ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› መጠን ዛሬ ይፋ ይሆናል

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያቀርበው ‹‹የሶቨሪን ቦንድ››  መጠን ዛሬ ይፋ እንደሚሆን ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር አመለከተ፡፡ 
የኢትዮጵያ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ››ን ለመሸጥ ከተመረጡ ኩባንያዎች ጋር መግለጫው በአውሮፓ እንደሚሰጥም የገንዘብና ኢካኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አህመድ ሽዴ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አቶ ሱፊያን አህመድ የሚመራ የኢትዮጵያ ቡድን ወደ አውሮፓ ማቅናቱን የገለጹት አቶ አህመድ፣ የኢትዮጵያን ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለመሸጥ ከተመረጡት አመቻች ኩባንያዎች ጋር በመሆን፣ በሚሰጠው መግለጫ ላይ ኢትዮጵያ በዶላር የምትሸጠው የዕዳ መጠን ወይም ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ይፋ ይሆናል ብለዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮም የዕዳ መጠኑን ወይም ቦንዱን ከሚገዙ ኢንቨስተሮች ጋር ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
ለዓለም አቀፍ ገበያው የሚቀርበው ቦንድ መጠንን ግን ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሽዴ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ማለት ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ለመገንባት ለኢትዮጵያውያን እንደቀረበላቸው ዓይነት የመንግሥት ሰነድ ሆኖ፣ ይኼኛው የሚለየው ለዓለም አቀፍ ገበያ ወይም ኢንቨስተሮች በዶላር ወይም በውጭ ምንዛሪ እንዲገዙት የሚቀርብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከውጭ የምታገኛቸው ብድሮች በረዥም ጊዜ የሚከፈሉና በአገሮች የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት ቀላል ወለድና ረዥም የዕፎይታ ጊዜን የሚሰጡ ናቸው፡፡
‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ግን በንግድ ወለድ መሠረት የሚገዛ ሲሆን፣ ገዢዎች ወደዚሁ ውሳኔ ከመግባታቸው በፊት የአገሪቱን ወይም የቦንዱ ባለቤት አገርን ብድር የመሸከምና አጠቃላይ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያው ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባሉ፡፡
የአንድ አገርን ወይም ድንበር ዘለል ኩባንያን ዕዳ የመሸከምና የመከፈል አቅም በማጥናት ደረጃ የሚሰጡ (ክሬዲት ሬቲንግ) ኩባንያዎችን በመቅጠር ኢትዮጵያ ብድር የመክፈልና የመሸከም አቅሟን ለመጀመርያ ጊዜ በማስጠናት የቢ ደረጃን ማግኘቷ ባለፈው ግንቦት ወር ይፋ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዚህ ምክንያትም ሚኒስትር ሱፊያን አህመድ፣ ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ ኢትዮጵያ መወሰኗን ይፋ ካደረጉ በኋላ ኅዳር 3 ቀን 2007 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በዝግ ስብሰባ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በተጠቀሰው ኅዳር 3 ቀን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት  ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርበው ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› በጥንቃቄ እንደሚመራ፣ በቦንድ ሽያጩ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ የሚውለውም በብር ሊሠሩ የማይችሉና የግድ የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ የፕሮጀክቶቹን ዓይነት በይፋ ባይገልጹም፣ ተጠቃሚ የሚሆኑት ፕሮጀክቶች በመገንባታቸው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ለውጥ ከማምጣት ባለፈ ብድሩን ለመክፈል የሚያስችል አቅም መፍጠር የሚችሉ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሪን የግድ ከሚጠይቁት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል የታላቁ የህዳሴ ግድብና በዕቅድ ተይዘው ያልተጀመሩት የባቡር ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ 
የኢትዮጵያ ብድር የመሸከምና የመክፈል አቅም ከኬንያ ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ኬንያ እ.ኤ.አ. በጁን ወር 2014 የሁለት ቢሊዮን ዶላር ‹‹ሶቨሪን ቦንድ›› ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማቅረቧን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ኬንያ ከሰጠችው ሁለት ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 500 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሚመለስ እንደሆነና በ100 ዶላር ላይም የ5.875 መቶኛ ወለድ እንደተጣለ ከዘገባዎች ለመረዳት ይቻላል፡፡ የተቀረው 1.5 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በአሥር ዓመት የሚከፈልና የወለድ መጠኑም 6.875 በመቶ ነው፡፡

Comments

Popular posts from this blog

ፓርቲው ምርጫ ቦርድ ከተፅዕኖ ነፃ ሳይሆን የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ማውጣቱን ተቃወመ

የሐዋሳ ሐይቅ ትሩፋት

በሲዳማ ክልል የትግራይ ተወላጆች ምክክር