ሕዝብ ለመንግሥት የቤት ሥራ ሰጥቷል ተግባራዊ ምላሽ ይጠበቃል!
ውል ክፍል መሄድ ሳያስፈልግና ቃለ ጉባዔ መፈራረም ሳይጠይቅ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንግሥት የቤት ሥራ ሰጥቷል፤ አደራ አቅርቧል፡፡ ተግባራዊ አዎንታዊ ምላሽም ከመንግሥት ይጠብቃል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት የተሰማውን ሐዘን በሚያስገርም፣ በሚያስመካና ታሪካዊ በሆነ ሁኔታ ከልብ ገልጿል፡፡ ታሪክም ለዘለዓለም ሲዘግበው ይኖራል፡፡ በክብር መዝገብ አስፍሮታል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ሐዘኑን ብቻ አይደለም የገለጸው፡፡ የተጀመረውን የልማት ሒደት ዳር ለማድረስም ቃል ገብቷል፡፡ አሁንም በሕገ መንግሥታችን የሰፈሩትን መብቶችና ጥቅሞች እውን ለማድረግና የኢትዮጵያን ራዕይ ዳር ለማድረስ ዝግጁነቱን ገልጿል፡፡ በእንባም፣ በቃላትም፣ በፀሎትም፣ በሠልፍም፡፡ ሕዝብ መንግሥትን ‹‹ምራ እንከተልሃለን›› ብሏል፡፡ አደራውና የቤት ሥራውም ይኼው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ በተገቢው መንገድ በተግባር ለመመለስ መንቀሳቀስ ይጀምር፡፡ መንግሥት ይህን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ የሚመልሰው እንዴት ነው? ለመመለስስ ይችላል ወይ? ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና መንግሥት ይህን የሕዝብ አደራና የቤት ሥራ በሚገባ ከተገነዘቡትና መመለስ አለበት ብለው ካመኑበት ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ምንም አያዳግታቸውም፡፡ ይቻላል፡፡ ለመመለስ ግን የሚከተሉትን መፈጸም አለባቸው፡፡ 1. ቀጣይነት ሕገ መንግሥቱን መንግሥትም እንደ መንግሥት ኢሕአዴግም እንደ ገዥ ፓርቲ ያመኑበትና የተቀበሉት ብቻ ሳይሆን፣ እነሱ ሥልጣን ይዘው ባሉበት ጊዜ በራሳቸው ተነሳሽነት እውን የሆነ ነው፡፡ ስለሆነም ለቀጣይነቱ ችግር የለውም፡፡ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ባለው መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ የታቀደና የፀደቀ ነው፡፡ ለተግባራዊነቱ ችግር የለ