የመለስ ሕልፈት በኢሕአዴግ ጫንቃ ላይ የሚያሳርፈው ታላቅ ሸክም አለ


በክንፈ ኪሩቤል ተስፋሚካኤል
የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግናዬ ነው የሚለው መሪውን መለስ ዜናዊን በሞት ካጣበት ቀን ጀምሮ አክብሮቱንና ፍቅሩን በታላቅ ሐዘንና እንባ ገልጿል፡፡ መለስ ላይመለስ አርፎአል፡፡ ዕድሜውን ሙሉ ዕረፍት ወስዶ አያውቅምና፡፡ ብዙዎች እንደ ተዝናኑት አልተዝናናም፡፡ እርግጥ ነው ሥጋዊ ደማዊ ለሆነ ሰብዓዊ ፍጡር ሁሉ ሞት አይቀሬ ነው፤ ምድራዊ ሥልጣን ዘለዓለማዊ አይደለም፡፡ ገንዘብ፣ ሀብትና ንብረትን ትቶ መሰናበት የግድ ነው፡፡ ነገር ግን ለአገር፣ ለወገንና ለሕዝብ ታላቅና አኩሪ ሥራ ሠርቶ ማለፍ ግን ክብር ነው! ሲዘከርም ይኖራል፡፡

ኢሕአዴግ ታላቅና ፈታኝ ሁኔታ ከፊቱ ተደቅኖበታል ሆኖም ግን ጥበብና ማስተዋል፣ ትዕግሥትና እርጋታ በተሞላበት እንዲሁም ጨዋነትና ይቅርባይነት በታከለበት መንገድ አመራሩን ከቀጠለ ሁሉንም መሰናክል ማለፍ ይቻለዋል፡፡ አቶ መለስ በትግሉና ከትግሉ በኋላ ራሳቸውን በኢኮኖሚክስና በማኔጅመንት ትምህርቶች አስተምረው ዕውቀትን ያገኙና ለአገራቸው ዕድገት የቀሰሙትን ዕውቀት ወደ ተግባርም የለወጡ ሰው ነበሩ፡፡ ስለ መለስ የአዕምሮ ችሎታ የሚወዷቸው ቀርቶ የሚጠሏቸው እንኳን አይክዱትም፡፡ ይህንን አይነት ሰው መተካት ለጊዜውም ቢሆን ይከብዳል፡፡

ስለ መለስ ባህርይ እንዲሁም ስለ ሥራዎቻቸው ጠንካራና ደካማ ጎን እንዲሁም ስለ ትክክለኛ ውሳኔያቸውና ስለ ስህተቶቻቸው የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች ወደ ፊት ይጽፉታል ብሎ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፡፡ ሆኖም ግን ለአንባብያን ማስታወስ የሚፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይህ ጸሐፊ ከወራት በፊት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ያሰፈረው ጽሑፉ በአጭሩ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹በተለይ አሁን እንደሚታየው ብዙዎቹ የአገሪቱ ቁልፍ መሪዎች በዕድሜ እየገፉ ናቸው፡፡ ብዙዎቹም በሥራ ድካምና በሕመም ያሉ ይኖራሉ፡፡ አንዳንድ ተንታኞች እንደሚሉት በተለይ ቁልፍ የሆነው መሪ በድንገት በሞት ቢለይ በሚፈጠረው የሥልጣን ክፍተት አጋጣሚ የውጭና የውስጥ ሊበራል ኃይሎች (የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ማለት ነው)፣ በሩቅም ሆነ በቅርብ ሆነው አሁን እያኮላሹትና ግራ እያጋቡት ያለውን ይህንን ተተኪ ትውልድ መጠቀሚያ በማድረግ (የትርምስንና የብጥብጥ ሁኔታን በመፍጠር) አገሪቱን ወደ አልታሰበ ወታደራዊ ግጭት ሊያስገቡ ይችላሉ፡፡ ምናልባትም ለምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት በር የሚከፍትና እጁን ለስውር ቅኝ ተገዢነት የሚሰጥ መንግሥት ሊመሠርቱ ይቻላቸው ይሆናል የሚሉ ጥርጣሬዎች አሉ፡፡ ይህ እንዳይሆን የሚከለክላቸው ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲና የተደራጀ ሕዝባዊ ኃይል የለም ይላሉ ተንታኞቹ፡፡ መላምት ሊሆን ይችላል፤ ላይሆንምም!››

ከላይ እንደተገለጸው የአገራችን መሪ ባልተገመተና ባልተጠበቀ ሁኔታ በድንገት ተለይተውናል፡፡ የመለስ የጤና ጉዳይ መባባስና የመሞት ጉዳይ የታየው ከቅርብ ወራት በፊት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጠሩት የቡድን ስምንት አገሮች የዋሽንግተን ስብሰባ ከተገኙ በኋላ የመሆኑ ጉዳይ በጥንቃቄ ሊጤን ይገባዋል፡፡ የእዚህን ጽሑፍ አቅራቢ ትኩረት የሳቡና ጥርጣሬ ውስጥ የከተቱት ሁለት ሁኔታዎች አሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስከሬን ገና አፈር ሳይነካው የሽግግር መንግሥት ምክር ቤት መሥርተናልና ዕውቅና ይሰጠን በማለት በዋሽንግተን ከተማ ተገኝተው ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ማመልከቻ ያቀረቡ ተቃዋሚ ተብዬዎች ጉዳይ አንዱ ነው፡፡

ሌላው በተጨማሪ የሚገርመው መሪያችን የነበሩትን አቶ መለስ ሕዝባቸው ገና አልቅሶ ሳይቀብራቸው ይተኳቸዋል የተባሉት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሹመታቸው በይፋ በፓርላማ ሳይፀድቅ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አብሮ ስለ መሥራት፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ ሒደቶች፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ልማትና ደኅንነት ጉዳይ ከወዲሁ በስልክ  ማነጋገራቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን መደመጡ ነው፡፡ ሚስተር ኦባማ ይህንን ማድረጋቸው ምን ፈልገው ይሆን? ለምን ተቻኮሉ? ይህ ሁኔታ ከአስገራሚነቱ ባሻገር ጥርጣሬን የሚያሳድር ነው፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናዊ ታሪኳ እንደ አሁኑ ያለ ፈታኝ ወቅት ገጥሟት አያውቅም፡፡ ከዘመናት የእንቅልፍ ሰመመን ነቅታ ካደጉት አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ዕርምጃ በጀመረችባቸው ጥቂት ዓመታት ውስጥ እያሳየች ያለችውን ዕድገት በበጎ የማይመለከቱ የቅርብም ሆኑ የሩቅ መንግሥታት ስለ መኖራቸው አያጠራጥርም፡፡ በተለይ በሊበራል አስተሳሰብ እንመራለን የሚሉት የምዕራብ መንግሥታት ራሳቸው እንኳን በአግባቡ በማይተገብሩት የዴሞክራሲ መርህ እያሳበቡ፣ በአፍሪካ ዕድገት ላይ ሲያሳድሩት ስለኖሩት አሉታዊ ተፅዕኖ መካድ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ የምዕራባውያን አጀንዳ አፍሪካን ማሳደግ እንዳልሆነ ሳይታለም የተፈታ ነውና፡፡

አሁን ያለው ታላቅ አገራዊ አጀንዳ በአገራችን እስካሁን የተጀመሩትንና ቀጣይ ሥራዎችን  አጠናክሮ የሚያስቀጥልና የሚያስጠብቅ እንደ መለስ ጠንካራ መሪ አሁን ልናገኝ ባንችልም፣ ለጋራ ራዕይ መቆም ከቻልን ግን ካሰብንበት መድረስ ይቻላል፡፡ ቀጣዩን የመንግሥት ሥራ ፈር ለማስያዝ ከሁሉ በላይ  ለአገራቸው ሰላም፣ ዕድገት፣ ልማትና ብልጽግና የሚቆሙ በውስጥና በውጭም ያሉ ወገኖችን ማሰባሰብ ወቅቱ የሚጠይቀው ታላቅ ኃላፊነት ነው፡፡ 

ከመለስ ሞት ወዲህ የአገራችን ሕዝብ ያሳየው ጨዋነት፣ ታጋሽነት፣ ዕንባና ሐዘን ከልብ የመነጨ ለመሆኑ ለወዳጅ መፅናናትን ለጠላት ደግም ኃፍረትን አከናንቦአል፡፡ ይህ ዕንባ ለኢሕአዴግ አመራር ደግም ታላቅ ሸክምንና አደራን ጥሎበታል፡፡ ሕዝቡ ዕንባውን በከንቱ አላፈሰሰም፤ ቢያንስ መሪውን ገምግሞ ለሕዝቡ አሳቢ ነበር በማለት ተቀብሏልና፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ የኢሕአዴግ አመራር ሕዝብን የሚያጉላላ ቢሮክራሲን ሊሸከም አይገባውም፡፡ ሙስናን መግታት አለበት፡፡ የመንግሥት ቢሮዎች ሕዝብን በቅንነት ለማገልገል መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ሕዝቡ ለሰላሙና ለመብቱ በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉለትን መብቶች ማስከበር ይገባዋል፡፡ ይህ ታላቅ ሕዝብ ለብዙ ሺሕ ዘመናት አብሮ በመኖር ያዳበረውን ሥርዓቱን፣ ባህሉን፣ ወጉን፣ ሃይማኖቱን፣ መከባበሩንና መቻቻሉን በመጠበቅ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ተግባር በማከናወን ዕድገቱን ማፋጠን ይኖርበታል፡፡

ኢሕአዴግ ዘመነ ህዳሴው እንዲሰምርና የታቀደው መርሐ ግብር እንዲሳካለት ከፈለገ ማድረግ ያለበት በመጀመሪያ ህዳሴውን ከራሱ በመጀመር የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ለውጥ አራማጅ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ በውስጥም በውጭም የሚገኙትንና በዕውቀት የበለፀጉትን የአገሪቱን የተማሩ ዜጎች ክህሎት፣ ልምድና ችሎታ ከጥቅም ላይ የሚያውሉበትን ሁኔታ መፍጠር፣ ገንቢ ትችትን ማዳመጥና መቀበል፣ ሕዝባዊ ኃይልን ማሰባስብ፣ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት የጭንቅ ኑሮውን ለማቃለል ተገቢ ፖሊሲዎችን መንደፍ፣ ትክክለኛ ዕርምጃዎችን መወሰዳቸውንና ተግባራዊነታቸውን መቆጣጠር፣ ተጠያቂነትን ማስፈን፣ የሕዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር እንዲሁም ተጠቃሚ እንዲሆን ሁኔታዎችን ማመቻቸት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህ ቢደረግ የኢትዮጵያ ህዳሴና መፃዒ ሁኔታ ብሩህ ሊሆን ይችላል፡፡

ሕዝቡ ኑሮው አልከበደውም ማለት አይቻልም፤ አልተበደለም አይባልም፡፡ ጥቂቶች የአገሪቱን ሀብት በመዳፋቸው ውስጥ ስለ ማስገባታቸው፣ የመንግሥትን ንብረትና ሀብት ዘረፋና ሙስና መስፋፋቱ ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ስለመሆኑ መካድ አይቻልም፡፡ የመለስን ራዕይ ለማሳካት በቁርጠኝነት ከተወሰነ ግን ኢሕአዴግ የሕዝብን ብሶትና ጩኸት ችላ ማለት አይገባውም፡፡ ይልቁንም ከምንጊዜውም በላቀ ሁኔታ የሕዝብን ድምፅ ለማዳመጥ ዝግጁ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለአገራቸው ተቆርቋሪ የሆኑትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአገሪቱ ጉዳይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የግድ ይላል፡፡

ኢሕአዴግ ራሱን በህዳሴ በመቀየር የተነሻሽነት መንፈስ ማሳየት አለበት፡፡ የድርጅቶች ስብስብ ሆኖ ከመቀጠል ይልቅ ወደ ፓርቲነት ራሱን ለማሳደግ ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ለጥቅም ብቻ ሲሉ የገቡትን መለየት ይገባዋል፡፡ በተለይ በዚህ ተለዋዋጭ ዓለም የምናያቸውና የምንሰማቸው የዕለት ተዕለት ሁኔታዎች የሚያስገነዝቡን ነገር ቢኖር የሕዝብ ቅሬታዎች ሲከማቹ ወዳልተፈለጉና ወዳልተጠበቁ አቅጣጫዎች ሊያመሩ እንደሚችሉ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ እጃቸውን በአገሪቱ ጉዳይ ጣልቃ ለማስገባት ለሚያደቡ የውጭ ኃይሎች እንዳንጋለጥ ሕዝቡ በአገሩ ጉዳይ ላይ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ ከግል ሥልጣን በላይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በማሰብና በመሥራት የማይናጋ መሠረትን መጣል ይቻላል፡፡ መለስ ዜናዊ ያደረጉት ይህንን ነበር፡፡

ኢሕአዴግ የኢትዮጵያን ህዳሴ ለማሳካት እንዲቻለው ያለበትን ሁኔታ በጥልቀት ይመርምር፡፡ ኢሕአዴግ ደጋግሞ ያስተውል፡፡ ይህ ታላቅ ሕዝብ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት አሳይቶት የነበረውን አገር ወዳድነትና ከኢሕአዴግ መንግሥት ጋር የመቆሙን ጉዳይ መለስ ብሎ ይመልከት፡፡ ቀጥሎም በዓባይ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያሳየው ቁርጠኛ አቋምና አሁንም በሞት በተለየው መሪው መለስ ዜናዊ ምክንያት እያሳየ ያለውን ሐዘንና ቁጭት ያጢን፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን ሕዝባዊ ማዕበል በብልህነትና በማስተዋል በመጠቀም አመራር መስጠት ይገባዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀር ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይጥሉሃል›› የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዳይደርስ መጠንቀቅ ይገባል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር