ፕሬዝዳንት ግርማ ሁለቱን ምክር ቤቶች በንግግር ከፈቱ



አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2005 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ የህዝብ ተወካዮችና  እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ መደበኛ ስብሰባን በንግግር ከፍተዋል።

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሶስተኛ ዓመት የስራ ዘመናቸውን ዛሬ ጀምረዋል።

በምክር ቤቶቹ የጋራ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ፕሬዝዳንት ግርማ  ባቀረቡት የመክፈቻ የ2005 በጀት ዓመት የመንግስት ትኩረት የሰጠባቸውን  ጉዳዮች አንስተዋል ።

ፕሬዝዳንት ግርማ በንግግራቸው በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ቀያሽነት ባለፉት ሁለት ዓመታት ተግባራዊ መደረግ የጀመረው የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገበበት ይገኛል ብለዋል።

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ሃገሪቱ እያስመዘገበች ያለው ባለሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገትም በዘንድሮው ዓመት እንደሚደገም የሚያረጋግጡ ተግባራት በመንግስት እየተናወኑ እንደሚገኙም ነው የጠቆሙት።

ግብርና አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እድገት እያስመዘገበ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ለማሰቀጠል የሚያግዙ ሰፋፊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች በክረምቱ ወቅት በመላ ሃገሪቱ ተከናውኗል ብለዋል።
         
ከማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት አንስቶ የአርሶ አደሩ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣት ከዓምናው የተሻለ የምርት ጭማሪ እንደሚኖር የሚጠበቅ ነው ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

ስራ አጥነትን ለመዋጋት በተሰሩ ስራዎችም ባለፈው ዓመት ለ1 ነጥብ 1 ሚሊየን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል መፍጠር መቻሉንም ተናግረዋል።

በከተሞች የሚስተዋለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት እየተከናወነ ያለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታም በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የቤት ባለቤት ማድረግ መቻሉን በማንሳትም ይኽው ስራ በዘንድሮው ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል ።

የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር ፣ ትላልቅ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ ፣ የባቡር መስመር ዝርጋታን ማፋጠን ፣ መልካም አስተዳደርን ማረጋገጥ ፣ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሃሳብ እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች የተገኙ ውጤቶችን በበለጠ ሁኔታ ማስቀጠል የመንግስት ትኩረት መሆናቸው በፕሬዚዳንቱ ንግግሮች ላይ ተነስተዋል  ።

Comments

Popular posts from this blog

Israel Eshetu back to his childhood club

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት