በሐዋሳ ከተማ ህገወጥ ነጋዴዎችና ፖሊሶች ሲታኮሱ አደሩ


የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ሐዋሳ፣ ባለፈው ረቡዕ ምሸት ፖሊሶችና የኮንትሮባንድ ነጋዴዎች ሲታኮሱ አደሩ፡፡ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማወቅ ባይቻልም አንድ ህፃን መቁሰሉን የክልሉ ፖሊስ አስታውቋል፡፡በከተማው ሐይቅ ዳር ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘውና በተለምዶ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ፣ ባለፈው ረቡዕ ከምሽቱ 4፡30 ላይ የተጀመረው የተኩስ ልውውጥ እስከ ሌሊቱ ስምንት ሰዓት ድረስ ቀጥሎ መቆየቱንና በዚህ ምክንያትም የተመቱና የቆሰሉ ሰዎች በአዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና ሲደረግላቸው እንደቆዩ ምንጮች ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡
የተኩስ ልውውጡ መንስኤ ከኮንትሮባንድ ንግድ ጋር የተገናኘ መሆኑን የገለፁልን የክልሉ የወንጀል መከላከል ዋና የሥራ ሂደት ባለቤት ኮማንደር በላይነህ በላይ፤ በህገወጥ መንገድ የገቡና የተከማቹ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች እንዳሉ ለፖሊስ ጥቆማ ደርሶት ወደ ስፍራው እንደሄዱ ተናግረዋል፡፡ ቦታው ሲደርሱ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎቹ ያደራጇቸውና ኮንትሮባንድ ዕቀዎቹን በመጫን፣ በማውረድና በመበለት ሥራ ላይ የተሰማሩ ወጣቶች በጉምሩክ ሠራተኞችና በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ መሞከራቸውን ኮማንደር በላይነህ ገልፀዋል፡፡ በህገወጥ ነጋዴዎቹ የተደራጁት ወጣቶች፣ መሣሪያ ታጥቀው ነበር ያሉት ኮማንደሩ፤ በፀጥታ ኃይሎቹና በጉምሩከ ሠራተኞቹ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ለማድረስ ከመሞከራቸውም በላይ ኦፕሬሽኑን ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን በሄደው የፌደራል፣ የክልሉና የከተማው የፀጥታ ኃይሎችና በጉምሩክ ሠራተኞች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ጠቁመው፤ በተኩስ ልውውጡ ከየትኛው ወገን እንደተተኮሰ ባልታወቀበት ሁኔታ አንድ ህፃን መቁሰሉን ገልፀዋል፡፡ ከችግሩ ጋር በተያያዘ 40 የሚደርሱ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው የማጣራት ሥራ መከናወኑን የተናገሩት ኮማንደር በላይነህ፤ ከተያዙት ሰዎች አብዛኛዎቹ ጉዳያቸው ተጣርቶ መለቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ክልል ፖሊስ፣ ከፌደራሉና ከከተማው የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ባካሄደው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር የዋለውና 10 መጋዘን ሙሉ ነው የተባለው ኮንትሮባንድ ዕቃ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን መደረጉንም ኮማንደሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
http://www.ethiopianreporter.com/news/293-news/5639-2012-03-17-10-45-16.html

ተጨማር ዜና



•    ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልባሽ ጨርቅ በቁጥጥር ሥር ውሏል
በአስፋው ብርሃኑ፣ ልዩ ዘጋቢ ከሐዋሳ
መጋቢት 5 ቀን 2004 ዓ.ም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ በሐዋሳ ከተማ ዓረብ ሰፈር አካባቢ ለአራት ተከታታይ ሰዓታት በጉምሩክ ፖሊሶችና በኮንትሮባንዲስቶች መካከል በነበረው የተኩስ ልውውጥ ስድስት ሰዎች ቆሰሉ፡፡ የተኩሱ መንስዔ የሆነው በልባሽ ጨርቅ የተሞሉ በርካታ የኮንትሮባንድ ቦንዳዎች በሐዋሳ ከተማ አሮጌው ገበያ ውስጥ ባለው አንድ መጋዘን ተደብቀው በመገኘታቸው ነው፡፡ የፌደራል ፖሊስ ዕቃዎቹን ለማውጣት ሲሞክር በአካባቢው በነበሩ ሰዎች የድንጋይ እሩምታ በመለቀቁ እንደሆነ በወቅቱ በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ያልጠበቁት ነገር የገጠማቸው ፖሊሶች ተጨማሪ ኃይል ጠይቀው ለመከላከል ቢሞክሩም፣ የኮንትሮባንዲስቶቹ ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች ያለማቋረጥ የድንጋይ ውርወራ በማድረጋቸውና መሣሪያ የታጠቁም ተኩስ በመጀመራቸው እንደሆነ አስተየየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡

በገበያው አካባቢ የሻይ ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ መሐመድ ነስረዲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የተጀመረው ተኩስ ያለማቋረጥ እስከ ሌሊቱ 7፡00 ሰዓት ድረስ ቀጥሏል፡፡ ‹‹መሰል የተኩስ እሩምታ በሕይወቴ ያየሁት በ1983 ዓ.ም ደርግ የወደቀ ጊዜ ነው፡፡ ቢሆንም የዚያን ቀን የምሽቱ ተኩስ የተለየ ነው፡፡ በአንዴ አካባቢው ሩዋንዳ መሰለ እኮ፤›› በማለት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፖሊሶቹ በአካባቢው በብዛት የወጣውን ሕዝብና ኮንትሮባንዲስቶቹን መለየት ተስኖዋቸው የተቃውሞ ሠልፍ በመምሰሉ አስለቃሽ ጭስ መጠቀማቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ከቆሰሉት ስድስት ሰዎች መካከል አንድ ሕፃን እንደሚገኝበት፣ በወቅቱ የነበረው አዝማሚያ ከተማውን ለኹከት ያጋለጠ እንደነበረ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በሐዋሳ ከተማ ሰልባጅ ገበያ መሀል በጠራራ ፀሐይ በፖሊሶችና በኮንትሮባንዲስቶች መካከል ለ1፡00 ሰዓት የቆየ ግርግር ተከስቶ እንደነበረ የሚያስታውሱት የዓረብ ሰፈር ነዋሪዎች፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኬላዎችን መቆጣጠር ተስኖታል ወይም ፈታሾች አካባቢ ችግር አለ በማለት ባለሥልጣኑ ራሱን ቢያጠራ ይሻለዋል የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በሐዋሳ ገበያ ማናቸውም ሸቀጦችና ዕቃዎች በየመደብሩ ጥበቃ ተመድቦላቸው እንደሚያድሩና በተፈጠረው ግርግር ገበያውን የመዝረፍ አዝማሚያ ስለነበር፣ ፖሊሶቹ ያንን ድርጊት ለመከላከል ጥረት እንዳደረጉ ትዕግሥቱ ረድኤት የተባለ የአካባቢው ባለቡቲክ ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡

በምሽቱ ስለተፈጠረው ሁኔታ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሐዋሳ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያሬድ ፈቃደን ተጠይቀው፣ ‹‹በሐዋሳ ከተማ ገበያ ውስጥ የተከማቸ የኮንትሮባንድ ዕቃ መኖሩን ባለን መረጃ ከክልሉ፣ ከፌደራልና ከከተማው አስተዳደር ፖሊስ ኃይል በማቀናጀት ወደተባለው ክምችት ልንገባ ስንል፣ ኮንትሮባንዲስቶቹ ያዘጋጇቸው ምንም የማያውቁ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወርና ኹከት በመፍጠር የመከላከል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የተኩስ ልውውጥ ተደርጓል፤›› ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የታጠቁ ኮንትሮባንዲስቶችም ስለነበሩ ወደ ላይ እየተኮሱ ከተማዋን ለመረበሽ ፈልገው ነበር፡፡ እኛ የማንለቃቸው መሆኑን ሲያውቁ ወደ ሌሎች የከተማ አካባቢዎች እየሄዱ በተኩስ ሕዝቡን ለማነሳሳት ጥረት አድርገው ነበር፤›› በማለት በምሽቱ የነበረው የተኩስ ልውውጥ ለማንኛውም ነዋሪ አስደንጋጭ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ልባሽ ጨርቆችና 10 ኩንታል ቡና ተይዞ ጉዳዩ እየተጣራ መሆኑን ታውቋል፡፡ ኬላዎች አካባቢ ልል የሆነ ፍተሻ አለ ስለመባሉ እንደማይስማሙበት ሲገልጹ፣ ‹‹በመሰል ተግባር የተሰማሩ ሰዎች በጠራራ ፀሐይ እንደማይፈጽሙና በገጠር ጋሪና አህያ ተጠቅመው እንደሚያሻግሩ በርካታ ጊዜ ደርሰንባቸዋል፡፡ የዚያን ምሽት ዕርምጃ የዚህ እንቅስቃሴ አካል ነው፤›› ብለዋል፡፡ በወቅቱ የደረሰ አደጋ ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ ፈቃደ፣ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ አደጋ እንዳይደርስ የፖሊስ ኃይሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረጉ ምንም ዓይነት አደጋ አልተፈጠረም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ድንገተኛ ጦርነት የተፈጠረ የመሰላቸው የሐዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተኩሱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ሳይተኙ ለሊቱን እንዳጋመሱ ለማወቅ ተችሏል፡፡   

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር