ቡና አቅራቢዎች ክፍያ እየተፈጸመላቸው ባለመሆኑ ከገበያ ለመውጣት መገደዳቸውን አስታወቁ



  • ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በአምስት ኤክስፖርተሮች ላይ ዕርምጃ ወስጃለሁ አለ

ቡና አቅራቢዎች ቡናቸውን ለኤክስፖርተሮች ሲያቀርቡ ክፍያ በትክክለኛው መንገድ ስለማይፈጸምላቸውና ከባንኮች ብድር በአግባቡ ስለማያገኙ፣ ከገበያ ለመውጣት መገደዳቸውን ተናገሩ፡፡

ቡና አቅራቢዎቹ ይህንን የተናገሩት ዓርብ የካቲት 29 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን፣ የ‹‹ቀጥታ የገበያ ትስስር››ን ወይም (ቨርቲካል ኢንተግሬሽን)ን በተመለከተ ከአርሶ አደሮችና ከቡና አቅራቢዎች ጋር ውይይት ሲያካሂዱ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ ቡና አቅራቢዎች ንብረታቸውን አስይዘው ከአርሶ አደሩ ቡና ከገዙ በኋላ ለኤክስፖርተሮች በሚሸጡበት ጊዜ፣ ኤክስፖርተሮች ‹‹የሸጣችሁልን ቡና የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስቀመጠውን መሥፈርት አላሟላም›› በማለት ዓመቱ ሙሉ ገንዘባቸውን ይዞ እንደሚያንገላቷቸው የጅማ ዞን ቡና አቅራቢዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ናስር አብዱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ቡና አቅራቢዎች ለኤክስፖርተሮች ቡናቸውን በመሸጥ ይተዳደሩ እንደነበር፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ባወጣው ደንብ ቡና አቅራቢዎችም ሆኑ አርሶ አደሮች ቡናቸውን በቀጥታ ኤክስፖርት ማድረግ መቻላቸውን ገልጸው፣ ዘንድሮ በቀጥታ ቡና በመላክ 2.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት እንደቻሉ አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል በተወሰኑ ኤክስፖርተሮች የቡና ግብይት በሞኖፖሊ በመያዙ ቡና አቅራቢዎች ብዙ ጊዜ የውጭ ገበያ ሰንሰለቱ ላይ ችግር እንደሚገጥማቸው የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ቡና አቅራቢዎች በቀጥታ የገበያ ትስስር ከውጭ ገዥዎች ጋር የሚገናኙበት ሁኔታን መንግሥት መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ኤክስፖርተሮች የውጭ አገር ፈቃድ በማውጣት በሕገወጥ መንገድ ቡና እንደሚሸጡ፣ በዚህ ሳቢያ በርካታ ቡና አቅራቢዎች ወደ ውጭ ኤክስፖርት አድርገው ለመሸጥ ቀዳዳው እንደጠበባቸው አክለው ገልጸዋል፡፡

ቡና ኤክስፖርተሮች በፋይናንስም ሆነ በሌሎች ነገሮች አቅማቸው ትልቅ በመሆኑ እስከ ታች ወርደው ቡናን እንደሚገዙ፣ በሲዳማ ክልል የጌዴኦ ዞን ቡና አቅራቢና የዞኑ የነጋዴዎች ማኅበር ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ወራሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ብዙ ጊዜ ለኤክስፖርተሮች ብቻ ትረኩት እንደሚሰጥ የገለጹት ሰብሳቢው፣ ቡና አቅራቢዎች ከባንክ በአግባቡ ብድር ስለማያገኙ ቡናቸውን በኪሳራ ለመሸጥ መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት በዲላና በተለያዩ ቦታዎች የነበረውን የምርመራ ማዕከል ባለሥልጣኑ ወደ ሐዋሳ ማምጣቱን፣ በቡና አቅራቢዎች ላይ ትልቅ ችግር መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

በዚህ የተነሳ በርካታ ተሽከርካሪዎች ቡና ጭነው ለብዙ ቀናት ውጭ እንደሚቆሙ ገልጸው፣ ችግሩንም የቡናና ሻይ ባለሥልጣን እንዲያይ ጥያቄ ቢቀርብም ምላሽ አለማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ ሁሉም ባንኮች ለቡና አቅራዎች ምንም ዓይነት ብድር አለመስጠታቸውን የተናገሩት ሰብሳቢው፣ ‹‹ለምንድነው ብድር የምትከለክሉን?›› የሚለው ጥያቄ ሲነሳባቸው፣ ብድሩን ሙሉ ለሙሉ ለኤክስፖርተሮች መስጠታቸውን እንደሚነገግሯቸው፣ በዚህ የተነሳ የኮንትሮባንድ ንግድ በዞኑ መስፋፋቱን አክለዋል፡፡

በእርግጥ አንዳንድ ኤክስፖርተሮች ከአቅራቢዎች ጋር በገቡት ውል መሠረት ክፍያ የሚፈጽሙ እንዳሉ፣ ነገር ግን አብዛኞቹ ኤክስፖተሮች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ በማስቀደም ለአቅራቢዎች ገንዘብ እንደማይከፍሉ ተናግረዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስቀመጠው የቀጥታ የገበያ ትስስር መንገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳው፣ ነገር ግን ቡና አቅራቢዎች ጥራቱን የጠበቀና ትክክለኛ የሆነ ቡና በማቅረብ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ቡናው ኤክስፖርተሮች ጋር በሚደርስበት ጊዜ ዋጋ ለማራከስ ሲባል ‹‹ጥራቱ ተጓድሏል›› የሚል ጥያቄ እንደሚነሳ አስረድተዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ቡና አቅራቢዎችም ሆኑ አርሶ አደሮች የቀጥታ የገበያ ትስስርን በመጠቀም ቡናቸውን ኤክስፖርት ማድረግ ይችላሉ፡፡

ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ የቀጥታ የገበያ ትስስርና ኤክስፖርትን በመጠቀም፣ ከአርሶ አደሩ ጀምሮ እስከ ኤክስፖርተሩ ቡናን ወደ ውጭ አገር የሚልኩበት አጋጣሚ መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ያወጣውን መመርያ በተላለፉ አምስት ኤክስፖተሮች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ገልጸው፣ እነዚህም ኤክስፖርተሮች በማንኛውም የቡና ንግድ እንዳይሳተፉ የብቃት ማረጋገጫቸው እንደተወሰደባቸው አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ኤክስፖርተሮች ከአቅራቢ ቡና ከወሰዱ በኋላ በጊዜ ክፍያ የማይፈጸሙበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸው፣ ባለሥልጣኑ ያወጣው መመርያ አቅራቢም ሆነ ላኪ ቡና ሲረካከብ ክፍያ መፈጸም እንዳለበት የሚያዝ ነው ብለዋል፡፡

በዚህ መሠረትም በዚህ ጉዳይ ላይ ባለሥልጣኑ ክትትል እያደረገ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ አርሶ አደሮችም ሆኑ አቅራቢዎች የሚያቀርቡትን የቡና የጥራት ደረጃ ባለሥልጣኑ በመከታተል ተገቢውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ1,000 በላይ አርሶ አደሮች የኤክስፖርት ፈቃድ እንዲያገኙ መደረጉን፣ ባንኮች ለአቅራቢዎችና ለኤክስፖርተሮች የሚያበድሩት የብድር መጠን የተለያየ መሆኑ እንደ ችግር የሚታይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር