ቴሌቪዥን ያደመቀው ምርጫ
ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ነበር፡፡ ከአንድ የኢሕአዴግ ደጋፊ ወዳጄ ጋር ወደ አንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎች አብረን ሄደን ነበር፡፡ በምርጫ ጣቢያዎቹ ስለተመለከትናቸው ጉዳዮች እያወራን ወደ ቤታችን እተመለስን ሳለን ከሁለት ወንዶች ጋር ፈጠን ፈጠን እያለች የምትጓዝ ሴት ጓደኛዬን ‹‹ደህና ነህ? እንዴት ነህ?›› በማለት ጠጋ ብላ፣ ‹‹አንተ አታውቀኝም እኔ ግን አውቅሃለሁ፤›› ትለዋለች፡፡ ጓደኛዬ ግራ በተጋባ አኳኋን ሰላምታ እየተለዋወጠ ሳለ ጊዜ ሳትሰጠው፣ ‹‹አልመረጥክም አይደለም? እባክህ ቁጥሩ አልሞላልንም፡፡ ጎድሎብናል ሂዱና ምረጡ፤›› ትላለች፡፡ በነገሩ ግራ መጋባቱ የሚያሳብቅበት ጓደኛዬ፣ ‹‹አይ መርጫለሁ›› ይላል፡፡ ‹‹ጓደኛህስ?›› ትለውና እሱም እየቀለደ፣ ‹‹ተይው እሱ አሸባሪ ነው፡፡ ተቃዋሚ ነው፤›› ይላታል፡፡ ‹‹አሃ የእኛ መስሎኝ'ኮ ነው›› የሚለውን ስሜታዊ ንግግሯን ሳትጨርሰው ወደ እኔ እያየች፣ ‹‹ለነገሩ ተቃዋሚም'ኮ ይመርጣል፤›› ትላለች፡፡ ‹‹ምንድን ነው የጎደለባችሁ?›› ብዬ ስጠይቃት፣ ‹‹ቁጥር አልሞላልንም፣ ሰው አልመጣም፤›› በማለት እቅጩን ነገረችን፡፡ ጓደኛዬ የሴትየዋ ንግግር እኔ ጆሮ መድረሱ ትንሽም ቢሆን ያስጨነቀው ይመስል፣ ‹‹አሃ መስማት የምትፈልገውን አገኘህ አይደል?›› እያለ መቀለድ ይጀምራል፡፡ እሑድ ሚያዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም. በተካሄደው የአካባቢና የከተማ አስተዳደር ምርጫ፣ 31.6 ሚሊዮን መራጮች መመዝገባቸውን የአገሪቱ ምርጫ ቦርድ ያሳወቀ ሲሆን፣ በአጠቃላይ በአገሪቱ 44,509 የምርጫ ጣቢያዎችም ለድምፅ መስጫ አገልግሎት ክፍት ሆነው ውለዋል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ለዚሁ ለአካባቢ፣ ለአዲስ አበባና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምርጫዎች ከፍተኛ ዕጩዎች ያቀረበው ኢሕአዴግ በመሆኑ፣ ብቻውን 3.7 ሚሊዮን ተወዳ