በቡና ዘርፍ ማሻሻያ ሳይደረግ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ታቀደ
• ንግድ ሚኒስትር ሕገወጥ የቡና ንግድ ለመግታት ከነጋዴዎች ጋር መወያየት ጀመረ • የቡና ላኪዎች ማኅበር የመፍትሔ ሐሳቦችን አቀረበ በቡና ወጪ ንግድ ዘርፍ የማሻሻያ ዕርምጃ ሳይወሰድ በ2007 በጀት ዓመት ከዘርፉ 900 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቀደ፡፡ የንግድ ሚኒስቴር በበጀት ዓመቱ 235,000 ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ ውጭ በመላክ 900 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት የተያዘውን ዕቅድ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሚመራው ብሔራዊ የኤክስፖርት ምክር ቤት ማፅደቁ ታውቋል፡፡ ይኼንን ዕቅድ ለማሳካት ንግድ ሚኒስቴር በቅርቡ ዋነኛ ከሚላቸው 195 ቡና ላኪዎች ጋር ለመምከር እንደተዘጋጀ የሚናገሩት ምንጮች፣ ሚኒስቴሩ በቡና የወጪ ንግድ ዘርፍ ያሉትን መሠረታዊ ችግሮች እስካልፈታ ድረስ በታቀደው ዕቅድ ስኬት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው እየገለጹ ነው፡፡ ‹‹በሕገወጥ ነጋዴዎች ምክንያት ሥራችን ለማካሄድ ተቸግረናል፤›› የሚሉ ቡና ላኪዎች ባይቀበሉትም፣ ንግድ ሚኒስቴር ሕገወጥ የቡና ንግድን ለማስቀረት ያስችላል ያለውን ሥራ ጀምሯል፡፡ ሚኒስቴሩ ደረስኩበት ያለው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በኤክስፖርት ደረጃ የተዘጋጀ ቡና በየሱፐር ማርኬቱና በየገበያው በብዛት ይገኛል፡፡ የዚህ ቡና ምንጩ አዲስ አበባ ውስጥ መፈልፈያ ጣቢያ ካላቸው ነጋዴዎች እንደሆነ የሚያስረዳው የሚኒስቴሩ መረጃ፣ እነዚህን ነጋዴዎች ማወያየት ያስፈልጋል የሚል ዕምነት እንዳሳደረ አመልክቷል፡፡ በዚህ መሠረት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የቡና መፈልፈያ ባለቤቶች ሚኒስቴሩ አንድ በአንድ እየጠራ በማነጋገር ላይ እንደሚገኝም ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን ሕጋዊ ነኝ የሚሉ ነጋዴዎች በዚህ የሚኒስቴር ተግባር ዕምነት እንደሌላቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ምክንያታቸው