በኢትዮጵያ የአፍረካ የቀርከሃ ልህቀት ማዕከል ሊገነባ ነው

የአፍሪካ  የቀርከሃ የስልጠናና ሰርቶ ማሳያ ማዕከል በ600 ሚሊዮን ብር ወጪ በኢትዮጵያ ሊገነባ ነው።
በአምስት ሄክታር ቦታ ላይ የሚያርፈው የማዕከሉ ግንባታ በደን ምርምር ማእከል በገፈርሳ ምርምር ጣቢያ ውስጥ ሀሙስ ጥቅምት 27/2007 ለማዕከሉ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
የግብርና  ሚንስትር ዴኤታው አቶ ስለሺ ጌታሁን እንዳሉት ማዕከሉ የአሰራርና የፈጠራ ችሎታን በማዳበር አዳዲስ የቀርከሃ ምርቶች የሚመረቱበትንና ለአገር ውስጥና ለውጭ  ገበያ የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል።
ማዕከሉ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጥሮ  የሚገኘውንና በባህላዊ መንገድ ብቻ ይመረት የነበረውን የቀርከሃ ምርት በማሻሻል ተክሉን በማልማት፣ በመጠበቅ፣ እሴት በመጨመርና አጠቃቀሙን ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ በማስፋፋት የገበያ ትስስር ለመፍጠር ይረዳል።
የልህቀት ማዕከሉ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለረጅምና ለአጭር ጊዜ ስልጠና ከሚመጡ ተሳታፊዎች ጋር የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
የዓለም ዓቀፉ የቀርከሃና ራታን መረብ ድርጅት በኢትዮጵያ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ሁንዴ እንደተናገሩት ማዕከሉ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲገነባ የተደረገው ኢትዮጵያ የድርጅቱ  አባል በመሆን በምክር ቤቱ ውስጥ ጉልህ አስተዋጽኦና የነቃ ተሳትፎ በማድረጓ ነው።
ማዕከሉ በአጠቃላይ ለሰርቶ ማሳያ የሚውሉ የቀርከሃ ማባዣ ችግኝ ጣቢያዎች፣ ሰው ሰራሽ የቀርከሃ ደን የሙከራ ተከላ ቦታ፣ የተለያዩ ዝርያዎችን መትከያና ማሳያ ቦታ፣ የማሽነሪዎች መትከያና የተግባር ስልጠና ቦታና የተለያዩ የቀርከሃ ዲዛይኖች ማሰልጠኛ አዳራሽ ያካተተ ነው።
ከሙያዊ ድጋፍ በተጨማሪ የማዕከሉ የግንባታ፣ የቀርከሃ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎችና ተጓዳኝ መሳሪያዎች ወጪ በቻይና መንግስት እንደሚሸፈን EBC ዘግቧል።

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር