የቀብር ማስፈጸሚያ የመድን ሽፋን አገልግሎት ተጀመረ

 የቀብር ማስፈጸሚያ የመድን ሽፋን አገልግሎት ተጀመረ
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የቀብር ማስፈጸሚያ የመድን ሽፋን አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ ለደንበኞቹ መስጠት መጀመሩን አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ የወንድወሰን ኢተፋ እንደገለጹት፥ አገልግሎቱ የሰው ሞትን ተከትሎ የሚመጡና  የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪዎችን በተሟላ ሁኔታ የሚሸፍን የዋስትና አይነት ነው።
ሽፋኑ በእድር ላልታቀፉ ዜጎች አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ያሉት ስራ አስፈጻሚው ፥ እየናረ የመጣውን የቀብር ማስፈጸሚያ ወጪን ለመሸፈን ከእድሮች ጋር በመቀናጀት የሚሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
ድርጅቱ በመላው አገሪቱ በሚሰጠው አገልግሎት ከአንድ ትሪሊዮን ብር በላይ ለሆነ ንብረት የመድን ሽፋን መስጠቱን አመልክተዋል።
በደንበኞቹ ንብረትና ህይወት ላይ ለደረሰ ጉዳትና ከሶስተኛ ወገን ለቀረበባቸው ህጋዊ ኃላፊነት 6 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ በመፈጸም አጋርነቱን እያረጋገጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የተዘጋጀው የመድን ሽፋን ዕድሜ፣ ጾታ፣ ሃይማኖት ሳይለይና የጤንነት ሁኔታን ሳይጠይቅ  ለሁሉም ዜጎች የሚያገለግል ሲሆን፥ በተጨማሪ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ሽፋኑን ለገዙ ዜጎች የመድን ዋስትና ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከተቋቋመ 39 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን በመላው አገሪቱ በሚገኙ 66 ቅርንጫፎቹ የተለያዩ የመድን ሽፋን አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል።
ምንጭ፦ኤፍ.ቢ.ሲ

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር