ማንን እንስማ፦ ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ገለጹ፤ የዓለም ምግብ ድርጅት ፋኦ በበኩሉ በኣገሪቷ ከ2 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል ይላል
የዜናው ምንጭ፦ www.ena.gov.et
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2006 ኢትዮጵያ በሁለት አሥርት ዓመታት ውስጥ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በአገር አቀፍ ደረጃ በምግብ ራሷን መቻሏን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተከበረው 23ኛው የግንቦት 20 የድል በዓል የማጠቃለያ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት ባለፉት 20 ዓመታት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጡ ፕሮግራሞች ተግባራዊ በመሆናቸው ስኬታማ ውጤት ተመዝግቧል።
ከሦስት ዓመታት በፊት የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገሮች ባለፉት ስድስት አሥርታት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በድርቅ ክፉኛ ተመተው እንደነበር አስታውሰው፣ ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት ያለአንዳች መሰናክል ችግሩን ማለፏን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከ23 ዓመታት አገሪቱ ከነበረችበት ከፍተኛ ተመጽዋችነት በመውጣት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በዓመት ከ250 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማምረቷንም አቶ ኃይለማርያም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አርሶ አደሩ ከፍተኛ ገቢ ወደሚያስገኙ ምርቶች መሸጋገሩንና በቀጣይም ጠንካራ አገር በቀል ባለሃብቶችን በማፍራት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ ጥረት ይደረጋል።
ለሁለት አስርት ዓመታት በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግልም አገሪቱ በዓለም ኅብረተሰብ ዘንድ ትታወቅበት ከነበረው ረሃብና ጉስቁልና በመውጣት ከኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላትም የረሃብተኝነት ምሳሌ መሆኗ እንዲፋቅ መደረጉን ተናግረዋል።ይህም ለኢትዮጵያውያን ታላቅ እመርታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ከሚፈለገው ምርታማነትና የብልፅግና ደረጃ ለመድረስና ግሎባላይዜሽን የደቀነውን የውድድር ፈተና በብቃት ለማለፍ ዜጎች ከመንግስት ጎን በመቆም አስተዋጽኦቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በዘመነ ደርግ በግለሰብ ደረጀ ከ500 ሺህ ብር ካፒታል በላይ ማንቀሳቀስ የማይቻልበት ወቅት እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፣ ከግንቦት 20 ድል በኋላ በከተማም ሆነ በገጠር ብዙ ሚሊዮነር ባለሃብቶችን ማፍራት እንደተቻለም ተናግረዋል።
በትምህርት ጥራት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በማስወገድ ወጣቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣በፈጠራ በእውቀትና ክህሎት የታነጹና ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግ ዋነኛው የመንግስት ትኩረት ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ህዳሴ ዙሪያ ብሄራዊ መግባባት ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ የሃይማኖት ተቋማት፣መገናኛ ብዙኃን፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ሌሎች ተቋማት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።
በ23 ዓመታት ውስጥ የተገኙ ስኬቶችን ማጣጣም ብቻ ሳይሆን፣ በመንግሥት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች ለመፍታትም ልዩ ትኩረት መሰጠቱንም አቶ ኃይለማርያም አመልክተዋል።
መንግስት በቀጣዩ ዓመት የሚካሄደው አምስተኛው አገር አቀፍና ክልላዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ዴሞክራሲያዊ፣ነጻና ፍትሐዊ ሆኖ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞ ክብሯ ለመመለስ ከ1983 ወዲህ የምታደርገውን ግስጋሴ በርካታ አገሮች አድናቆት እየቸሩት መሆኑን አመልክተዋል።
መንግስት ኅብረተሰቡ በኢኮኖሚ፣በማህበራዊና ፖለቲካዊ መስኮች እንዲስተካከሉ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ህዝባዊ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት የተጠናከረ ስራ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ስታዲዬም በተዘጋጀው 23ኛው የግንቦት 20 ማጠቃለያ ልዩ ስነ-ስርዓት ላይ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶችን ጨምሮ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
Comments
Post a Comment