በኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በድርቅና በድህነት ምክንያት በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግር መጠን ሊድበሰበስ አይገባም!! – መድረክ

በኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ፣ በድርቅና በድህነት ምክንያት በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግር መጠን ሊድበሰበስ አይገባም!!

(ከኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ የተሰጠ መግለጫ)
ሀገራችንን ላለፉት 25 ዓመታት ሲገዛ የቆየው ኢህአዴግ ባለ2 አሀዝ ፈጣን እድገት እያስመዘገብኩ ሀገራችን በምግብ ራሷን እንዲትችል፣ ከስንዴ ልመና ለመውጣትና እያንዳንዱ ዜጋም በቀን ቢያንስ ሶስት ጊዜ ለመብላት እንዲበቃ እያደረኩ ነኝ ብሎ በሚያሰራጨው የፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ሕዝባችንን የተስፋ ዳቦ እየመገበ ለማኖር ቢሞክርም በአገዛዙ ጊዜ የተፈጥሮ ድርቅ በሚከሰትበትም ሆነ በሌላ ወቅት በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው ከፍተኛ ችግርና መጎሳቆል የፕሮፓጋንዳውን ባዶነት በተጨባጭ በተደጋጋሚ አሳይቷል፡፡ ሀገራችንን በዓለማችን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ በአጭር ጊዜ ለማሰለፍ የሚያስችል ፈጣን እድገትና ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ነን፣ በማለት በሚያሰራጨው ፕሮፓጋንዳም የጥቅት የሥርዓቱ ገዥዎችና ምንደኞች በስተቀር የብዙሃኑ ሕዝባችን ኑሮው ሲሻሻል አልታየም፡፡
አህአዴጎች ምርታማነትን በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ሀገራችን በምግብ ራሷን እንዲትችል ብቻ ሳይሆን ለውጭ ገበያም ለማቅረብ በቅተናል፣ በማለት በተደጋጋሚ ድስኩር ባሰሙ ማግስት፣ በአንድ የምርት ወቅት ብቻ እንኳ የተከሰተው የዝናብ እጥረት የድስኩራቸውንና የፉከራቸውን ባዶነት እያጋለጠ እርቃናቸውን ሲያስቀራቸው ለማየትና ለመታዘብ ችለናል፡፡ በእጂጉ የሚያሳስበን ይህንን ባዶ ፕሮፓጋንዳቸውን ለመሸፋፈን ሲሉ በሕዝባችን ላይ እየደረሱ ያሉ ችግሮችን በትክክል ባለመግለጽ ሕዝባችንን ለባሰ ጉዳት እየዳረጉት መገኘታቸው ነው፡፡ ለእነዚህ ችግሮች ዋና መሠረቱም ኢህአዴጎች ብዙ የሚያወሩለት የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲ የምልአተ-ሕዝባችንን የኑሮ ችግሮች በተጨባጭ ሊቀርፍና ሊያስወግድ በሚያስችልና ዜጎች ፍትሐዊ ተጠቃሚ በሚሆኑበት አቅጣጫ ያልተመራ መሆኑ ነው፡፡ አርሶ አደሩ ሕዝባችን እንዳለፉት ሥርዓቶች ሁሉ በትናንሽ የመሬት ይዞታዎች ላይ በተመሠረተ እጅግ ኋላ ቀርና የዝናብ ጥገኛ በሆነው የግብርና ምርት አመራረት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ለአንድ የምርት ወቅት የሚከሰት የዝናብ እጥረት ለመቋቋም የሚያስችል ምርት በግልም ሆነ በሀገር ደረጃ ማምረት ባለመቻሉ የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት ለአስከፊ አደጋ ሲጋለጥ ቆይቷል፡፡
ከ2007 ዓ ም ጀምሮ በበርካታ የሀገራችን አከባቢዎች የተከሰተው የዝናብ እጥረትም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበርካታ ዜጎቻችንን ሕይወትና ንብረት በተለይም በሰብል ምርትና የእንሰሳት ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ሕዝባችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ከአስር ሚሊዮን በላይ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንና የቤት እንሰሳት የሚበሉትንና የሚቀምሱትን አጥተው በረሃብና በውኃ እጦት የሚጎዱበት ሁኔታ ሊፈጠር ችሎአል፡፡ ይህንንም አሳዛኝ ክስተት የኢህአዴግ አገዛዝ እጅግ አቃልሎ በጣም ጥቂት ዜጎችን ብቻ የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ፣ እንደዚሁም በመንግስት አቅምና በሀገር ውስጥ ባለ የምግብ ክምችት ችግሩን መቋቋም እንደሚቻል አስመስሎ ስያድበሰብስ ቆይቷል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የውጭ ሀገር ሚዲያዎች የችግሩን መጠን ይፋ ሲያደርጉም ኢህአዴግም እንደ ቀደምቶቹ የሀገራችን አምባገነን ገዥዎች ለማስተባበልና ለመሸፋፈን እየሞከረ ይገኛል፡፡

እስከአሁን ድረስም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በትክክል ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም ሕብረተሰብ ባለመግለጹና የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሀገር እርዳታ በተገቢው ደረጃ ለማሰባሰብና ለማሰራጨት ባለመንቀሳቀሱ እጅግ በርካታ የድርቁ ተጎጂ ወገኖቻችን እርዳታ በወቅቱ እየደረሳቸው አለመሆኑ በእጂጉ ያሳስበናል፡፡ በአንዳንድ አከባቢዎች እርዳታው በወቅቱ ያልደረሰላቸው ወገኖቻችን ጠብቀው በማጣታቸው እርዳታ ፍለጋ ለመሰደድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ድረስ የሚታይ ቢሆንም የኢህአዴግ ካድሬዎች እርዳታውን በማድረስ ችግሩን ከመፍታት ፋንታ ሕዝቡ በግድ ባለበት እንዲቆይ በማድረግ ሥራ ላይ አተኩረው ይገኛሉ፡፡
እርዳታው እየደረሰ ባለበት አንዳንድ አከባቢዎችም በኢህአዴግ ዘንድ የተለመደውን ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በማንጸባረቅ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ለሆኑ ተጎጂዎች “ፓርቲያችሁ አምጥቶ ይስጣችሁ” በማለት፣ ሰብአዊ እርዳታን ለፖለቲካ መሳሪያነት እየተጠቀሙ ይገኛሉ፡፡ በአንዳንድ እርዳታው እየተከፋፈለ ባለባቸው አከባቢዎችም የእርዳታ እህልና ዘይቱን እየሸጡ ለምንም የማይበቃ ትንሽ ገንዘብ ለተጎጂዎች እየሰጡና ለልማት እያሉም ተጎጂዎቹን ገንዘብ እንደሚያስከፍሉ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ በድርቅ ምክንያት ምርት ለማግኘት ያልቻሉ አርሶ አደሮችም አመታዊ ግብር መክፈል ባልቻሉባቸው አከባቢዎች እርዳታውን ሳይቀበሉ እንዲፈርሙና ለእርዳታ የተመደበላቸው እህል ተሸጦ በግብር ስም ለመንግሥት ገቢ እንዲደረግ ሕገወጥና ኢ-ሰብአዊ ጫናዎች በአርሶ አደሮች ላይ እየተፈጸሙ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሎአል፡፡
በአጠቃላይ ሲታይ በቅርቡ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ ኢህአዴግ ላለፉት አሥር ተከታታይ አመታት አስገኘሁ ያለው የኢኮኖሚ እድገት የጥቂት የሥርዓቱን ባለሟሎች ሕይወት ከመለወጥ በስተቀር ሰፊውን ሕዝባችንን በአንድ የምርት ወቅት የሚከሰተው የዝናብ እጥረት ከሚያስከትለው የምግብ እጥረት ሊታደግ ያልበቃ መሆኑ ሀገራችን በምን ያህል ችግር ውስጥ እንዳለች ያሳያል፡፡ የኢህአዴግ አገዛዝም እንደቀደምቶቹ ሥርዓቶች ሁሉ ለሕዝባችን ችግሮች ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጥ ለራሱ አባል ድርጅቶች አመታዊ ክብረ በዓላት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ገደብ በሌለው ወጪ የሀገር ሀብት በማባከን የሚሠማራ አምባገነናዊ መንግሥት መሆኑን በግልጽ አሳይቷል፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሕዝባችን በችግር ላይ ባለበት ወቅት ኢህአዴግ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎችም ሆነ በየአከባቢው ባሉት የካድሬ ሠራዊቱ አማካይነት በስፋት ትኩረት ሰጥቶ በማሰራጨት ላይ ያለው ፕሮፓጋንዳ፣ በሕዝባችን ላይ እየደረሱ ያሉትን የረሃብና የኑሮ ችግሮች ለሕዝባችንና ለዓለም ሕብረተሰብ በማሳወቅና ለችግሩ መፍትሔ በመሻት ላይ ሳይሆን፣ ለአባል ድርጅቶቹ ዓመታዊ ክብረ በዓላት ድምቀት ከፍተኛ ሀብት በማባከን በሚከናወን ፈንጠዚያ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህም “ታሪክ ራሱን ይደግማል” እንዲሉ ቀደምት አምባገነናዊ ሥርዓቶች ሕዝባችን በድርቅ ሲጠቃ በነበረባቸው ጊዜያት በረሃብ የሚሰቃየውን ሕዝብ ችግሮች ችላ ብለው ለራሳቸው ክብረበዓላትና ለቤተሰቦቻቸው የልደት ቀናት አከባበር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው የሀገር ሀብት ሲያባክኑ ከኖሩበት አሰነዋሪ ተግባራት ጋር ተመሳሳይ ድርጊት ነው፡፡
ስለዚህም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ/መድረክ/ የኢህአዴግ አገዛዝ ከዚህ አስነዋሪ ተግባሩ ተቆጥቦ ፡-
1ኛ፡- በሕዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ረሃብ ስፋትና ጥልቀት ለሕዝባችንና ለዓለም ሕብረተሰብም በትክክል እንዲያሳውቅና የተጎዱት ወገኖቻችን የሚገባቸውን ያህል እርዳታ በወቅቱ የሚያገኙበትን ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲያመቻች፣
2ኛ፡- ለተራበው ሕዝባችን እርዳታ ከሀገር ውስጥ በማሰባሰብ በውጭ ልመና ያጠለሸውን የሀገራችንን ገጽታ የማጥራት እርምጃ እንዲወስድ፣
3ኛ፡- በረሃብ ለተጎዳው ሕዝብ የሚሰጠው እርዳታም ካለአንዳች አድሎኦና የፖለቲካ ወገንተኝነት ለተጎዳው ዜጋ ሁሉ በትክክል እንዲዳረስ እንዲያደርግ፣ የእርዳታ እህሉን በሚሸጡና የልማት መዋጮ ክፈሉ በማለት ተጎጂዎችን ገንዘብ በሚያስከፍሉ ካድሬዎች ላይም ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ፣
4ኛ፡- ለአባል ድርጅቶቹ ክብረበዓላትም ሆነ ሕብረተሰቡን ለመደለል ለሚያዘጋጃቸው የተለያዩ የመደለያ ፕሮግራሞች ያለገደብ እየባከነ የሚገኘውን የሀገር ሀብት በድርቁ ለተጎዳው ሕዝባችን እርዳታ እንዲውል እንዲያደርግ፡-
5ኛ፡- ኢህአዴግ ሕዝባችንን ከድህነትና ከረሃብ ያላላቀቀውን “የፈጣን የኢኮኖሚ እድገት” አምጥቻለሁ የሚለውን ባዶ ፕሮፓጋዳ አቁሞ፣ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ በዘላቂነት የሕዝባችንን ኑሮ በተጨባጭ የሚያሻሽልና ከድህነትና ከረሀብ በሚያላቅቅ ስልት እንዲመራ እንዲያደርግ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
ድል ለሕዝባዊ ትግላችን!!
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት
መድረክ/መድረክ/
ህዳር 20 ቀን 2008 ዓ ም

Source:http://www.mereja.com/amharic/475339

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር