የዘጠኝ ፓርቲዎች ትብብር ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን በጊዜ እንዲወስድ ጥሪ አቀረበ

የዘጠኙ ፓርቲዎች ትብብር በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ በመሳተፍ ከጐኑ መቆም ያስችለው ዘንድ፣ የምርጫ ካርድ በመውሰድ ዝግጅቱን እንዲጀምር ጥሪ አስተላለፈ፡፡  
ትብብሩ ይህን ያሳወቀው ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም. ‹‹በነፃነት ለፍትሐዊ ምርጫ የጀመርነው ነፃነታችንን የማስመለስ ትግል ይቀጥላል›› በሚል ርዕስ በሰማያዊ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ሲሆን፣ መግለጫውን የሰጡት ደግሞ የትብብሩ ሰብሳቢ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት፣ ምክትል ሰብሳቢው አቶ ኤርጫፎ ኤርዴሎና ዋና ጸሐፊው አቶ ግርማ በቀለ ናቸው፡፡ 
‹‹የትግሉ ቀዳሚና ዋነኛ ባለቤት የሆንከው መራጩ ሕዝብ ነፃነትና ክብርህን ለማስመለስ በምናደርገው ትግል በንቃት እንድትሳተፍ ዛሬውኑ በመመዝገብ፣ የሥልጣን ባለቤትነትህን የምታረጋግጥበትንና ይህን አምባገነናዊ ሥርዓት የምትቀጣበትን ትጥቅ ‹‹የምርጫ ካርድህን›› በእጅህ እንድታስገባ ጥሪያችንን እናቀርባለን፤›› በማለት ሕዝቡ የምርጫ ካርዱን በጊዜ ወስዶ እንዲጠባበቅ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በመጀመርያ ዙር በጋራ የትብብሩ እንቅስቃሴዎች የትግሉን አስፈላጊነት፣ ወቅታዊነት፣ የዓላማና የትግል ሥልት ትክክለኛነት በተግባር ማረጋገጡን ትብብሩ የገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይም ትብብሩ ያስገኛቸውን ውጤቶች በመመዝገብ በሁለተኛ ዙር ላስቀመጠው ዕቅድ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በመጀመሪያው ዙር የተመዘገቡት ውጤቶች ምን ምን እንደሆኑ ሪፖርተር ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፣ የትብብሩ ኃላፊዎችም ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡ 
ባለፈው የመጀመሪያ ዙር እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድል እንዳስመዘገቡ የገለጹት የትብብሩ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኤርጫፎ፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፍ ለማድረግ ተነስቶ በነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ገዥው ፓርቲ በወሰደው ዕርምጃ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ለማድረግ ዝግጁ አለመሆኑን አሳይቷል›› በማለት ‹‹ይህም ለትብብሩ ትልቅ ድል ነው፤›› ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ‹‹በኅዳር 27 እና 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መንግሥት ዕውቅና አልሰጥም ሲል ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድ አይገባንም በማለት በተጠራው ሠልፍ፣ ምንም እንኳን ዋጋ ቢያስከፍለንም ይህ በራሱ እንደ ስኬት የሚቆጠር ነው፤›› ሲሉ ምላሽ የሰጡት ደግሞ የትብብሩ ዋና ጸሐፊ አቶ ግርማ በቀለ ናቸው፡፡ 
ትብብሩ በመግለጫው መራጩ ሕዝብ የምርጫ ካርዱን በጊዜው እንዲወስድ ከማሳሰብ በተጨማሪ በውጭ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ በተቃውሞ ጐራው ለተሳተፉ ፓርቲዎች፣ በተለይም ለመድረክ አባላት ፓርቲዎችና ለአንድነት ፓርቲ፣ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡ 

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር