ኢትዮጵያ ከቡና ለማግኘት ያሰበችውን ገቢ ለማሳካት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ተቀናጅተው ለመሥራት ተስማሙ


አዲስ አበባ ህዳር 1/2005 ኢትዮጵያ ከቡና በዚህ ዓመት ለማግኘት ያሰበችውን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማሳካት በዘርፉ የተሰማሩ አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚያደርጉ የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቡና ጉባዔ ተሳታፊዎች አረጋገጡ። በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት የተካሄደው ጉባዔ ተካፋዮች በማጠናቀቂያቸው ላይ እንደገለጹት የአገሪቱ ቡና በዓለም ገበያ ባለው ተቀባይነትና በተለይም ስፔሻሊቲ ቡና ባለው ተፈላጊነት ምርቱን በጥራትና በብዛት በማቅረብ በዕቅዱ የተያዘውን ገቢ ለማሟላት የጋራ ጥረት ያደርጋሉ። አገሪቱ ለዓለም ያበረከተችውን ቡና አልምታ ልትጠቀምባቸው የምትችላቸው ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ተሳታፊዎቹ አመልክተው፣የቡናውን ልዩ ባህርያት በመመርኮዝ ልማቱንና ግብይቱን በማሳደግ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደሚቻል አስረድተዋል። ለዚህም ባለድርሻ አካላት ተገቢ ሚናቸውን እንዲወጡ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል። ጉባዔው በቡና ምርትና ግብይት ሂደት የተሰማሩ አካላትን በማሳበሰብ የኢትዮጵያን ቡና ሁኔታ የሚያሳውቅበት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን የቦርድ አባል አቶ ታደሰ መስቀላ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስረድተዋል። ጉባዔው በቡናው ዘርፍ ያሉትን ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች በስፋት በመዳሰስ በቀጣይ መከናወን ያለባቸውን ተግባራት ለመለየት የሚያስችሉ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደቀረቡበት አስታውቀዋል። ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ጉባዔው በየዓመቱ ኤግዚቢሽንና የመስክ ጉብኝትን በማካተት እስከ አራት ቀናት ቆይታ እንዲኖረው ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን አቶ ታደሰ ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ ኢትዮጵያ ጥራቱ የተጠበቀ ቡና ተከታታይነት ባለው መንገድ ማቅረብ በምትችልበት፣የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ያለዉ ሁኔታና የዘርፉን ስጋት መቀነስ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ በቡድኖች ተከፋፍለው ተወያይተዋል። ጥናት አቅራቢዎች ባቀረቧቸው ጽሁፎች እንዳመለከቱት ኢትዮጵያ ከቡና መገኛነቷ ባሻገር፤ልዩ ባህርያት ያለው ቡና ለገበያ በማቅረብ እያሳየች ያለቸውን መልካም ጅምር አጠናክራ መቀጠል እንዳለባት ያሳስባሉ። በተለይም ስፔሻሊቲ ቡናን በማቅረብ ገቢዋን የምታሳድግበት ሰፊ ዕድልም እንዳላት ከአሜሪካ ስፔሻሊቲ ቡና ማህበር ሚስተር ፒተር ጁሊያኖ ይናገራሉ።በደቡብ ክልል የይርጋ ጨፌና የሲዳማ ስፔሻሊቲ ቡናዎች ከፍተኛ ጥራት ያላቸው መሆናቸውንም መስክረዋል።የገላና ዓባያ ቡናም ተፈጥሮአዊነቱን ጠብቆ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። አዲስ አበባ ላይ ቀመሳው የተደረገው ቡና በጉዞና ተያያዥ ችግሮች ኒው ዮርክ(አሜሪካ) ላይ ተፈልቶ ሲቀመስ ጣዕሙን የመቀነስ ችግር እንደሚታይበትም አስረድተዋል።ሆኖም ተፈጥሮአዊነቱንና ጥራቱን ጠብቆ በማምረት ገበያውን በይበልጥ ሰብሮ በመግባት ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ሚስተር ጁሊያኖ አስረድተዋል። የሞንዴሌዝ ኢንተርናሽናል የዘላቂነትና የሀብት ሥራ አስኪያጅ ሚስተር አሽሊን ራሞልቻን በበኩላቸው ኩባንያቸው በሚያመርታቸው የቸኮሌት፣የብስኩትና ከዱቄት የሚሰሩ ለስላሳ መጠጦች ውስጥ ቡናን በግብዓትነት እንደሚቀጠም አመልክተው፣በዓለም በሁለተኛ ደረጃ በሚይዘው የቡና ግብይታቸው የኢትዮጵያ ቡና ያለውን ሚና ቀላል እንዳልሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡናን ባሉት ልዩ ባህርያት ምክንያት በኩባንያው ከፍተኛ ተፈላጊነት እንዳለው አመልክተው፣ቡናውን በብዛት ለመግዛት ጥራቱን ጠብቆ በዘላቂነት ማቅረብ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንተነህ አሰፋ በበኩላቸው ምርት ገበያው በ17 ከተሞች የሚያካሂደውን የቡና ግብይት ወደ ሌሎች ከተሞችም በማስፋፋት በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከምርቱ ለማግኘት የሚደረገውን ዕቅድ ለማሳካት ጥረት እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል። ምርት ገበያው ጥራትና ብዛት ያለው ቡና ለገበያ ለማቅረብ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በአዳዲስ አሰራሮች ጭምር ለማገዝ ዝግጁ መሆኑንና በዚህም ስፔሻሊቲ ቡናን በቀጥታ ለመግዛት የሚያስችል ግብይት እንደሚጀምር ለተሳታፊዎቹ ባደረጉት ገለጻ አስረድተዋል። ''የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኢትዮጵያ ቡና ላይ ተጨማሪ እሴት ለማከልና ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆን ይሰራል'' ሲሉም አቶ አንተነህ ተናግረዋል። የካሪቡ ኮፊ የቡናና ሻይ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቻድ ትሬዊክ አገሪቱ የጫካ ቡናዋን ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነቷን በይበልጥ የምታሳድግበት ዕድል እንዳለ አመልክተዋል።የኢትዮጵያን የጫካ ቡና እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2004-06 ባሉት ዓመታት መጎብኘታቸውን አስታውሰው፣ምርቱን ሕጋዊ የምስክር ወረቀት እንዲያገኝ በማድረግና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚቻል ያስረዳሉ። የስታር ባክስ ተወካይ ሚስተር አርተር ካሩሌትዋ በበኩላቸው ኩባንያቸው ለኢትዮጵያ ቡና ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለውና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ የሚቀርበውን ቡና ለመግዛት ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል። ለሁለት ቀናት የተካሄደውን ጉባዔ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተር አሶሴሽን፣የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት(ዩ ኤስ ኤይድ)ና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር