በደቡብ ሙስና የፈፀሙ 413 ተጠርጣሪዎች እስከ 17 ዓመት ተቀጡ

በደቡብ ክልል የሙስና ወንጀል የፈፀሙ 413 ግለሰቦች እስከ 17 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡
በደቡብ ክልል በ2009 ዓመተ ምህረት ከሙስና እና ብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘ ክስ በተመሰረተባቸው 413 ተከሳሾች ላይ እስከ 17 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት ቅጣት መተላለፉን የክልሉ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለጸ።
በክልሉ በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት በተካሄደው የፀረ ሙስና እና ብልሹ አሰራር እንቅስቃሴ በተጋለጡት ግለሰቦች እስካሁን በ3 ሺህ 134 ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ሃይሉ ዛሬ አስታውቀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ፖለቲካዊ እርማጃ የተወሰደባቸው ሲሆን፤ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃ እንደተወሰደም ገልጸዋል።
ሙስና ብልሹ አሰራር በመፈፀም የመንግስትን እና የሕዝብን ጥቅም ያሳጡ ግለሰቦች ላይ 211 መዝገብ ተከፍቶ 413 ተከሳሾች ላይ ህጋዊ ውሳኔ እንደተሰጠባቸውም አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡
እነዚህም ከ17 ዓመት ፅኑ እስራት እስከ እስከ 3 ወር ቀላል እስራት እና እስከ ከ105 ሺህ 300 ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ገልፀዋል፡፡
በክልሉ 291 ሚሊዮን 299 ሺህ 512 ብር ከምዝበራ ማዳን ተችሏል ነው ያሉት ሃላፊው፡፡ ገንዘቡ ተመዝብሮ በክትትል እንዲመለስ የተደረገ እና በጥቆማ ቀድመ መከላከል የተቻለ መሆኑንም አብራርተዋል።
ከሙስና ጋር በተያያዘ መኖሪያ ቤቶች፣ ባለ ሁለት እና ባለ አራት ወለል ህንፃዎች፣ ፔኒሲዮን፣ ጥሬ ገንዘብ እና ተሸከርካሪዎች መታገዳቸውንም አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል።
ከገንዘብ ባሻገር በገጠር 10 ሺህ ሄክታር እና በከተማ 1 ሚሊየን ካሬ ሜትር መሬት ተመላሽ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡
ህዝቡ ችግሮችን በማጋለጥ ረገድ ዋንኛ ተሳታፊ ነበር ያሉት አቶ ሰለሞን፤ የህዝብ ተሳትፎ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አስገንዝበዋል።
እስካሁን የተወሰደው እርምጃ መነሻ እንጂ በቂ ባለመሆኑ በተያዘው የፀረ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ትግል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል-(ኤፍ.ቢ.ሲ)፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር