POWr Social Media Icons

Saturday, December 6, 2014

እ.ኤ.አ. በ2012 መጨረሻ አቅራቢያ፣ ሊበርታድ የተባለችውና ንብረትነቷ የአርጀንቲና ባሕር ኃይል የሆነችው ወታደራዊ ማሠልጠኛ መርከብ በዓለም አቀፍ የሕግ አስከባሪ አካል በቁጥጥር ሥር የዋለችው፣ በጋና ቴማ ወደብ አቅራቢያ
ሲሆን በዚያ ለሁለት ወራት ከሁለት ሳምንት እንድትቆይ ተገዳለች፡፡ ከዚህች መርከብ ባሻገር ንብርትነቱ የአርጀንቲና የሆነው ፕሬዚዳንታዊ አውሮፕላንም ሲበር ከነበረበት አገር ተይዞ በቁጥጥር ሥር ለመዋል በቅቷል፡፡ በዚህ አላበቃም፡፡ በአሜሪካው ፌዴራል ሪዘርቮ ባንክ የሚከማቸው የአርንቲና ማዕከላዊ ባንክ ተቀማጭ እንዳይንቀሳቀስ ከመደረጉ በላይ እንዲወረስ መደረጉ የሚታወስ የቅርብ ጊዜ ክስተት ነው፡፡   
አርጀንቲናውያን ከጥቂት ሰዎች በተበደሩት ገንዘብ ሳቢያ ዕዳ አለባቸው እንበል፡፡ እውነታው ይሄው ነው፡፡ መሠረቱ በአሜሪካ ሆነ መቀመጫውን ኬመን ደሴት ያደረገውና ከአሜሪካ ውጭ በመንቀሳቀስ፣ የተለያዩ ፈንዶችን በማስተዳደር ከሚታወቀው ኤንኤምኤል ካፒታል ከተባለው ኮርፖሬሽን ጋር በተፈጠረ ቅራኔ ሳቢያ ነበር ንብረቶቹ የታገዱት፡፡ የኒውዮርክ ፍርድ ቤት በፍትሐብሔር ክስን ባስቻለበት ወቅት፣ ኤንኤምኤል ኮርፖሬሽን በአርጀንቲና ያለኝ ከ800 ሚሊዮን ዶላር በላይ ዕዳ ይከፈለኝ ሲል ጠይቋል፡፡   
አርጀንቲና እ.ኤ.አ በ2001 በነበረባት የ82 ቢሊዮን ዶላር የብድር ቃልኪዳን ሰንድ (ሶቨሪን ቦንድ) ዕዳ በወቅቱ ለመክፈል አልቻለችም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1989 እስከ 2000 ድረስ በዘለቀውና አርጀንቲናን በመታው የፋይናንስ ቀውስ ሳቢያ፣ አገሪቱ ያለባትን የብድር ዕዳ ለመክፈል ሳትችል መቅረቷ፣ የአገሪቱን የቦንድ ሰርቲፊኬት የገዙ የውጭ ኢንቨስተሮችን ድንጋጤ ውስጥ የከተተ ክስተት ነበር፡፡ አርጀንቲና ዕዳዋን ለመክፈል አለመቻሏ ብቸኛ አገር ባያሰኛትም፣ አዲሱ ክስተት ግን ዕዳውን አለመከፈሏን ተከትሎ የተነሳው የሕግ ጥያቄ ነበር፡፡ እንደሌሎች አገሮች ሁሉ አርጀንቲናም የተቆለለባትን የዕዳ ሥሪት በማስተካከል የተወሰነውን መጠን ለመክፈል ተስማምታለች፡፡ ሆኖም ኢንቨስተሮቹ የተደረገውን ማስተካከያ በመቃወም፣ ከቦንድ ብድሩ ማግኘት የሚገባቸው ሙሉ ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ይጠይቃሉ፡፡ የኢንቨስተሮቹን ጥያቄ ሊያስተናግድ የሚችል አቅም ግን አርጀንቲና አልነበራትም፡፡ ከዕዳ ጠያቂዎቹ አንዱ የሆነው ኤንኤምኤል ግን አገሪቱን ለማስገደድ የሚያስችል አቅም ነበረው፡፡ ይህንን ተከትሎ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች አገሪቱ ከገባችበት ቀውስ የማገገሟ ተስፋ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን ተንብየው ነበር፡፡ 
የአርጀንቲናን ታሪክ ለኋላ እናቆየውና የዓለም ፋይናንስ ባለሙያዎች እንዲህ ዓይነቱ ክስተት በፋይናንስ ገበያው ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ በማስመልከት ያላቸውን ሥጋት መመልከቱ ይበጃል፡፡ አገሮች ከዓለም ገበያ ፈንድ በብድር ሲገዙ ጥንቃቄ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው ባለሙያዎቹ ይመክራሉ፡፡ ይህ ምክራቸው ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ እንደ አዲስ እየተሟሟቀ የሚገኘውና ኢትዮጵያም ዘግይታ የተቀላቀለችውን የቦንድ ሻጮች ቀጣና በሰፊው ይመለከታል፡፡ 
ባለፈው ሳምንት ከአውራዎቹ ሕግ አውጪዎች የተውጣጣ ቡድን በአውሮፓና በአሜሪካ ግብኝት አድርጎ፣ ኢትዮጵያ አንድ ቢሊዮን ዶላር የቦንድ ሰርቲፊኬት ለዓለም ገበያ ማቅረቧን ይፋ አድርጓል፡፡ ቡድኑ ይፋ ላደረገው ቦንድ ከገመተው በላይ የኢንቨስተሮች የቦንድ ግዥ ጥያቄ እየቀረበለት ሲሆን፣ ለግዥውም ከቀረበው የቦንድ መጠን በላይ ዋጋ እየቀረበ ነው፡፡ 
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች አርጀንቲና የገጠማት ችግር እኛም ላይ ይደርሳል በሚል ፍራቻ ዓለምአቀፍ ቦንድ ከመሸጥ መታቀብ እንደማይገባ ያስጠነቅቃሉ፡፡ በተቃራኒው የቦንድ ገበያውን በመቀላቀል በሚገኘው ጥቅም ላይ ይስማማሉ፡፡ ታዋቂው ኢንሹራንስ ዘርፍ ባለሙያ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ እንደሚሉት፣ አትዮጵያ የዓለም የቦንድ ገበያን መቀላቀሏ ተቀባይነት ያለውና አወንታዊ ዕርምጃ ነው፡፡ የኧርነስት ኤንድ ያንግ ኢትዮጵያ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱም የዕርምጃውን ወሳኝነት የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 
እርግጥ ዓለም አቀፍ ሚዲያው ኢትዮጵያ ካላት የነፍስ ወከፍ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ገቢ አኳያ ከድሆች ሁሉ ድሃ በመሆኗ፣ ዓለምአቀፍ ቦንድ ለመሸጥ እንደሚቸግራት ዘግበዋል፡፡ ይህም ቢሆን የካፒታል ገበያውን የመቀላቀል ዕርምጃው ዓለም ለአገሪቱ ያለውን አወንታዊ ምልከታ የሚያረጋግጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሆኗል፡፡ 
ዞሮ ዞሮ ሶቨሪን ቦንድን መሸጥ ብድር የመጠየቂያ መሣሪያ መሆኑ እውነት ነው፡፡ የቦንድ ታሪክ ወደኋላ በመሔድ ከ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ በጊዜው አገሮች ለተንዛዙ የጦርነት ተልኳቸው በቂ ገንዘብ ለማግኘት ይጠቀሙበት ነበር፡፡ በዚያን ዘመን መንግሥታት ከገዛ አገራቸው ለጦርነት ማፋፋሚያ ፈንድ ለማግኘት እንዲችሉ ቦንድ ይሸጡ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ቦንዶቹ የሚሰጡት ጠቀሜታ እየጨመረ በመምጣት፣ በዓለም መድረክ እየተሸጡ የየትኛውም አገር ዜጎች ቦንዶቹን በመግዛት ኢንቨስት የሚያደርጉበት ሥርዓት ሆኗል፡፡ ከዚህ በመነሳት ቀድመው የነቁ አገሮች በውጭ መገበያያ ገንዘቦች ቦንዶችን በመሸጥ ጠቀም ያለ የፋይናንስ ካፒታል ማሰባሰብ የሚችሉበት መንገድ እንደሆነ ተረዱ፡፡ የኢኮኖሚ ታሪክ አጥኚዎች እንደሚሉት፣ እንዲህ ያሉት ቦንዶች የሶቨሪን ቦንድ ወይም ዩሮ ቦንድ እየተባሉ ለሚጠሩት የዚህ ዘመን መሣሪያዎች መነሻ ምንጮች ሆነዋል፡፡
ታዳጊ አገሮች በተለይም ከሰሃራ በታች የሚገኙት ከዓለም ቦንድ ገበያ ውጭ ሆነው እስከቅርብ ጊዜ የቆዩት በኢኮኖሚያቸው ደካማነት ሳቢያ ነበር፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ2000 አጋማሽ ወዲህ ባለው የዓለም ኢኮኖሚ ሁኔታ የተነሳ ለድሆቹ አገሮች ከጥንት ጀምሮ አበዳሪ የነበሩት አገሮች ሳይቀሩ ማጥ ውስጥ በመግባታቸው የተነሳ፣ ድሆቹ ታዳጊዎች አማራጭ ለማፈላለግ ተገደዱ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢንቨስተሮች እንደ አፍሪካ ያሉና ጠቀም ያሉ የብድር ወለድ ሊሰጧቸው የሚችሉ የቦንድ ምንጮችን ማነፍነፍ ጀምረው ነበር፡፡ እዚህ ላይ ‹‹ሁለቱ ተገጣጠሙ›› ማለት ይቻላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ቆስጠንጢኖስ በርኸተስፋ (ዶ/ር)፣ የአውሮፓ ኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ በገባበት ሰሞን እንደኢትዮጵያ ያሉና አሁን ቦንድ መሸጥ የጀመሩ አገሮች ኢኮኖሚ ግን አወንታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብ ላይ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ ይህ በመሆኑም ኢንቨስተሮች ወደ ቦንድ ገበያውና ከአደጉ አገሮች ሶቨሪን ቦንድ ውጪ ወደሌሎች የብድር ዘዴዎች እንዲመጡ፣ አፍሪካውያኑ ለዓለም አቀፍ ቦንድ ገበያ ያቀረቡትን ለመግዛት እንዲሳቡ ያደረገ እንደነበርም ምሁሩ ያብራራሉ፡፡
አቶ ዘመዴነህ እንደሚያስታውሱት፣ እ.ኤ.አ. በ2007/08 የተከሰተውን የፋይናንስ ቀውስ ተከትሎ፣ ያደጉር አገሮች መንግሥታት በትልልቅ የፋይናንስ ወይም የካፒታል ገበያዎች ውስጥ ጣልቃ እንዲገቡ ያስገደደና ዕድገታቸውን የገታ ክስተት እንዲፈጠር ምክንያት ነበር፡፡ ‹‹ሁኔታው ብድር የመሸከም አቅማቸው ከፍተኛ የሆነና በብድር ምዘና አውጪ ተቋማት ሦስት A ያገኙ አገሮች ሳይቀሩ በወቅቱ ብድር ማግኘት እንዳይቻላቸው ያደረገ ነበር፤›› በማለት ያስታውሱታል፡፡ ይህ በእሳቸው ምልክታ መሠረት ኢንቨስተሮች በሌሎች የብድር መሣሪያዎች ማለትም ከታዳጊ አገሮች ለገበያ የሚቀርቡ ሶቨሪን ቦንዶች ላይ ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ነፀብራቅ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡ ለአቶ ዘመነዴነህ ደግሞ ክስተቱ በአሜሪካና በሌሎች መንግሥታት የተደረገውና ከገበያው ቦንድ በመግዛት ገንዘብን ወደ ኢኮኖሚው የማስገባት ተግባር፣ አገሮችን ከቀውስ ውስጥ ለማውጣት ወሳኙን ሚና ተጫውቷል፡፡ ‹‹ይህ መሆኑ የወለድ መጠንን ወይም የመበደሪያ ዋጋን በመቀነስ ታዳጊ አገሮች ርካሽ ፋይናንስ እንዲያገኙ አስችሏል፤›› በማለት ይገልጹታል፡፡ 
እ.ኤ.አ. በ2006 ሲሺየልስ ከሰሃራ በታች አገሮች(ደቡብ አፍሪካን አይጨምርም) የሶቨሪን ቦንድ በመሸጥ ቀዳሚ ሆነች፡፡ ጥቂት ቆይቶ እንደ ጋና ያሉ አገሮች የ750 ሚሊዮን ዶላር ቦንድ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሸጥ ሲከተሉ፣ ሴኔጋል፣ ኮትዲቯርና ሌሎችም ተቀላቅለዋል፡፡ ኬንያ ከቡድኑ ዘግይታ፣ ከኢትዮጵያ ቀድማ የሁለት ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ለገበያ አቅርባለች፡፡
ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ እንደሚገልጹት፣ የሶቨሪን ቦንድ ገበያው የአፍሪካ አገሮች ስምንት ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ ማግኘት የቻሉበት ተመራጭ ገበያ ለመሆን በቅቷል፡፡ ይህ ደግሞ እነዚህ አገሮች የተጎሳቆሉ መሠረተ ልማቶቻቸውን ለማደስ አስችሏቸዋል፡፡ ኢተዮጵያም ርካሹን ፋይናንስና የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ገበያውን ተቀላቅላለች፡፡ አቶ ኢየሱስወርቅ ዛፉ የቦንድ ሽያጩ አገሪቱ ለዘረጋቻቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ወሳኝ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ‹‹ብዙ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ነገሮችን አልገነባንም፡፡ ያሉን እንደ ቡና፣ ቅባት እህልና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህ ከገበያ ዋጋ ጋር የሚዋዥቁ በመሆናቸው እስከዚህም አስተማማኝ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች አይደሉም፤›› በማለት የቦንድ ሽያጩ አማራጭ የብድር መሣሪያ መሆኑን ያሳያሉ፡፡ 
የማክሮ-ኢኮኖሚ ባለሙያው ኢዮብ ተስፋዬ (ዶ/ር) የውጭ ቦንድ ገበያ ውስጥ መግባቱ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱን ቁጠባ መጠን ከመደጐም አንፃር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡ በአገሪቱ ከሚታየው መሠረተ ልማት የግንባታ አኳያ፣ ይህንን ፋይናንስ ለማድረግ የሚያችል አቅም ከአገር ውስጥ ማግኘት እንደሚከብድም አብራርተዋል፡፡ 
ይህም ሲባል ግን ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች የውጭ ቦንድ ሽያጭ የሚያስከትላቸውን የሥጋት መዘዞች መዘንጋት እንደማይገባ ያሳስባሉ፡፡ በጠቅላላው ግን ኢትዮጵያ ብድር ከምታገኝባቸው መስኮች ሁሉ አሁን ላይ፣ ከዓለም ቦንድ ገበያ የምታገኘው ብድር ውድ የሚባለው እንዳልሆነ ባለሙያዎቹ ይጠቁማሉ፡፡ በዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስትና በአፍሪካ ቀጣና የድህነት ቅነሳና የኢኮኖሚ አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት ላርስ ክርስቲያን ሞለር ኢትዮጵያ ከውጭ ቦንድ በ6.6 ከመቶ ወለድ ለመበደር መነሳቷ፣ በፊት ትበደርበት ከነበረው ሁለትና ሦስት ከመቶ የብድር ወለድ አኳያ ሲታይ ውድ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ከሁለትዮሽ የብድር ምንጮች ይገኝ የነበረው ብድር የሚከፈልበት ትልቁ የወለድ ምጣኔ አራት ከመቶ ነው፡፡ እስከ 13 ዓመት የሚቆይ የብድር መክፈያ ጊዜ ነበረው፣ እንደ ዓለም ባንክ ባሉ በባለብዙ ወገን የብድር ሰጭ ተቋማት ዘንድ ዳግም የብድሩ መክፈያ ጊዜ እስከ 38 ዓመት ሊራዘም ይችላል በማለት አስረድተዋል፡፡
የአርጀንቲና ቀውስ በተነሳበት ወቅት በዚያ ይሠሩ ለነበሩት አቶ ዘመዴነህ ግን ትልቁ የውጭ ቦንድ ሥጋት፣ ቦንዱን ለሽያጭ በሚያቀርበው አገር ውስጥ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ አለመጣጣም ነው፡፡ ‹‹እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ አርጀንቲና ከውጭ በከፍተኛ ደረጃ ተበድራ የነበረ ቢሆንም በመጨረሻው አሥር ዓመት ግን የኢኮኖሚዋ ዕድገት መቀዛቀዝና የመገበያያ ገንዘቧ መግዛት ከሚችለው በላይ ዋጋ ተሰጥቶት ነበር፤›› በማለት አስታውሰዋል፡፡ ጥቂት ቆይቶም አገሪቱ ለተበደረችባቸው ቦንዶች ዕዳ ተገዥ መሆን እንዳልቻለች ግልጽ ከመሆኑም ባሻገር ክሶችና አቤቱታዎች እንዲያዋክቧት ምክንያት ሆኗል፡፡
በጠቅላላው የውጭ ምንዛሪ መለዋወጥ ለውጭ ብድሮች በጥቅሉ ለዩሮ ቦንድ ደግሞ በተናጠል ከፍተኛ ሥጋት ሆኖ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለዚህ በተለይ በውጭ አገር ገንዘቦች የሚገባው ዕዳ ዋናው መንስዔ ነው፡፡ ሞለር እንዳብራሩት፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሲቀንስ በብር ታሳቢ የሚደረገው የብድር መጠን ወዲያውኑ ይጨምራል፡፡ ‹‹ለአብነት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር በአሁኑ ወቅት ባለው የምንዛሬ ምጣኔ መሠረት 20 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ነገር ግን የምንዛሪው ተመን ወደ 22 ብር ከፍ ቢል ተመሳሳይ መጠን ላለው ብድር (የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር) የሚከፈለው 22 ቢሊዮን ብር ይሆናል፤›› በማለት በምሳሌ አስረድተዋል፡፡ እርግጥ እንዲህ ያለው ተጋላጭነት እንደኢትዮጵያ ዝቅተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ባለው አገር ላይ እንደሚብስ ባለሙያዎቹ ይሞግታሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ወደ ውጭ የሚላክ ምርት ሳይኖር፣ ከውጭ ለመግዛት የሚያስችለው ከሁለት ወር ብዙም ፈቅ ለማይል ጊዜ ነው፡፡ ሞለር እንደሚሞግቱት ከኢትዮጵያ የመንግሥት ዕዳ ውስጥ ግማሽ ያህሉ በዶላር የሚከፈል በመሆኑ የምንዛሪ ችግሩን ያባብሰዋል የሚል ስጋት አለ፡፡ 
ከውጭ የሚገኘው ብድር በማክሮ-ኢኮኖሚው ላይ ሊያስከትል ስለሚችለው ፈተና ለመረዳት በዝርዝር ጉዳዩን ማየት ይመርጣሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ይላሉ ዶ/ር ኢዮብ በብድር የሚገኘው ገንዘብ የሚውልበት መስክ በቅጡ ማየት ያስፈልጋል፡፡ የግሪንክን ታሪክ ዋቢ ያደረጉት ባለሙያው፣ አገሪቱ ከውጭ ምንጮች የተበደረችውን ገንዘብ በሙሉ ያን ያህል ምርታማ ባልሆኑ የፍጆታ መስኮች ላይ በማዋሏ፣ በመጨረሻ ለአበዳራዎች ዕዳዋን መክፈል ሳትችል እንድትቀር ምክንያት ሆኗታል፡፡ 
ዶክተር ኢዮብና ዶክተር ሞለር እንደሚያሳስቡት ከሆነ፣ በብድር የሚሠሩ ፕሮጀክቶች የአፈፃፀም ሁኔታ ሌላው ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ መሠረተ ልማት ለመገንባት ፋይናንስ ማግኘቱ አንዱ ፈተና ቢሆንም፣ ማስፈጸም አለመቻል ደግሞ ሌላኛው አደጋ ነው፡፡ ‹‹ከውጭ የመጣው ብድር ሥራ ላይ ሳውል በተቀመጠ ቁጥር፣ ተጨማሪ የወለድ ወጪ እየተከማች ይሄዳል፤›› የሚሉት ዶ/ር ሞለር ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ የውጭ ምንዛሪ አደጋ ወይም ሌሎች እንደሚሉት ዕዳን የመሸከም አቅም፣ ዋናው ቁም ነገር የውጭ ዕዳ የመከማቸት ችግር ነው፡፡ እንደ ዓለም ባንክ መረጃ፣ ኢትዮጵያ ስምንት ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ብድር ከሁለትዮሽ አበዳሪዎች ያገኘች ሲሆን ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ቻይና ትሸፍናለች፡፡ እንደ ሶቨሪን ቦንድ የወለዱ መጠን አይብዛ እንጂ፣ እንዲህ ያሉት ብድሮች በብዛት ግዴታዎች ያስከትላሉ፡፡ ይህ እንግዲህ የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የሰጠውን የሦስት ቢሊዮን ዶላር የረጅም ጊዜና የአነስተኛ ወለድ ብድርን የሚያካትት ነው፡፡
ሁሉም ባለሙያዎች እንደሚስማሙበት፣ የኢትዮጵያ አጠቃላይ የብድር ክምችት ከኢኮኖሚው አኳያ(ከጠቅላላ ምርት አኳያ) ከ50 በመቶ በታች መሆኑና በሁሉም ዓይነት መመዘዎች የዕዳው መጠን ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት ብድር በማስተዳደር ረገድ ወገቡን ጠበቅ ማድረግ እንደሚገባው ይመከራል፡፡
ብዙዎችን ያስገረመው የአርጀንቲና ስንክሳር እስካሁን ማብቂያ አለማግኘቱ ነው፡፡ ምንም እንኳ የአርጀንቲና መንግሥት በአፋጣኝ ጣልቃ ገብቶ ጉዳዩን ለመቀልበስ ቢሞክርም፣ ኤንኤምኤል ወዲያኑ አካሔዱን በመቀየር የአርጀንቲና መንግሥት ከሌሎች አበዳሪዎች ዘንድ ለኩባንያው መከፈል ያለበት ዕዳ እስካልተከፈለ ድረስ ብድር እንዳያገኝ አድርጐታል፡፡ 
በመሆኑም አርጀንቲና በአሁኑ ወቅት ከዓለም ገበያ ፋይናንስ እንዳታገኝ እጇ ተሳስሮ እንዳትቀመጥ ሆናለች፡፡ 
http://www.ethiopianreporter.com/index.php/business-and-economy/item/8151-%E1%8B%A8%E1%8B%8D%E1%8C%AD-%E1%89%A6%E1%8A%95%E1%8B%B5-%E1%88%BD%E1%8B%AB%E1%8C%A9%E1%8A%93-%E1%88%A5%E1%8C%8B%E1%89%B6%E1%89%B9

0 comments :