ደቡብ ግሎባል ባንክ በይፋ ሥራ ጀመረ



አዲስ አበባ፡- በ266 ሚሊዮን 964 ሺ ብር የተፈረመና በ138 ሚሊዮን 901 ሺ 836 ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመው ደቡብ ግሎባል ባንክ በይፋ ተመርቆ ሥራ ጀመረ።
ባንኩ በአዲስ አበባ በተለምዶ በቅሎ ቤት በሚባለው ስፍራ በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ትናንት ተመርቆ በተከፈተበት ወቅት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ወርቁ ለማ እንደገለጹት፤ ባንኩ በ5ሺ 481 ባለ አክሲዮኖች የተቋቋመ ነው።
ባንኩ የተከፈለ ካፒታል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተው፤ ከነሐሴ 22 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ለደንበኞቹ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በባንክ ዘርፉ ያለው ውድድር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ ውድድሩን ለማሸነፍ ባንኮች አሰራሮችን ለማሻሻል የቅርንጫፉችን ቁጥር መጨመርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በአስፈላጊው ደረጃ ጥቅም ላይ ማዋላቸውን ገልፀዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ ባንኩ በወቅቱ ያለውን የውድድር ሁኔታ አሸናፊ ሆኖ በስኬት ጐዳና እንዲራመድ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት አቅዷል። ዘመናዊ የባንክ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት የካርድና ኢ-ባንኪንግ አገልግሎቶች ለመስጠት ተዘጋጅቷል። 
ባንኩ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ቅርንጫፎችን ለመክፈት መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ በሚቀጥለው ሳምንት የሐዋሳና ሆሳዕና ቅርንጫፎች ሥራ እንደሚጀምሩ አመልክተዋል።
የደቡብ ግሎባል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኑረዲን አውል በበኩላቸው በዕለቱ እንደገለጹት፤ ባንኩ በሥራ ላይ ባለው የመንግሥት ፖሊሲ ላይ በመመርኮዝ ለኢንቨስትመንትና በንግድ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ጥረት ለመደገፍና ለባለአክሲዮኖች ተገቢውን ጥቅም ለማስገኘት የተቋቋመ የግል ባንክ ነው።
መንግሥት የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ውስጥ ሰፊ ድርሻና ተሳትፎ እንዲኖረው እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የባንክና የፋይናንስ ዘርፍም በመንግሥት በተቀመጠለት ምቹ ፖሊሲ ተመርኩዞ ፈጣን ዕድገት እያሳየ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መኮንን ማንያዘዋል የፋይናንስ ዘርፍ ለአንድ አገር ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ገልጸው፤ የአገሪቷ ባንኮች የበለጠ ቀልጣፋ ተደራሽና ፈጣን ዕድገት እንዲያስመዘግቡ መንግሥት የሚያወጣቸውን ፖሊሲዎችን አውቀው መተግበር እንዳለባቸው አመልክተዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው መንግሥት ባስቀመጠው ፖሊሲ ተጠቅመው ዜጐች በፋይናንስ ሴክተር ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። የደቡብ ክልል መንግሥት ዘርፉን ለማበረታታት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አመልክተዋል።
ባንኩ በተያዘው የበጀት ዓመት በመላው አገሪቱ 10 ቅርንጫፎችን ለመክፈት ማቀዱንም በዕለቱ ተገልጿል።
http://www.ethpress.gov.et/ethpress/main/news.php?newsLocation=home&newsInstruction=more&newsId=9537

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር