POWr Social Media Icons

Friday, July 1, 2016

የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፊቼ መከበር ጀመረ
የሲዳማ ብሄር ዘመን መለወጫ ፊቼ በዓል ዛሬ መከበር ጀምሯል፡፡
በሲዳማ ባህል አዳራሽ በተካሄደ ሲምፖዚየም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ደሴ ዳልኬ የበዓሉን እሴቶች  ከዘመን ዘመን በማሸጋገር ለአለም ቅርስነት እንዲበቃ ላደረጉ የሃገር ሽማግሌዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
"የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ በአለም ቅርስነት መመዝገቡ የክልሉን ብሔሮች ብሔረሶቦችና ህዝቦች አንድነት የሚያጠናክር ነው "ብለዋል፡፡
የብሔሮች ብሔረሶቦችን ማንነት የሚያስከብር ስርዓት በመገንባቱ ባህሎቻቸው በአደባባይ እንዲከበሩ እድል መፈጠሩንም አቶ ደሴ ገልጸዋል፡፡
የበዓላቱ መከበር ለተጀመረው ልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ በዓሉን ከማክበር ባሻገር የተግባር አጀንዳ ማድረግ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ለደንና ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣ የመቻቻልና የመከባበር እሴቶች እንዲጎለብቱ ወጣቶች የድርሻቸወን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል፡፡
ዛሬ የተጀመው የፊቼ በዓል ነገም በጉዳማሌ አደባባይና  በተለያዩ ወረዳዎች የሚቀጥል በመሆኑ  ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር የሃገር ሽማግሌዎች ሃላፊነት እንዳለባቸውም ተመልክቷል፡፡
በዓሉ በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ተቋማትና ግለሰቦች ርዕሰ መስተዳድሩ አመስግነዋል፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሃመድ በበኩላቸው "ቅርሶች የማንነታችን መገለጫ በመሆናቸው በማንኛውም ጊዜና ቦታ ተገቢው እንክብካቤና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል" ብለዋል፡፡
የሲዳማ ብሄርም ለዘመናት ጠብቆ ለዚህ ትውልድ እንዲበቃ ያደረገው ፊቼ ጨምባላላ በማይዳሰሱ ቅርሶች በመመዝገቡ ሃገሪቱን ቀደምት የቅርስ ባለጸጋ አድርጓታል፡፡
የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ቅርሶችን ከስር መሰረት በማጥናት ለትውልድ ተሸጋግረው  ሃገራዊና አለም አቀፋዊ እውቅና እንዲኖራቸው ለማድረግ በሚሰራው ስራ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ቅርሱን ለማስመዝገብ ከፍተኛ ጥረት መደረጉን ያስታወሱት ሚኒስትሯ አሁን ያለው ትውልድ አደራውን ተቀብሎ ቅርሶቹን በተሻለ ሃላፊነት መጠበቅ እንደሚገባውም ጠቁመዋል፡፡
የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ አዱላ በበኩላቸው ሳይማሩ ባህሉ ሳይበረዝ ለትውልድ እንዲተላላፍ ያደረጉ የሲዳማ አባቶችን በማመስገን ይህም ያለፉት 25 ዓመታት የልማትና ዴሞክራሲየዊ ስርዓት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም ወጣቶች ይህንን አደራ በመረከብ ባህላዊ እሴቶቹ ሳይበረዙ በዓሉ በአለም ህዝብ እንዲጠበቅና እንዲከበር የማድረግ ሃላፊነት እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
ከበበዓሉ ተሳታፊ የብሄሩ የሀገር ሽማግሌ አቶ አለሙ አደመ በሰጡት አስተያየት ፊቼ ጨምበላላ ጥንት አባቶች ኮከብ ቆጥረው የሚያከብሩት እንደሆነ ተናግረው በዓሉ ሲከበር የተጣላ የሚታረቅበት ጭምር መሆኑን  ገልጸዋል፡፡
የሲዳማ ባህል በርካታ ተጽዕኖዎችን አልፎ ህገ መግስቱ የሰጠውን መብት ተጠቅሞ ዛሬ አለም አቀፍ አውቅና በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በሲምፖዚየሙ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

0 comments :