በርግጥ በአድዋ ጦርነት ላይ ሲዳማ ተሳትፎ ነበረውን?


የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት አምስት አመታት በአገሪቱ ውስጥ የታዩትን፤ በዘር፣በብሔር፣በብሔረሰብ እና በጎሳ የመከፋፈል አባዜን በትንሹም ቢሆን ለማክሰም፣ የአንድነትን ስሜት በመላው የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ዘንድ ለማነቃቃት ሲል፣ እንዲሁም ካለው ታላቅ ታርካዊ ፋይዳ አንጻር፤ በተለይ በዚህ አመት የአድዋን ድል በአል፣ ከአድዋ ሙዝዬም ምረቃ ጋር ተያይዞ፤ ብሎም በተለያዩ የአገሪቱ አከባቢዎች በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች በታላቅ ድምቀት እንዲከበር ማደርጉ የምታወቅ ነው።

የአድዋ ድል በአል ከተከበረባቸው አከባቢዎች ወይም ክልሎች መካከል፤ የኛ ክልል - ሲዳማም ይገኝበታል። በሲዳማ ክልል የአድዋ ድል በአል እንደሌሎቹ ክልሎች ሁሉ፤ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅበው ሲከበር፤ የሲዳማ ህዝብ የድሉ አካል መሆኑ በብልጽግና ፓርቲ ሰዎች ተደስኩሯል።

በተለይ የክልሉ መንግስት አለቃ ርዕሰ መስተዳድሩ የአድዋ ድል የነጮች የበላይነትንና የቀኝ አገዛዝ ሥርዓትን የሚያቀነቅኑ ምዕራባዊያን ያሳፈረና ያስደነገጠ፤የኢትዮጵያ ሐገራችንን ልዕልና ያስጠበቀ፤የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ አንድነትና ጀግንነት የተንፀባረቀበት ፤ ፤የአፍሪካዊያንን የአሸናፊነት ስነ ልቦና ከፍ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።


አውሮፖውያን የቀኝ አገዛዝ ፖሊሲያቸው ነድፎ አፍሪካን ሲቀራመቱ ጣሊያን ኢትዮጵያውያንን በቀኝ አገዛዝ ቀንበር ለማንበርከክ ወረራ አካሄዶ አልተሳካላትም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም የሆነው አባቶቻችን ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስበው በአንድነትና በህብረት፤ በቆራጥነትና በጀግንነት ፤ባደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል። ሆኖም በዚህ ድል የሲዳማ ህዝብ ተሳትፎ ሳይናገሩ ቀተዋል።

በርግጥ በአድዋ ጦርነት ላይ ሲዳማ ተሳትፈዋል ወይ?

እንግዲህ የአድዋ ድል የኢትዮጵያውን ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝብ ሁሉ ድል ነው። ጥቁር ህዝቦች ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ቁጥር እና የወቅቱን ዘመናዊ ተክኖሎጂ የታጠቀውን የአውሮፓ ጦር በማሽነፍ ታርክ የሰራበት እና ጥቁር ህዝቦችን በበታችነት የሚመለከቱት የአውሮፓ የቅኝ ገዥዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደረገ ድል ነው። በእኔ አመለካከት፤ ይህ ድል በመላው የአለማችን ጥቁር ህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን፤ የቅኝ ግዛት ተጠቅዎች በነበሩ ህዝቦች ዘንድ ሁሉ ልከበር የሚገባ ነው።

ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን የፖለቲካ ሰዎች የህዝቦችን ታርክ ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ከመጀመራቸው ጋር ተያይዞ፤ ይህንን የጭቁን ህዝቦች ድልን ወደ ተወሰኑ ብሔሮች ድል አድርጎ የመግለጽ አባዜ፤ በተለይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ይታያል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በርካታ ግለሰቦች፤ ድሉ በሁሉም የአገሪቱ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን በመጥቀስ ስከራከሩም ይታያሉ። ይህ አይነት አገላለጽ፤ ከግለሰቦችም አልፎ በመንግስት ሚዲያዎችም ላይ ስስተጋባ ይሰማል።

ከላይ እንዳነሳሁት የአድዋ ድል ለጥቁር ህዝቦች እና ለኢትዮጵያውያን ካለው ታርካዊ ፋይዳ አንጻር የሁላችንም ድል ቢሆንም፤ እንደእኔ አመለካከት የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በጦርነቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ በግልጽ መገለጽ አለበት። በደፈናው ከመናገር ይልቅ በግልጽ በጦርነቱ ወቅት የነበረውን የብሔሮች ተሳትፎ ማሳወቅ፤ ብሔሮች በጦርነቱ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ አውቀው፤ ድሉን እንድቀበሉ ያደርጋል ባይ ነኝ።

ይህንን ካልኩ በሃላ ከላይ ወዳነሳሁት ጥያቄ ሲመለስ፤ ለመሆኑ የሲዳማ ህዝብ በአድዋ ጦርነት ላይ ተሳትፎ ነበረውን? በርግጥ ይህ ጥያቄ ከዚህ በፊት ተጠይቆ ይሁን፣ አይሁን የማወቀ ነገር ባይኖርም፤ ጥያቄው ግን ምላሽ የሚያስፈልገው መሆኑን አምናለው። ምንም እንኳን እንዳው በቀላሉ መመለስ የሚቻል ባይሆንም ማለቴ ነው።

ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ለማፈላለግ መጀመሪያ ስራዬ የሆነው፤ የሲዳማ ህዝብ ኢትዮጵያን ወይም አብሲኒያን የተቀላቀለበት የመጀመሪያ አምስት አመታት ውስጥ ያለውን ታርክ መቃኜት ነበር። እንደሚታወቀው አጸ ሚኒሊክ ስከተሉት በነበረው የመስፋፋት ፖሊስ፤ ሲዳማን የኢትዮጵያ አካል ያደረጉት እ.አ.አ. በ 1891 መሆኑን የታርክ ድርሳናት የሚያሳዩ ሲሆን፤ የአድዋ ጦርነት የተካሄደ ደግሞ የዛሬ 125 አመታት በፊት፣ እ.አ.አ. በ 1896 ነው። ይህም ማለት ሲዳማ የኢትዮጵያ አንድ አካል ከሆነ በአጭር ጊዜ ወይም ከአምስት አመታት በሃላ መሆኑን ነው።

እንግዲህ ሲዳማ የኢትዮጵያ አካል የሆነው በውዴታ አይደለም። ሲዳማ የአገሪቱ አካል ላለመሆን እና ሉአላዊነቱን ላለማስነጠቅ በተደጋጋሚ ከአጸ ሚኒሊክ ጦር ጋር ተፋልሟል። በአጸ ሚኒሊክ ጦር ተሸንፎ፤ ለንጉሱ ጦር ገባሪ የሆነ የሲዳማ ህዝብ፤ ያውም ከሺዎች ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚካሄደው ጦርነት ላይ በፍላጎት ይሳተፋል የሚል እምነት የለኝ። በርግጥ እዚህ ላይ አጸ ሚኒሊክ ሁሉም አገሪቱ ህዝቦች በጦርነቱ ላይ እንዲሳተፉ ጥር ከማስተላለፍ አልፈው፤ ማስፈራሪያ ጭምር ማስነገራቸው ይታወቃል። ይህም ማስፈራሪያ ሲዳማዎቹንም ወደ ጦርነቱ እንዲዘምቱ አድርጓቸው ይሁን አሁን የሚታወቅ ነገር የለም። ወይንም ልክ እንደደርግ ዘመን፤ የሲዳማ ወጣቶች በግድ ተይዘው ለውትድርና ተልከው ከአድዋ ጦርነት ላይ ተሳትፎ ይሁን ይህም ግልጽ አይደለም። ነገር ግን ከሲዳማ አጎራባች አከባቢዎች የዘመተ ጦር መኖሩን፤ ከወላይታ እና ከመሳሰሉት የሚንሰማቸው ታርኮች፤ የሲዳማ አጎረባቾች ከዘመቱ፣ ሲዳማ የማይዘምትበት ምክኒያት እንደሌለ የሚያሳዩ ናቸው።

ሆኖም በጦርነቱ ወቅት የነበረውን የኢትዮጵያ ጦር አስተላላፍ በሚናይበት ጊዜ፤ THE BATTLE OF ADWA በሚል ርእስ በበርካታ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጸሃፍት በተጻፈው እና የአድዋን ጦርነት በሚተርከው መጽሐፍ ውስጥ ከጦርነቱ በፊት የነበረውን የአትዮጵያ ጦር አስተላላፈ ስገልጽ፤ የሲዳማ ጦረኞች ስም አላካተተም።

ያም ሆነ ይህ፤ የሲዳማን በአድዋ ጦርነት ላይ መሳተፍ ወይም አለመሳተፍ በእርግጠኝነት መናገር የሚያስችሉ የታርክ ድርሳናት እኔ በበኩሌ ማግኘት አልቻልኩኝም። የተሳትፎ ጥያቄው ግን ምላሽ ማግኘት አለበት የሚል እምነት አለኝ። ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ መረጃው ያላችሁ ሰዎች እንድትጋሩን ይሁን።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር