አስተዳደር እንዲሁም በሌሎችመስኮች በክልሉ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ በየደረጃው ለተመዘገቡ ለውጦች መንግስታዊ አደረጃጀቶች፣ መላው ህብረተሰብ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የግል ባለሃብቶች በጋራ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል ። በተለይ ይላሉ አቶ ማሞ ሁሉም ዜጋ በሀገሪቱ ውስጥ በሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውስጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ መንግስት ያስቀመጣቸው ውጤታማ ፖሊሲዎችና ስትራቴጅዎች ለተመዘገበው ስኬት ቁልፍ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ በዚህም በክልሉ ከ1986 ወዲህ ከ68 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ ከአምስት ሺህ የሚበልጡ ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መሰማራታቸውንና ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠራቸው ተናግረዋል፡፡ የሃዋሳ ከተማ ባለፉት ጥቅት አመታት ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ የሀገራችን ከተሞች አንዷ መሆኗን የጠቆሙት አቶ ማሞ የግል ባለሃብቶች ከከተማው ዕድገት ጋር የሚጣጣም የልማት አቅርቦት እንዲኖር ከመንግስት ጎን በመሆን እያበረከቱት ያለው አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል ። የዳሎል ኦይል አክሲዮን ማህበር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደረጀ ዋለልኝ በበኩላቸው ኩባንያው ከአራት አመት በፊት በሰባት ኢትዮጵያዊን ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ካፒታል የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በርካታ አከሲዮኖችን ለህዝብ በመሸጥ ከ1ሺህ 230 በላይ ባለአክሲዮኖችያቀፈ ነዳጅና የነዳጅ ምርቶችን የሚያሰራጭ አገር በቀል ኩባንያ ነው ብለዋል፡፡ ኩባንያው በሃዋሳ አገልግሎት የጀመረውን ማደያ ጨምሮ በአርባምንጭ፣ በሃላባ፣ በአዲስ አበባ፣ በሰመራና በሌሎች አከባቢ ዘጠኝ ማደያዎችን በማስገንባት በየጊዜው እየተሻሻለ ለመጣው ለትራንስፎርት ዘርፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የነዳጅ ምርቶችን በማሰራጨት ላይ መሆኑን አመልክተዉ ከ580 ለሚበልጡ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡
http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=4934&K=1

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር