ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በይርጋዓለም ከተማ አዲስ ካምፓስ ከፈተ



ሀዋሳ (ኢዜአ)፦ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በይርጋዓለም ከተማ በ55 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው አዲሱ የአዋሳ ካምፓስ ትናንት ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ካምፓሱን መርቀው የከፈቱት የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የዩኒቪርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ናቸው፡፡
የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሴፍ ማሞ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት፤ የዩኒቨርሲቲውን የቅበላ አቅም ለማሳደግ ከሚካሄዱ የማስፋፊያ ግንባታዎች አንዱ አካል የሆነው አዲሱ የአዋሳ ካምፓስ በ65 ሄክታር ቦታ ላይ ያረፈ ነው፡፡
በ2002 ዓ.ም ተጀምሮ በአሁኑ ወቅት የተጠናቀቀው ይኸው ካምፓስ ለ800 ተማሪዎች የመኝታ አገልግሎት የሚሰጥ ዘመናዊ ህንፃ ፣ የመማሪያና ሌሎችም ክፍሎችን የያዘ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ካምፓሱ በአሁኑ ወቅት በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስና፣ በኮፕሬቲቭስ ዘርፍ በመጀመሪያ ዲግሪ የተቀበላቸውን 580 ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም በዚሁ አዲስ ካምፓስ በ38 ሚሊዮን ብር ወጪ የተጀመሩ የአስተዳደር ቢሮዎች፣ የተማሪዎች መመገቢያ፣ ቤተመጻሕፍትና የመምህራን መኖሪያ ግንባታ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ ዶክተር ዮሴፍ አመልክተው፤ የካምፓሱን የቅበላ አቅም በማገናዘብ ሌሎች የማስፋፊያ ግንባታዎች ለማካሄድ 320 ሚሊዮን ብር መመደቡን ጠቁመዋል፡፡
አዲሱን ካምፓስ እንዲከፈት ድጋፍ ላደረጉ ለክልሉ፣ ለሲዳማ ዞን፣ ለዳሌ ወረዳና ለይርጋዓለም ከተማ አስተዳደር፣ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡ 
የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ካምፓሱን መርቀው ከከፈቱ በኋላ እንደተናገሩት በአገሪቱ ከ21 ዓመት በፊት የቅበላ አቅሙ 3 ሺ ተማሪዎች ብቻ የሆነ አንድ ዩኒቨርሲቲ እንደነበር አስታውሰው አሁን በመገንባት ላይ ያሉትን ሳይጨምር የቅበላ አቅማቸው 100 ሺ የሆነ 31 ዩኒቨርሲቲዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
ወደ አዲሱ ካምፓስ የገቡት ተማሪዎችም በትምህርታቸው በርትተው ውጤታማ እንዲሆኑ የመስተዳድሩና የአካባቢው ማህበረሰብ ድጋፍ እንደማይለያቸው አቶ ሺፈራው አረጋግጠውላ ቸዋል፡፡
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች በበኩላቸው የካምፓሱ መከፈት ለልማት መሰረት የሆነውን የተማረ የሰው ሃይል ለማፍራት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድል ለመፍጠርና ልማትን ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልፀዋል፡፡
ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አዋዳን ጨምሮ በአምስት ካምፓሶች፣ በ8 ኮሌጆች እና በቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ36 የትምህርት ክፍሎች የተዋቀረ ሲሆን፤ በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት መርሐ ግብሮች 25 ሺ 250 ተማሪዎችን በመጀመሪያ፣ በሁለተኛና በዶክትሬት ዲግሪ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡
የቅበላ አቅሙን ለማሳደግ በሚያካሂደው የማስፋፊያ ግንባታ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመት መጨረሻ የተማሪዎች ቁጥር ወደ 30 ሺህ ለማድረስ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በምረቃው ሥነ ሥርዓት የካምፓሱ አዲስ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ መምህራን፣ የመስተዳድር አመራሮች፣ የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር