አንድነትና መድረክ ተለያዩ
ላለፉት ስድስት ዓመታት ገደማ ያህል በጋራ ለመሥራት ተስማምተው የተቃውሞ ጐራው ላይ በጋራ ሲሠሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) እና አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የነበራቸውን አብሮ የመሥራት ስምምነት አቋርጠው ተለያዩ፡፡ ሁለቱ ፓርቲዎች የቀድሞው የአንድነት ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ሰጥተውታል በተባለው አስተያየት የተነሳ እሰጥ አገባ ውስጥ መግባታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አስተያየቱን አንድነት ያስተባብል በሚል ከመድረክ የቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ለፓርቲዎቹ መለያየት ከፍተኛውን ድርሻ መውሰዱን የሁለቱ ፓርቲዎች ባለድርሻ አካላት መግለጻቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ ከሁለት ሳምንታት በፊት ዳግም የመድረክ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለአንድነት እስከ ኅዳር 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ ገደብ መስጠታቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አንድነት ለመድረክ ኅዳር 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በጻፈው የመልስ ደብዳቤ፣ ከመድረክ አባልነት መውጣቱን ገልጾ መጻፉን የመድረክ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጥላሁን እንደሻው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡ የአንድነት ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ ‹‹ከመድረክ ጋር በይፋ ተለያይተናል፤ ፊርማችንን ቀደናል፤›› በማለት ከመድረክ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ማቋረጣቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለሁለቱም የፓርቲ አመራሮች ምርጫ በተቃረበበት ወቅት እንዲህ ዓይነት ውሳኔ መውሰድ አጠቃላይ ሰላማዊ ትግሉን አይጐዳውም ወይ የሚል ጥያቄ ሪፖርተር አቅርቦ ነበር፡፡ የሁለቱም ፓርቲ አመራሮች ጉዳት ማስከተሉን ተቀብለው ነገር ግን ከአቅም በላይ በመሆኑ መለያየት መፍትሔ እንደሆነ አስረ