POWr Social Media Icons

Saturday, June 25, 2016


የወሬው ምንጭ ኢዜ ኣ ነው
በሀዋሳ ከተማ ከ34 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሊገነቡ ነው
በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ማዕከል በሆነው ሀዋሳ ከተማ   ከ34 ሺህ በላይ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እንደሚገነቡ የክልሉ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ሰፋፊ ይዞታ ያላቸውና ለኪራይ የሚሆን ቤት ለሚገነቡ ግለሰቦች የብድር አገልግሎት የሚውል ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ መመቻቸቱም ተመልክቷል፡፡
የኤጀንሲው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ካሳዬ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት በከተማዋ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ግንባታው የሚካሄደው ከመጪው ዓመት ጀምሮ ነው፡፡
"የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች የገቢ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት የሚገነቡ ሲሆን ከ34 ሺህ ቤቶች ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት በአስር ዘጠና መርሀ ግብር የሚገነቡ ናቸው" ብለዋል፡፡
በአስር ዘጠና መርሀ ግብር ለሚገነቡት  ስቱዲዮ ቤቶች የሚመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች በወር 199 ብር ሄሳብ ለሶስት ዓመት መቆጠብ አለባቸው፡፡ 
" ለባለ አንድ መኝታ ቤት 368 ብር ለባለ ሁለት መኝታ 575 ብር እና ለባለሶሰት መኝታ ቤት ደግሞ  739 ብር በወር ለሰባት ዓመት የቆጠበ የቤት ባለቤት መሆን ይችላል " ሲሉ  ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡ 
ለግንባታው የቦታ ፣ የገንዘብና ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን  ጠቁመው ለቤት ፈላጊዎች ምዝገባው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
ተመዝጋቢዎች ከተመዘገቡበት ጊዜ ጀምሮ በየወሩ መቆጠብ ያለባቸውን ገንዘብ እየቆጠቡ 10 እና 20 በመቶ የሚሆነውን ቆጥበው እንዳጠናቀቁ ቤቱን በዕጣ እንደሚያገኙና በአንድ ጊዜም መክፈል እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
" የመኖሪያ ቤት እጣው በሚወጣበት ጊዜ መንግስት በሰጠው ትኩረት መሰረት ከእጣው 10 በመቶ ለመምህራን ፣ 30 በመቶ ለሴቶች ፣20 በመቶ ለመንግስት ሰራተኞች እንዲሁም 5 በመቶ ለአካል ጉዳተኞች ቅድሚያ ቀሪው 25 በመቶ ለሌሎች ተመዝጋቢዎች በዕጣ ይሰጣል"ብለዋል፡፡
አቶ አስቻለው እንዳሉት በተጨማሪም ሰፊ ይዞታ ያላቸው ግለሰቦች ለኪራይ የሚሆን ቤት ገንብተው የመኖሪያ ቤት እጥረቱን ለማቃለል እንዲችሉ ለግንባታ ብድር እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡
ከብሔራዊ የኢንደስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር ግለሰቦች ለሚያከናውኑት ለኪራይ የሚሆን ቤት ግንባታ የሚውል ከ50 ሚሊዮን በላይ ብር ብድር ተመቻችቷል፡፡
ለዚህም በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በሙከራ ደረጃ ተመርጦ እስካሁን 1 ሺህ 400 ግለሰቦች ለግንባታ የሚሆን ብድር ለመውሰድ ተመዝገበዋል፡፡
እንዲሁም በማህበር ተደራጅተውና ሀምሳ በመቶ የሚሆነውን ክፍያ ቅድሚያ ለሚከፍሉ ማህበራት ቦታ ተመቻችቶ እየተሰጠ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

0 comments :