ኢትዮጵያ ለምታስተናግደው ዓለም አቀፍ የቡና ጉባዔ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ ነው


አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2005 ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንትለመጀመሪያ ጊዜ ለምታካሂደው ዓለም አቀፍ የቡና ጉባዔ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን የቦርድ አመራር አባላት አስታወቁ። የቢርዱ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ እመቤት ታፈሰና የቦርድ አባሉ አቶ ታደሰ መስቀላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በአዲስ አበባ ከተማ ለሚደረገው ጉባዔ ዝግጅቱ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል።ጉባዔው አገሪቱ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን፤የተለየ ጣዕምና ማንነት ያለው ቡና ባለቤት መሆኗንም ለማሳየት ያስችላል። በጉባዔው 250 የሚደርሱ ተሳታፊዎች ከውጭና ከአገር ውስጥ እንደሚሳተፉበትም አስረድተዋል። በጉባዔው የዓለም አቀፍ ቡና ድርጅት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሚስተር ሮቢዬሮ ኦሊቬራ ሲልቫ፣ታዋቂ የቡና ገበያ ድርጅቶች ኃላፊዎች፣በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት ልዑካን ቡድንና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅት ኃላፊዎች እንደሚገኙም ገልጸዋል። ማህበሩ ከንግድ ሚኒስቴርና ከሌሎች አግባብ ካላቸው አካላት ጋር በመቀናጀት በሚያስተናግደው ጉባዔ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚገባ በማስተዋወቅ የተሻለ ገቢ የሚገኝበትን መንገድ ለመፍጠር ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል። ጉባዔው ቡና አምራቾችን፣አቅራቢዎችን፣በምርትና በግብይት ሂደት ውስጥ የሚሳተፉ ሌሎች አካላትን በማሰባሰብ አገሪቱ ከምርቱ በይበልጥ ተጠቃሚ የምትሆንበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚያስችልም የቦርድ አመራር አባላቱ አስታውቀዋል። በተጨማሪም በቡና ምርትና አቅርቦት ዘርፎች የሚታዩ ችግሮችን የሚያቃልሉ ጥናታዊ ጽሁፎች እንደሚቀርቡበትም ተናግረዋል። ጉባዔው ከሌሎች አገሮች ጋር እየተደባለቀ የሚቀርበውን የአገሪቱን ቡና ችግሮች ለመፍታት እንደሚያስችል ኃላፊዎቹ እምነታቸውን ገልጸዋል። በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከቡና ምርት ለማግኘት የታቀደውን 220ሺህ ቶን ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማስገኘት ለተያዘውን ግብ ለመምታት ያስችላል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል። ማህበሩ ወደፊት በየዓመቱ ወይም በየሁለት ዓመቱ የቡና ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት የአገሪቱን ቡና በይበልጥ ለማስተዋወቅ ማቀዱንም ኃላፊዎቹ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያ በቡና ምርትና በውጭ ገበያ አቅርቦት ከአፍሪካ አንደኛ ደረጃ የያዘች ሲሆን፣ከዓለም በምርት በአምስተኛ ደረጃ በውጭ ገበያ አቅርቦት ደግሞ ሰባተኛ ደረጃ መያዟን መረጃዎች ያመለክታሉ። የኢትዮጵያ ኮፊ ኤክስፖርተርስ አሶሴሽን ከ40ዓመታት በፊት የተቋቋመ ማህበር ነው።
http://www.ena.gov.et/story.aspx?ID=3193

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር