POWr Social Media Icons

Saturday, December 6, 2014

ቴላሞ የጡማኖ  መታሰቢያ

sidma tomano memoraial
የጡማኖ መካነ መቃብር እና የሃገር ሽማግሌው አቶ ሲዳሞ ቢረጋ

ከለኩ ከተማ በስምንት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኘው ቴላሞ ነው፤ ቴላሞ የሲዳማ አድባር ነው ሲሉ የሃገር ሽማግሌዎቹ ይገልጻሉ፡፡ አረንጓዴ ምድር ምን ማለት እንደሆነ በቴላሞ ቅጥር ግቢ ያሉት ሃገር በቀል ግዙፍ የዛፍ ዝርያዎች ለትውልድ የቆሙ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ መልከአ-ምድራዊ ውበቱ ይማርካል፤ ከደኑ መሃል በአጥር የተከበበ አንድ ቅጥር አለ፤ በዚህ ቅጥር ውስጥ የሲዳማ ነገድ አባት የሆነው የጡማኖ መቃብር ይገኛል፡፡ በስፍራው በየእጽዋቱ ስር የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች ይገኛሉ፤ እንደ አካባቢው ሽማግሌዎች ገለጻ እነዚህ የአረብኛ ጽሁፍ ያለባቸው ድንጋዮች መቃብሮች ናቸው፡፡
ሲዳሞ ቢራጋ የሃገር ሽማግሌ ናቸው፤ በየግዜው ለተለያየ ጉዳይ ወደ ቴላሞ ይመጣሉ፤ ይህንን ስናጠናቅር በስፍራው ያገኘናቸውም ለተመሳሳይ ዓላማ በቴላሞ ውብ ቅጥር ግቢ ለውይይት አረፍ እንዳሉ ነው፡፡ የሲዳማ የሃገር ሽማግሌዎች የሚለብሱትን ባህላዊ አለባበስ የለበሱት አቶ ሲዳሞ ቢራጋ ስፍራውን በሚመለከት አንዳንድ ጥያቄዎችን ስናቀርብላቸው በማራኪ አተራረክ ለዛ መልሰውልናል…መነሻችን ደግሞ ቴላሞ ምንድን ነው የሚል ነበር አቶ ሲዳሞ በተረጋጋ ሁኔታ ረጃጅም የቅጥሩ ዛፎች ላይ አይናቸውን ተክለው አብራሩልን….
 
ይሄ ቦታ ቴላሞ ይባላል፤ ጡማኖ የሲዳማ አባት ነው፤ እዚህ ነው የተቀበረው፤ ቦታው ብዙ ዓመቱ ነው….ማን ይቆጥረዋል ብዙ ነው፤ እዚህ የወለደ ሰው አሁን አስራ ስድስት ትውልድ ሆኗል፡፡
የቅጥሩን ዙሪያ ገባ በዓይናቸው ቃኘት አድርገው መልሰው ወደ ሽማግሌዎቹ በመመልከት የቴላሞን አካባቢ ሁለንተናዊ እሴት በወፍ በረር መተረኩን ቀጥለዋል…..
በዓመት በዓመት ኮርማ ይገባል….ማር ይጠመቃል፤ ሃገሩን ይጠራል፣ ይደግሳል…እንዲህ ነው የሲዳማ ባህል….ፍቼ አለ፤ በጨምባላላ በጣም ብዙ ኮርማ ይገባል፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ ሸንጎ ተቀምጠን የተጣላ ሰው፣ ሰው የገደለ ሰውም ቢሆን  እናስታርቅበታለን፣ ሽምግልና አለ…ሸንጎው ይሰበሰብበታል፣
ወደ ሌሎች ሽማግሌዎች ተመለከቱ….. ሁሉም እንደሳቸው ግርማ ሞገስን የተላበሱ፣የሲዳማ የሃገር ሽማግሌዎች የሚለብሱትን አለባበስ የለበሱ ነበሩ፣ አቶ ሲዳሞ ቀጥለዋል ስለ ቴላሞ ስለ ጡማኖ መካነ-መቃብር ቅጥር እና ስለሚከናወንበት ሥነ-ሥረዓት
ዝናብ እንቢ ሲል በኛ ባህል  ጭዳ ይደረጋል፤ እዚህ ቦታ ጭዳ ተደርጎ እርድ ይታረዳል፤ እግዜርን ይለምናል፤ ሽማግሌውም ሸንጎውም ብዙ ስራ አለው….. አካባቢውንም የሚጠብቀው ሸንጎው ነው….እኛ ነን…..ደኑ እዚህ ያለው በአጠቃላይ በአካባቢው ሁሉ ነበር ድሮ .…እኔ ሰማኒያ አመቴ ነው፤ እኔ ልጅ ሆኜ ደኑ ሌላ ነው፤ ጫካ ነበር…. አውሬ ነበር….ሰው እየበዛ ሲሄድ ደኑ ጠፋ….አውሬው ሸሸ
በደኑ ማካከለኛ ስፍራ ያለው ባለ በር የእንጨት አጥር ቅጥር የጡማኖ የመቃብር ስፍራ ነው፤ እንደሌሎቹ አካባቢዎች ቤት አልተሰራበትም ለምሳሌ ወንሾ እና ፋቂሳ ቤት ተሰርቶባቸዋል፡፡ ይሄ ምን ይሆን ብለን ለአቶ ሲዳሞ ጥያቄ አቀረብንላቸው
አዎ የመቃብር ቤት አልተሰራም…በረት ብቻ ነው፤ ቤት የመስራት ሀሳብ አለን ጉልበት አጣን የምንሰራው ቀላል ቤት አይደለም፤ ጉልበት ግን አጣን ድሮ አባቶቻችን ለመስራት እያሰቡ ጉልበት አጡ፤ አሁን እኛ ደረስን ጉልበት አነሰን የሚያግዘን እየፈለግን ነው ግን እንሰራልን
ወደ ስፍራው የሚመጡ ሽማግሌዎች ቁጥር እየጨመረ ነው…. ዛሬ በአንድ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ይመክራሉ፤ ከዛፎቹ ጥላ ስር አጎዛ ተነጥፎ እዛ ላይ አረፍ ብለው እየተጠባበቁ ነው፡፡ ስፍራው በብዝሃ ህይወት የታደለ ነው፡፡ በአካባቢው ያለው አየር ይለያል… ሲስቡት የሚያረካ ንጹህ አየር…. ተፈጥሮ የምታሸንፍበት …..ባህል፣ተፈጥሮ፣ታሪክ….በአንድ የከተሙበት የመስህብ ስፍራ….ቴላሞ፤

ፋቂሳ
የፋቂሳ መካነ መቃብርና አካባቢው
sidma fikisa memorial  
ፋቂሳ እንደ ቴላሞ ሁሉ የሲዳማ የታሪክ አድባር ነው፡፡ ፋቂሳ የጡማኖ ልጅ ነው፤ በዙሪያው ያለው አካባቢ ቀድሞ ምን ይመስል እንደነበር  የፋቂሳ ቅጥር ግቢ እጽዋት እና መልከአ-ምድራዊ ውበቱ ማሳያ ነው፡፡ ረጃጅም ዛፎች…ሃገር በቀል እጽዋት፣ ደስ የሚል ነፋሻ አየር…. ወደ ቅጥር ግቢው ዘለቅን፣ ከእጽዋቱ ማኽል ግዙፍ ባለ ግርማ ሞገስ ቤት ቆሟል፡፡ በቅጥሩ የጠበቁን የሃገር ሽማግሌዎች መግባት የምንችልበት የቅጥሩ ክልል ድረስ ተጠግተን እንድንጎበኝ ፈቀዱልን….ማንም የሌለበት የሚመስለው ቅጥር የእንግዳ እግር እንደረገጠው ከግራና ከቀኝ ሽማግሌዎች ይሰበሰቡበታል፡፡
አቶ አሰፋ ጃሰነ የሃገር ሽማግሌ ናቸው፣ ወደ ቅጥሩ ከመግባታችን ከተፍ አሉ…ዓላማችን መጎብኘት መሆኑን ስለተረዱ  ስለአካባቢው ተጨማሪ መረጃዎችን ገለጹልን ስለ ፋቂሳ የታሪክ አድባርነት እየተረኩልን በሲዳማ ባህል የሃገር ሽማግሌ አለባበስ የለበሱ አንድ ሽማግሌ ወደ አለንበት ስፍራ መጡ በስፍራው የነበሩ ሁሉ ለሽማግሌው አክብሮት በመቸር ሰላምታ አቀረቡ፤ እኒህ ሰው ከንባታ ኢቲሶ ይባላሉ፤የሃገር ሽማግሌ ናቸው ማንን አስፈቅደን ወደ ቅጥሩ እንደገባን ቀልድ ባዘለ ቅላጼ ጠየቁን ዓላማችንን ነገርናቸው…ከፊታቸው ላይ ፈገግታ ተጻፈበት….ፈገግታውን አንብበን ጥያቄአችንን ቀጠልን…እርስዎ በዚህ ስፍራ ያለዎት ኃላፊነት ምንድን ነው ከሚለው ጀምረን……
እኔ ዙሪያውን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለኝ ነኝ፤ ክልሉን እጠብቃለሁ፣ ይሄ ስፍራ ባህላዊ ሥረዓት የሚከናወንበት ጥብቅ ስፍራ ነው፡፡ ፍቼ የሚባል የሲዳማ ዘመን መለወጫ ባአል አለ በዚያን ግዜ ብዙ ነገር ይደረጋል፡፡ ሌላ ግዜ ደግሞ የሞሳሉ ሰዎች አሉ ስዕለታቸውን ያስገባሉ፣ በዚህ በዚህ ግዜ እርድ ይኖራል፡፡
በእጃቸው የያዙትን ብትር ትከሻቸውን አስደግፈው….ጨዋታቸውን ቀጠሉ
የተጣላ በሚኖርበት ግዜ እርቅ የሚደረገው እዚህ ነው፤ ያኔ ሸንጎው ይሰበሰብበታል፡፡ ዝናብ ሳይዘንብ ሲቆይ ከብት አርደን ፈጣሪን ምንለማመነው እዚህ ነው፤ ደኑ አካባቢው የጥንት ነው አባቶቻችን የመሰረቱት…አሁን ይሄን ዝግባ እዩት አስራ አራት አባት አስቆጥሯል፡፡
ፋቂሳ የባህል እና የትውፊት መአከል ነው›››››

ምንጭ፦ ቱባ

0 comments :