በሃዋሳ ነጋዴዎች የሞባይል ካርድ ከታሪፍ በላይ እየሸጡ ነው


ሀዋሳ (ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌ ኮም በተመን የሚያከፋፍለውን የሙባይል ካርድ የሀዋሳ ከተማ ነጋዴዎች ከታሪፍ በላይ እየሸጡ መሆኑን አንዳንድ የቴሌ ደንበኞች ገለጹ፡፡
ኢትዮ ቴሌ ኮም በበኩሉ «ከታሪፍ በላይ መሸጥ ወንጀል በመሆኑ እርምጃ እየወሰድኩ ነው» ብሏል፡፡ ፖሊስ ደግሞ ድርጊቱን ሲፈፅሙ የተገኙትን ተከታትሎ በህግ እንደሚጠይቅ አመልክቷል፡፡
በከተማው ከሚገኙ የቴሌ ደንበኞች መካከል አቶ አብነት ደሜ፣ አቶ ሞገስ አይሶና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሙሉ አበበ ከትናንት በስቲያ በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮ ቴሌ ኮም በተመኑ ለነጋዴዎች የሚያከፋፍለው የሞባይል ካርድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከታሪፍ በላይ እየገዙ ነው።
ነጋዴዎቹ ከታሪፍ በላይ የሚሸጡት ባለ አምስት ብሩ ላይ 50 ሳንቲም በመጨመርና ዋጋቸው ከፍ ባሉት ካርዶች ላይ ደግሞ የአንድና የሁለት ብር ጭማሪ በማድረግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ተጠቃሚዎቹ «ለምን?» ብለው ሲጠይቁ፤ «ብትፈልጉ ግዙ አለበለዚያ መተው ትችላላችሁ» የሚል ምላሽ እንደሚሰጧቸው አመልክተው፤ አማራጭ አጥተው በተባሉት ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡
የሞባይል ካርድ ከቴሌ ተረክበው ከሚሸጡት መካከል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንዳንድ ነጋዴዎች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ በተመኑ እንደሚሸጡ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሪፖርተር ተዘዋውሮ እንደታዘበው ግን ነጋዴዎቹ ከተመን በላይ እንደሚሸጡ አረጋግጧል፡፡
የኢትዮ ቴሌ ኮም የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱራሂም አህመድ ስለጉዳዩ በስልክ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፤ «ማንኛውም ነጋዴ ከቴሌ በተመኑ የተረከበውን የሞባይል ካርድ ላይ በገባው የውል ስምምነት መሰረት ኮሚሽን ያለው ሲሆን ከታሪፍ በላይ መሸጥ ግን ወንጀል ነው» ብለዋል፡፡
በሌሎችም አንዳንድ ከተሞች ነጋዴዎቹ የገቡትን ውል ተላልፈው ከታሪፍ በላይ ሲሸጡ የተገኙ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያና ፈቃዳቸውን እስከ መሰረዝ የደረሰ እርምጃ መወሰዱን አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም ከቴሌ በጅምላ የሚውስዱትም ሆነ ማናቸውም ቸርቻሪ ነጋዴ ከተመን በላይ ሲሸጥ ከተገኘ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡
ደንበኞችም ከታሪፍ በላይ ተላልፈው የሚሸጡትን በአቅራቢያቸው ለሚገኘው ቴሌ ጽህፈት ቤትና ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት ፈጣን ምላሽ ማግኘት እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡
የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ የወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ባለሙያ ምክትል ሳጂን ደጀኔ አሰፋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የሞባይል ካርድ ከታሪፍ በላይ የሚሸጡትን ከቴሌ ጋር በመተባበር ተከታትሉ በህግ ለመጠየቅ ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር