ለኢንዱስትሪ ፓርኩ 120 ሜጋ ዋት ኃይል ለመስጠት እየተሰራ ነው


የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል የመሬት ዉስጥ መስመር ዝርጋታ እያከናወነ ይገኛል።
የመስመር ዝርጋታው ቀደም ሲል ለፓርኩ ከመሬት በላይ በምሰሶ የተዘረጋዉን የኤሌክትሪክ መስመር በመሬት ዉስጥ በመቀየር በቀጥታ ከማከፋፈያ ጣቢያ እንዲያገኝ ለማድረግ ነዉ።
በዚህም ለኢንዱስትሪ ፓርኩ የሚሰጠዉን የኤሌክትሪክ አቅርቦት መጠን በዕጥፍ ለማሳደግ እና ቀደም ሲል የነበረዉን የኃይል መቆራረጥ ለመቀነስ እንዲሁም ለኃይል ብክነት ያለዉን ተጋላጭነት ለመቅረፍ ያስችላል።
ግንባታው በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሲቪል ስራዉን 99 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ 2 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የመሬት ዉስጥ መስመር በኮንክሪት የመገንባት፤ ግራ እና ቀኝ የኤሌክትሪክ ገመድ አቃፊ ብረቶችን የመትከል ስራ ተከናዉኗል።
የሲቪል ስራው ኬዲቲ በተሰኘ ሀገር በቀል ኮንስትራክሽን ድርጅት እየተከናወነ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ የግንባታውን አጠቃላይ የማማከር እና የቁጥጥር ስራ ደግሞ በተቋሙ የኢንጂነሪንግ እና ኳሊቲ ዳይሬክቶሬት በኩል እየተሰራ ይገኛል።
ይህ የመሬት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መስመር ዝርጋታ ኘሮጀክት ለፓርኩ የሚሰጠውን የኃይል አቅርቦት መጠን በዕጥፍ የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ የኃይል መቆራረጡንና ብክነቱን በከፍተኛ ደረጃ በመቅረፍ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከኃይል አቅርቦት አንፃር የሚገጥሙትን ችግሮች በማስቀረት በሙሉ አቅሙ ማምረት የሚያስችለዉ እንደሆነ ይታመናል።
አጠቃላይ የሲቪል ግንባታ ስራው ለማጠናቀቅ 119 ሚሊየን ብር በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተመድቦ እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ አሁን ላይ የሲቪል ስራውን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ወደ ኤሌክትሪካል ስራው ለመግባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።
የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውስጡ 52 የማምረቻ ሼዶችን የያዘ እና 20 የሚሆኑ የውጭ ባለሀብቶች የተሰማሩበት ሲሆን፤ እራሱን የቻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም ምድብ መስመር (Dedicated line) ያለው ነው።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር