POWr Social Media Icons

Friday, June 19, 2015

ዜና ሐተታ
ከደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ወንዶገነት ወረዳ የሃዲቾ ጎሳ አባላት አቶ ዘሪሁን ሰንበቶና አቶ ሰለሞን አለሙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባስገቡት ቅሬታ «በሲዳማ ዞን የተለያዩ ቀበሌዎች ችግሩ ተፈጥሮ የአንድ ሰው ህይወት ከማለፉና ከ60 ቤቶች በላይ ከመቃጠሉና በርካታ ንብረት ከመውደሙ በፊት ከወረዳ እስከ ክልል በየደረጃው ላሉ ተቋማትና ኃላፊዎች ችግሩ እንዳይፈጠር ብናመለክትም ሁሉም አካላት ምላሽ ባለመስጠታቸው ጉዳት ደርሷል» ብለዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ የግጭቱ መንስኤ የወላቢቾ ጎሳ አባል የሆነችው ወይዘሪት መብራቴ ገልገሎ የተባለች ወጣትና የሃዲቾ ጎሳ አባል የሆነ አቶ ቢኒያም ብርሃኑ ተዋደው በመጋባታቸው የወላቢቾ ጎሳ አባላት «የሃዲቾን ጎሳ ልጅ እንዴት ያገባል። እኛ ምርጥ ዘር ነን» በሚል የጎሳው አባላት ተሰባስበው በሃዲቾ ጎሳ ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ጉዳት መድረሱን ጠቁመዋል።
የወላቢቾ ጎሳና አባላት በሃዲቾ ጎሳ አባላት ላይ ጉዳት ከማድረሳቸው በፊትና በዝግጅት ላይ እያሉ «ለወንዶገነት ወረዳ፣ ለሲዳማ ዞን አስተዳደር፣ ለደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንና ለሚመለከታቸው ተቋማት ሁሉ ግንቦት ቀን 2007 .ም አቤቱ ታችንን ብናቀርብም በወቅቱ ምላሽ ባለመስጠታቸው ጉዳቱ ተፈጥሯል» ብለዋል።
በተፈጠረው ችግር የአንድ ሰው ህይወት አልፏል፣ ሌሎችም ቆስለዋል፣ ከ60 በላይ ቤቶች መቃጠልና ዘረፋ ደርሷል፣ ቋሚ ተክሎች በገጀራ መጨፍጨፍና ሌሎች ጉዳቶችን እንዳደረሱባቸው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም ለሚመለከታቸው አካላት ችግራቸውን ቢያስረዱም ከጥቃቱ ሙሉ በሙሉ መፍትሄ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አጥፊዎችን እንዲያርምላ ቸውና በህገ መንግሥቱ የተሰጣቸውን መብት እንዲከበርላቸውም ይጠይቃሉ ። በተለይም ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆኑ፣ ችግሩ ሲፈጠር ቶሎ ምላሽ ያልሰጡና ተከባብረው የኖሩትን ጎሳዎች ወደ ግጭት እንዲገቡ ያደረጉትን አካላት መንግሥት እንዲጠይቅላቸው አቤቱታቸውን ያቀርባሉ።
የወንዶገነት ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጎሳዬ ጎዳና በሰጡት ምላሽ፤ምንም ሰው እንዳልሞተና የክልሉ150 የሚሆኑ ልዩ ኃይል አባላት፣ ከዞንና ከወረዳ ፖሊሶች ጋር በቅንጅት ችግሩን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አንስተዋል።
ከረብሻው ጋር በተያያዘ 68 ሰዎች የተያዙ ሲሆን፣ ማጣራት ተደርጎ 12 ተጠርጣሪዎች በፖሊስ ጣቢያ እንደሚገኙና ሌሎቹ ከችግሩ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ስለሆኑ ተለቀዋል። 25 ሰዎች ጉዳት አድርሰዋል በሚል ተጠር ጥረው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥቶ እየተፈለጉ እንደሆነ ያስረዳሉ።
«የከፋ ጉዳት አልደረሰም» ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ የጠፋውን ንብረትም ኮሚቴ ተቋቁሞ በማጣራት ላይ እንደሆነ ጠቅሰዋል። የተፈጠረው ግጭት በጎሳዎች መካከል የተፈጠረ ሳይሆን በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል የተፈጠረ እንደሆነም ያመለክታሉ።
ግጭቱን ለማስቆም የተሰማሩ አስራ አምስት የወረዳው ፖሊሶች፣ የልዩ ኃይል አካላትና የወረዳው አመራሮች መቁሰላቸውንና የዜጎች ህይወት እንዳያልፍ ከፍተኛ መስዋዕትነት መከፈሉንም የወረዳው አስተዳዳሪ ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች ተነጋግረው የተፈጠረው ችግር ቆሟል። ጉዳት ለደረሰባቸውም ወረዳው ቁሳቁስ እያቀረባለቸው ይገኛል። የአካባቢው ህብረተሰብ የተቃጠሉትን ቤቶች ለመስራት እየተነጋገረ ነው።
የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በበኩላቸው፤ «እኛ ጋር የመጣ ሁለት መስመር ወረቀት የለም። መጣም አልመጣም ስራችን በመሆኑ ግጭቱ እንደተከሰተ የፈጸሙትን አካላት ለመቆጣጠር ተችሏል። ፖሊስ ቀድሞ እርምጃ አልወሰደም የሚለው መሰረተ ቢስ ክስ ነው። ችግር ከተፈጠረበት ወቅት አንስቶ ከሃምሳ በላይ የክልሉ አድማ በታኝ ኃይል በስፍራው ይገኛል» ብለዋል።
በግጭቱ አንድ ሰው መሞቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ የሁሉት ጎሳ ግጭት ነው የሚለው ግን የተሳሳተ እንደሆነና በተወሰኑ ሰዎች መካከል የተነሳ ግጭት መሆኑን አንስተዋል። ሰው የገደሉትን፣ ቤት ያቃጠሉትንና ንብረት ያወደሙትን ወንጀለኞች ፖሊስ አድኖ በመያዝ ችግሩን እያጣራ እንደሚገኝና ወንጀለኞቹን ለህግ ለማቅረብ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
«እኛ ችግሩን ለመቆጣጠር እየሰራን ባለንበት ወቅት ቅሬታ ይዞ ወደ ሚዲያ መሄድ ተገቢ አይደለም» ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በአካባቢው ያለው ግጭት መቶ በመቶ መቆሙን አረጋግጠዋል። ማህበረሰቡም የግጭቱ መንስኤ ትክክል አለመሆኑን በመወያየትና ችግሩ እልባት አግኝቶ ወንጀለኞቹን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ምንጭ፦http://www.ethpress.gov.et/addiszemen/index.php/news/national-news/item/1310-2015-06-17-04-31-25

0 comments :