በሀዋሳ ከተማ ህዝበ ሙስሊሙ በቀበሌ ደረጃ ያካሄደው ምርጫ ተጠናቀቀ
አዋሳ መስከረም 28/2005 በሀዋሳ ከተማ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ትናንት በቀበሌ ደረጃ የሚመሩትን ተወካዮች ነጻና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መምረጡን የከተማው እስልምና ጉዳዮች ምርጫ አስተባበሪና መራጮች ገለጹ፡፡ የከተማው እስልምና ጉዳዮች የምርጫ አስተባባሪ ዶክተር ሁሴን መሐመድ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገጹት በከተማው 19 ምርጫ ጣቢያዎች በተካሄደው ምርጫ ከ3 ሺህ የሚበልጡ ሙስሊሞች ድምጽ ሰጥተዋል፡፡ በህዝበ ሙስሊሙ ቀጥተኛ ተሳትፎና ባለቤትነት በተካሄደው ምርጫ በእያንዳንዱ ምርጫ ጣቢያ ከተጠቆሙት 25 ዕጩዎች መካከል 20ዎቹ በድምጽ ብልጫ ተመርጠው ቃለ መሃላ መፈጸማቸውን አስታውቀዋል፡፡ የተመረጡት ተወካዮች በህብረተሰቡ ዘንድ በሚገባ የሚታወቁ ፣በሀይማኖት ስነምግባራቸው የተመሰገኑና በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን አመልክተው የምርጫው ሂደት ያለምንም ችግር መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡ ከመራጮችም መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የሚበጃቸውን መሪዎች በራሳቸው ቀጥተኛ ተሳትፎ መምረጥ ሲችሉ የአሁኑ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሆኑ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ጠቁመው ምርጫው ነጻ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ http://www.ena.gov.et/Story.aspx?ID=2722&K=1 |
Comments
Post a Comment