የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይወድቁ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን አምስተኛ ዙር አገር አቀፍ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ይፋ አድርጓል፡፡ ቦርዱ የፊታችን ግንቦት የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ለማካናወን የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶች በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅስቀሳ የሚያደርጉበት፣ መራጮች የሚመዘገቡበት፣ ምርጫው የሚካሄድበትና ውጤቱ ይፋ የሚደረግበት የጊዜ ሰሌዳ ታውቋል፡፡ ምርጫው ሊካሄድ ሰባት ወራት የቀሩት ሲሆን፣ በአገሪቱ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ምርጫ ለመሳተፍ፣ የቻሉትን ለማሸነፍ እንቅስቃሴ የሚያደርጉበት ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን የሚያዘጋጁበት፣ የምረጡኝ ቅስቀሳ ለመጀመር የቤት ሥራቸውን የሚያጠናቅቁበትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን የሚያሟሉበት ጊዜ ነው፡፡ ወቅቱ የምርጫ በመሆኑ የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝብ ትዝብት ውስጥ እንዳይወድቁ ሊጠነቀቁ ይገባል፡፡ እስካሁን አራት አገር አቀፍ ምርጫዎች በአገሪቱ የተካሄዱ ቢሆንም፣ ምርጫ 97 በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጥሎት ያለፈው ትዝታ ግን የሚረሳ አይደለም፡፡ በአገሪቱ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ታዳጊ የሚባል ቢሆንም፣ በምርጫ 97 ታይቶ የነበረው የተስፋ ጭላንጭል የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ዕድገት ያፋጥነዋል ተብሎ ይታመን ነበር፡፡ ያለመታደል ሆኖ በወቅቱ የነበረው የሕዝብ እንቅስቃሴ በቀጣዩ የ2002 ዓ.ም. ምርጫ ሳይታይ ቀረ፡፡ ሳይሟሟቅና ግለቱ ሳይሰማን አለፈ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ በቅርቡ እንደሰማነው ዘጠኝ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ትብብር መሥርተዋል፡፡ ትብብሩን የመሠረቱት የተቃዋሚ ፓርቲዎች የትብብሩ ዓላማ ነፃ፣ ፍትኃዊና ተዓማኒ ምርጫ ለማ