የዝቅተኛ ደመወዝ ወሰንየለሹ ኢኮኖሚ

ያሰረችው የወየበ ሻሽ ሙሉ በሙሉ ፀጉሯን አልሸፈነላትም፡፡ አቧራ የጠጣው ፀጉሯ በዚህም በዚያም አፈትልኮ ይታያል፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 17 አቅራቢያ ከሚገኝ የግንባታ ሳይት ላይ ያገኘናት አብነት ነጋሽ፣ ፀሐይ የጠበሰው ፊቷ ስለ ሥራዋ ፈታኝነት ብዙ ይናገራል፡፡ ምንም እንኳ ወቅቱ ሙቀት ቢሆንም አብነት በልብስ ላይ ልብስ ደራርባለች፡፡ ሱሪ፣ በሱሪ ላይ ቀሚስ፣ ሹራብ፣ አንገቷ ላይ ሻርፕ አድርጋለች፡፡ በካልሲ የተጫማችው አሮጌ ኮንጐ እንደዚያ መውጣት መውረድ ባለበትና ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚጠይቅ የሥራ አካባቢ ምቾት የሚሰጥ አይመስልም፡፡ ምንም እንኳ ከታች እስከ ላይ እንደዚያ መልበሷ ከሥራው ጋር እንዲሄድ በማሰብ ቢሆንም፡፡ 
ሸዋ ምንጃር አካባቢ የተወለደችው የ33 ዓመቷ አብነት የምትኖረው ገርጂ አካባቢ ሲሆን ከሥራ ቦታዋ የምትገኘው ማልዳ በመነሳት በእግሯ ተጉዛ ነው፡፡ መንገዱ አንድ ሰዓት የሚወስድባት ሲሆን ዘወትር ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ከሥራ ገበታዋ ትገኛለች፡፡ ትራንስፖርት፣ ቁርስና አለባበስ የሚባሉ ነገሮች ለሷ ብዙ ትርጉም የሚሰጡ ነገሮች አይደሉም፡፡ ስትመለስም በተመሳሳይ መልኩ በእግሯ እያዘገመች ነው፡፡ ረዥም ሰዓት መሥራት፣ በቀላሉ ንፁህ ውኃ ማግኘት አለመቻል፣ በተወሰነ መልኩ እንኳ ተመቻችተው ልብስ የሚቀይሩበት ወይም የሚመገቡበት ቦታ አለመኖር የየዕለቱ የሥራ ላይ ፈተናዎቿ ናቸው፡፡ በቀን የሚከፈላት 35 ብር ነው፡፡ ‹‹ቀን በቀን ሁሉም ነገር እየጨመረ የሚከፈለው ምንም ማለት አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ካልሠራን ምን እንበላለን፤›› ትላለች፡፡ 
ወርቅነህ ፈለቀ የመንገድ ሥራ ላይ በተሰማራ አንድ ኮንስትራክሽን ኩባንያ የፌራዮ ሠራተኛ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ ድርጅቱ በመንገድ ሥራው ላይ ከተሰማራ ከሞላ ጐደል ሁለት ዓመት ሊሆነው ቢሆንም እንደ ሔልሜት፣ ጓንትና ቱታ የመሳሰሉትንና ለሠራተኞች የሥራ ላይ ደኅንነት ወሳኝ የሆኑትን ቁሳቁስ ሳያሟላ ሠራተኞች በአነስተኛ ክፍያ ሕይወታቸውን ግን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ውስጥ እንዲሠሩ እያደረገ መሆኑን ይናገራል፡፡ ግንበኛ፣ እንደሱ ያለ የፌራዩ ሠራተኛ በተወሰነ ደረጃ ባለሙያ በመሆኑ ከሌላው ቀን ሠራተኛ ጋር ሲነፃፀር ሻል ያለ ክፍያ የሚያገኝ ቢሆንም በአጠቃላይ ክፍያው ትንሽ ስለመሆኑ ግን ‹‹ብዙዎቻችን እዚሁ አካባቢ የምንኖር በመሆናችን የትራንስፖርት የምግብ ወጪ ስለሌለብን እንጂ ከምንሠራው ጋር ተመጣጣኝ ክፍያ እያገኘን አይደለም፤›› በማለት ለማስረዳት ይሞክራል፡፡ 
በብዙ ትግል ውስጥ አልፈው የሠራተኛ ማኅበር መመሥረት ከመቻላቸው በፊት ሠራተኞች በሥራ ላይ ምንም ዓይነት አደጋ ቢደርስባቸው ሕክምና የሚባል ነገር እንዳልነበር፣ ይልቁንም ፎርማንም ሆነ ኢንጂነር እንደፈለጉ ሠራተኞችን ያባርሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወርቅነህ እንደገለጸልን በወቅቱ የሠራተኛ ማኅበር እንዲመሠረት ጥረት ያደረጉ ሠራተኞች ተባርረዋል፡፡ ከምሥረታ በኋላም ማኅበሩ ወደ ክስ አምርቶ ነበር፡፡ ከረዥም ጊዜ የክስ ሒደትና ጫና በኋላ ኩባንያው ለሠራተኛው የራስ መከላከያ ቆብና ቱታ የሰጠው አጠቃላይ የመንገድ ግንባታው በተገባደደበት ወቅት ላይ እንደነበር ያስታውሳል፡፡  
ርሳሽ የሰው ጉልበትን ታሳቢ በማድረግ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኮርፖሬሽኖች ወደ አገሪቱ እየገቡ ነው፡፡ በአገሪቱ የተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎታቸውን ያሳዩም ጥቂት አይደሉም፡፡ ወደ ኮንስትራክሽን ዘርፉ ሲመጣ ደግሞ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 494/1998 ላይ አንድ አሠሪ የሠራተኛውን ደኅነነትና ጤንነት የመጠበቅ ብሎም ከአደጋ መከላከልን የሚመለከቱ መመሪያዎችን የመከተል ግዴታ እንዳለበት በግልፅ ያስቀመጡ ቢሆንም፣ ሠራተኞች በዝቅተኛ ደመወዝን ከዚህም ሲያልፍ ደኅንነታቸው ባልተጠበቀበትና ሕይወትቸውን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ ውስጥ በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ 
በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ገብሩ፣ ደመወዝ በግሉ ዘርፍ አሠሪና ሠራተኛ ተነጋግረውና ተደራድረው የሚወስኑት ጉዳይ መሆኑ በሕግ የተቀመጠ መሆኑን፤ የደመወዝ መሻሻልም በተመሳሳይ መልኩ ለድርድር የተተወ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል ይላሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት አገሪቱ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ባለው የኢኮኖሚ ሥርዓት የምትመራ እንደ መሆኗና የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ አቅም እንደሚያመላክተውም ደመወዝ መወሰን ያለበት ሙያና እውቀት ባላቸው ተፈላጊነትና የገበያ ዋጋ ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ የአገሪቷ እውነታ ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ ይሁን ቢባል የሚያስኬድ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም ሰዎች ከዚህ በታች በሆነ ክፍያ አይቀጠሩም ከተባለ ሥራ አጥ ለሚሆኑ ሰዎች በዝቅተኛ ደረጃ የተቀመጠውን ክፍያ መክፈል የሚችል የኢኮኖሚ አቅም መኖሩ የግድ ይሆናልና ነው፡፡
‹‹ይኼ ኢኮኖሚክስ ነው፡፡ ሰዎች ከዚህ በታች አይቀጠሩም ሲባል መንግሥት ባይቀጠሩ የተቀመጠውን ዝቅተኛ ክፍያ ለእነዚህ ሰዎች የመክፈል አቅም ላይ መድረስ አለበት፤›› ይላሉ፡፡ 
የመንግሥት ታክስ የመሰብሰብ አቅም ሲያድግ፣ መሠረተ ልማቶች ሲስፋፉ በጥቅሉ ኢኮኖሚው ሲያድግ የሠራተኛው ማኅበራዊ ዋስትና ይመጣል በማለት ያስረዳሉ፡፡
አንድ ዓይነት ሙያ ገበያው ላይ በጣም ተፈላጊ ቢሆን ወይም በዚያ የተለየ ሙያ የሠለጠነ ሰው እጥረት ሲኖር በዚያ ሙያ የሠለጠኑ ሰዎች አማርጠው የተሻለ ክፍያ የማግኘት ዕድላቸውን የተጠበቀ ማድረጉ የዝቅተኛ ደመወዝ ወሰን አለመኖር አዎንታዊ ገፅታ ነው በማለት ያስቀምጣሉ፡፡ ይህን ቢሉም ግን ከዚህ በተቃራኒ የሆነ እውነታ ማለትም በአንድ የተወሰነ ሙያ ላይ የሰው ኃይል መትረፍረፍ ቢኖር ለባለሙያዎቹ የዝቅተኛ ደመወዝ ወሰን መኖር ዋስትና እንደሚሆንም አመልክተዋል፡፡
እንደ አቶ ፍቃዱ ገለጻ መንግሥትም ዝቅተኛው የደመወዝ እርከን መቀመጥ እንዳለበት ያምናል፡፡ ነገር ግን ከሥራ አጥነት ጋር በተያያዘ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድርበት ዕድል መኖሩን ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ በአሁኑ ወቅት ትልቁ ነገር ሥራ አጥነትን መቀነስ ሲሆን ጐን ለጐን ሠራተኛው እንዴት እየተጠቀመ ይሄዳል የሚለው ላይ መሥራት ትክክለኛው አካሄድ ነው የሚል እምነት አላቸው፡፡
ቢሆንም ግን የአንዳንድ የግል ድርጅቶችን ለሠራተኛ የምግብና የትራንስፖርት አቅርቦት ማሟላትን፣ የሠራተኞች ማኅበራዊ ፈንድ ሥርዓት መዘርጋትን በመጥቀስ ‹‹ሩቅ በማይባል ጊዜ ዝቅተኛ ደመወዝን ወደ መወሰን ማምራታችን አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡ ይህን እናድርግ ሲባል ግን እያንዳንዱ ሥራ በሚገባ መጠናት፣ መታወቅና መመዘን ያስፈልገዋል ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ሠራተኛ ማኅበራት ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ዘገየ ኃይለሥላሴን በግሉ ዘርፍ የሠራተኛ ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ አለመሆን በብዙ መልኩ ችግር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ብዙዎችን እየቀጠረ ባለው የኮንስትራክሽን ዘርፍ ሠራተኞች ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ እየሠሩ የሚከፈላቸው ግን ዝቅተኛ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዘገየ፣ ቀኑን ሙሉ ሠርተው ሰላሳ አምስትና አርባ ብር የሚከፈላቸው ግንበኞች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ የሠራተኛ ማኅበርና የቀጣሪ የኅብረት ስምምነት ባለበት ደመወዝ ሊሻሻል ቢችልም በስምምነቱ የተቀመጠው ነገር እንኳ እንደማይጠበቅ ይገልጻሉ፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ኮንስትራክሽን ላይ በተሠማሩ የውጭ አገር ኩባንያዎችም ዝቅተኛ የሠራተኞች ክፍያ የተወሰነ አለመሆን በተለያየ መልኩ ችግር ነው፡፡ የሥራ ላይ ደኅንነታቸው የተጠበቀ አለመሆን ደግሞ የበለጠ ችግሩን አስከፊ ያደርገዋል፡፡ 
የተለያዩ ምክንያቶችን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ለሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴር ዝቅተኛ የሠራተኞች ክፍያ የተወሰነ እንዲሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ እንደሚያቀርብ አቶ ፍቃዱ ይገልጻሉ፡፡ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ጋሻውም ኮንፌዴሬሽኑ ለእነሱም ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ እንዲሆን በተደጋጋሚ እንደጠየቁ ይገልጻሉ፡፡ በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ የሠራተኛ ክፍያ የተወሰነ ባለመሆኑ የዝቅተኛ ጡረታን የሚወስኑት በመንግሥት ዘርፍ ያለውን ዝቅተኛ ጡረታ በመከተል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ተስፋዬ በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ የሠራተኛ ክፍያ የተወሰነ ቢሆን ከዚያ አኳያ ጡረታውን ለመወሰን ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 
በግሉ ዘርፍ ዝቀተኛውን የሠራተኛ ክፍያ ለመወሰን ያላስቻለው ኢኮኖሚው አቅርቦትና ፍላጐት ላይ የተመሠረተ መሆኑ ነው በማለት የአቶ ፈቃዱን ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ይጋራሉ፡፡ ዝቅተኛ ደመወዝን የተወሰነ ማድረግ ውድድርን ያዳክማል የሚል መከራከሪያ የሚያስቀምጡ ድርጅቶች መኖራቸውንም ይገልጻሉ፡፡ የሰዎች የሥራ ዝውውር በሕግ የተፈቀደ በመሆኑ፣ ሠራተኞች እንደፈለጉ ተወዳድረው የተሻለ ነገር የማግኘት ዕድላቸው የተጠበቀ መሆንም የሚጠቅስ ሌላ የመከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ የቅጥር ውድድር ምን ያህል ፍትሃዊ ነው የሚለው ጥያቄ ሆኖ በሌላ በኩለ በአንድ ዓይነት ሙያ ተመሳሳይ የሥራ ልምድ ያላቸው ሰዎች በተለያየ ኩባንያ ውስጥ በመሥራታቸው ብቻ የተለያየ ክፍያ የማግኘታቸው ነገር ፍትሐዊ አይደለም የሚሉም አሉ፡፡ 
‹‹እንደ ተቆጣጣሪ የመንግሥት አካል በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ የሠራተኛ ክፍያ የተወሰነ ቢሆን ጥሩ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፤›› ይላሉ አቶ ተስፋዬ፡፡ ዝቅተኛ ክፍያ የተወሰነ መሆን ሰዎች ለትንሽ ልዩነት ከኩባንያ ኩባንያ የሚያደርጉትን ዝውውር ሊቀንስ መቻሉ በአዎንታዊ ጐን የጠቀሱት ሲሆን ዝቅተኛ ደመወዙ የተወሰነ ለማድረግ ኢኮኖሚው ሊጠናና የሌሎች አገሮች ልምድም ከግንዛቤ ሊገባ ይገባል ይላሉ፡፡ በግሉ ዘርፍ ተቀጣሪ የሆኑ ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ እንዲሆን ይፈልጋሉ ጥያቄም ያቀርባሉ ግን በፍላጐት ብቻ ወደዚያ መሄድ ስለማይቻል ነገሩ ሊጠና ሁኔታው ያን ሊፈቅድ ይገባል፡፡ ለሠራተኛ ዝቅተኛ የጡረታ ወሰን እንዲያደርጉ የግል ተቋማት ሲጠየቁ ሠራተኞች ውጤታማ ባልሆኑበት የኢንዱስትሪ ሥራ ባህል በሌለበት ሁኔታ እንዴት የዚህ ዓይነቱ ነገር ግዴታ ይሆናል የሚል ክርክር ያነሳሉ፡፡
በግሉ ዘርፍ ሠራተኞች በዝቅተኛ ክፍያ፣ ያለጥቅማ ጥቅም ወይም ይህ ነው የማይባል ጥቅማ ጥቅም መሥራታቸው ብቻም ሳይሆን ደኅንነታቸውን አደጋ ላይ በሚጥል ሁኔታ መሥራታቸው ሌላ ችግር ነው፡፡ በግሉ ዘርፍ የሰው ኃይል ብዝበዛ አለ የሚሉት አቶ ተስፋዬ፣ ምንም እንኳ የቅጥር ስምምነት ምን መምሰል እንዳለበት በግልጽ በአዋጅ የተቀመጠ ቢሆንም ብዙ ጊዜ በዘርፉ ቅጥሮች የሚፈጸሙት ከተቀመጠው ውጭ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በምን ያህል ደረጃ ተፈጻሚ እየሆነ ነው? የሚለው ይሆናል፡፡
በካፒታሊስት ኢኮኖሚ የሀብት ክምችት እንደ ዕድገት ይታያል፡፡ ባለሀብቶች እጅግ እየበለፀጉ በሀብታምና በደሀው መካከል ያለው ልዩነትም እጅግ እየሰፋ ይሔዳል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ በግሉ ዘርፍ የሠራተኛ የደመወዝ ጭማሪና የጥቅማጥቅም ጥያቄ ወሳኝ ነው፡፡ የአሠሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር በግሉ ዘርፍ የዝቅተኛ ደመወዝ ወሰን ማስቀመጥ (የተወሰነ እንዲሆን ማድረግ) አስፈላጊና የማይቀር ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ይህ ዝቅተኛ ደመወዝ የሚወሰነው እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን የአገሪቱ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትና ሌሎች ሁኔታዎች ከግምት ገብተው መሆን እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ሠራተኛው ለመኖር የሚያስፈልገው ነገር ሊሰጠው ይገባል ቢሉም በተቃራኒው ጉዳዩ በአሠሪውና በሠራተኛው የኢኮኖሚ ግንኙነት የሚወሰን መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ዝቅተኛ ደመወዝን የተወሰነ የማድረግ ነገር የሚወሰነው በኢኮኖሚው ነው በሚለው ሀሳባቸው የአቶ ፍቃዱንና የአቶ ተስፋዬን አቋም የሚጋሩት አቶ ታደለ አገሪቱ ድህነትን ለማጥፋት እየታገለች መሆኗም ከግምት የሚገባ ነው ይላሉ፡፡ ስለዚህም ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ ይሁን ሲባል የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ተጠንቶ እንጂ እንዲሁ ከሌላ አገር ጋር ተነጻጽሮ መሆን የለበትም በማለት ለማስረዳት ይሞክራሉ፡፡
አቶ ታደለ እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን ቀጣሪዎች የሠራተኞች ዝቅተኛ የደመወዝ  ወሰን እንዲቀመጥ አይፈልጉም የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ቢኖርም እውነቱ ግን የተለየ ነው ይላሉ፡፡ 
በግሉ ዘርፍ የሠራተኛ ዝቅተኛ ደመወዝ የተወሰነ መሆን አስፈላጊነትን አጀንዳው ያደረገው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ ፓርቲያቸው የመንግሥትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ተቀጣሪ የሠራተኛ ዝቅተኛው ክፍያ አንድ ሺሕ ብር መሆን አለበት ብሎ እንደሚያምን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ኑሮ እጅግ ውድ በሆነበትና የገንዘብ የመግዛት አቅም በወረደበት ጊዜ፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እውነታ ውስጥ ይሔ ገንዘብ በተወሰነ መልኩ ለሠራተኛው የሚያግዝ ቢሆንም አጠቃላይ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ፡፡ በመሠረታዊ ሸቀጦች፣ በትራንስፖርት፣ በጤናና በሌሎችም ወጪዎች ሰዎች ላለመውደቅ እየታገሉ መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር ጫኔ በዚህ የኑሮ ግብግብ ውስጥ በተለይም የቀን ሠራተኞች ዋነኛ ተጐጅዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡  
ደመወዝን የገበያ ተወዳዳሪነት ይወስነዋል የሚባል ነገር የለም፡፡ ይልቁንም ደመወዝ የሚወሰነው የሠራተኛው አገልግሎት፣ የአገሪቱ የኑሮ ሁኔታና የሸቀጦች ዋጋ ከግምት ገብቶ መሆን እንዳለበት የሚያስረዱት የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ደምስ ጫንያለው ናቸው፡፡ የተጠቀሱት ነገሮች ከግምት መግባታቸው እንዳለ ሆኖ የመጨረሻ የሚባለው የደመወዝ ወሰን ደግሞ ከድህነት መስመር በላይ መሆንም ይኖርበታል ይላሉ፡፡ ሠራተኞች ባመረቱት ነገር ላይ ባለመብት በማይሆኑበት ይልቅም የሚያገኙት ክፍያ ብቻ በሆነበት አካሔድ በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ የደመወዝ ወሰን ሊቀመጥ ግድ ነው ይላሉ፡፡ 
ዶ/ር ደምስ ርካሽ የሰው ኃይልን (አቶ ፍቃዱ ግን ርካሽ ሳይሆን ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ነው ያለው ይላሉ) ፈልገው ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ያሉ የውጭ ኩባንያዎች ጉዳይ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ሰዎች ምርጫ እንዲያጡና በተሰመረላቸው መስመር ላይ ሆነው እንዲሠሩ የሚያደርጉ በመሆናቸው የደመወዝ ነገር በገበያው ይወሰን ተብሎ መተው የለበትም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ ማኅበራዊ ዋስትና ባልተረጋገጠበት እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር ውስጥ ዝቅተኛ ደመወዝን መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ፤ መንግሥት እንደ አስፈላጊነቱ ከሸቀጥ ዋጋ ጋር በተያያዘ የኢኮኖሚ ጣልቃ ገብነቱን እንደሚያሳይ ሁሉ ባለው የሰው ኃይል ገበያም ዝቅተኛ የደመወዝ ወሰንን በማስቀመጥ ጣልቃ መግባት እንዳለበት ያስረግጣሉ፡፡    

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር