POWr Social Media Icons

Thursday, August 27, 2015

  • ውድድሩ የቡና ጥራትንና አቅርቦትን ለማሻሻል ያግዛል፤
  • ውድድሩ ከጥር እስከ የካቲት 2008 .ም የሚካሄድ ሲሆን፤ በሲዳማ አካባቢ የሚገኙ ከ24 ሺ በላይ የቡና አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃልየቡና አምራቾች ውድድር ይካሄዳል


ዩሺማ ኮፊ ካምፓኒ በተሰኘ የጃፓን የቡና ማቀናበሪያ ካምፓኒ አማካኝነት የኢትዮጵያን ቡና በዓለም የቡና ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅ የሚያስችልና የቡና አምራች አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ የሚያደርግ የኢትዮጵያ የቡና አምራቾች ውድድር ሊካሄድ ነው።
የውድድር ሂደቱን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ በጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ግቢ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት እንደተነገረው፤ ውድድሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካም የመጀመሪያ ነው። የውድድሩ ተግባራዊ መሆንም የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ እውቅና ባላቸው ድርጅቶች እንዲተዋወቅ ዕድል የሚፈጥርና አምራቾችም ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚያደርግ ነው።
የካምፓኒው ዳይሬክተርና የአቅርቦት ትስስር ማኔጅመንት ሊቀመንበር ሚስተር ቲቲሱያ ሴኪ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ በዚህ ውድድርም እስከ ስድስተኛ በመውጣት የሚያሸንፉ አምራች ገበሬዎችን ካምፓኒው ምርቶቻቸውን ከመደበኛው ዋጋ ጨምሮ የሚገዛና ለምርት ጥራት የሚያግዙ ድጋፎችን የሚያደርግ ሲሆን፤ ከስድስተኛ በላይ ለሚወጡ ደግሞ የምርት ግዥውን በተወሰነ መልኩ የሚያከናውን ይሆናል። በውድድሩም የሲዳማ ቡና አምራቾች ብቻ የሚሳተፉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የቡና አምራች አገር እንደመሆኗ በቀጣይ የሌሎች አካባቢ አምራቾችን ለማሳተፍ የሚሰራ ይሆናል። ቡናው ወደ ጃፓን ከተወሰደ በኋላም አስፈላጊው የጥራት መመዘኛ ተከናውኖ የማስተዋወቅ ሥራ ይሰራበታል። በመሆኑም አምራቾቹ በውድድሩ መሳተፋቸው የቡና ምርትና ጥራትን ጠብቀው እንዲያመርቱና በዛው ልክ ከሚገኘው የገበያ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዕድል ይፈጥራል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ካዙሂሮ ሱዙኪ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ቡናን በሰፊው የምታመርት ቢሆንም አምሯቾች ለፍሬው ደህንነት የሚሰጡት ትኩረት አናሳ ነው። በአንጻሩ የጃፓን አምራቾች ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። አወዳዳሪ ካምፓኒው ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው እንደመሆኑ ውድድሩ የኢትዮጵያን ቡና ወደ ውጭ በመላክ በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲስፋፋ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል። ከዚህም ባሻገር በሁለቱ አገሮች አምራቾች መካከል የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ዕድል ይፈጥራል። የጃፓን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ጃይካእና ሌሎች የጃፓን ድርጅቶች በኢትዮጵያ መሰል የልማት ተግባራትን እየደገፉ እንደመ ሆናቸውም፤ ተግባሩ የሁለቱን አገራት የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር የሚያሳድገው ይሆናል።
በጃፓን የኢትዮጵያ አምባሳደር ማርቆስ ተክሌ በበኩላቸው፤ ጃፓን በየዓመቱ እስከ 30ሺ ቶን ቡና ከኢትዮጵያ ትገዛለች። ይህን ከሚያደርጉ የጃፓን ኩባንያዎች አንዱ ዩሺማ ሲሆን፤ አሁን እያከናወነ ያለው ተግባርም የኢትዮጵያን ቡና በዓለም ገበያ የበለጠ ለማስተዋወቅና አምራቾችም ቡናን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው እንዲያመርቱ የሚሰራበትን ዕድል የሚፈጥር ነው።
እንደ አምባሳደር ማርቆስ ገለጻ፤ የብራዚልም ሆነ የሌሎች አገራት ቡና ከኢትዮጵያ ቡና በጥራት ያነሰ ሆኖ ሳለ በተገቢው መልኩ ተዋውቆ ስም ስለተከለ የተሻለ ጥራት ያለው ተደርጎ ይወሰዳል። ተቋሙ ቡናን እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርብ እንደመሆኑ ይህን ተግባር ማከናወኑ የኢትዮጵያ ቡና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለዓለም ገበያ እንዲቀርብና የተሻለ ስም እንዲተክል መደላድል የሚፈጥር ነው። በቀጣይም ገዝቶ ከማስተዋወቅ ባሻገር በሌሎች አገራት እንደሚያከናውኑት የቡና እርሻ ልማት በኢትዮጵያ እንዲያከናውኑ በሰፊው የሚሰራ ይሆናል።
ውድድሩ ከጥር እስከ የካቲት 2008 .ም የሚካሄድ ሲሆን፤ በሲዳማ አካባቢ የሚገኙ ከ24 ሺ በላይ የቡና አምራቾች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
- See more at: http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/national-news/item/2709-2015-08-26-13-18-47#sthash.VSzT5Zok.dpuf

0 comments :